የቱርክ ምርጫ እና የገዢው ፓርቲ ድል | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 02.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የቱርክ ምርጫ እና የገዢው ፓርቲ ድል

ቱርክ ዉስጥ ትናንት በተካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ ገዢው ወግ አጥባቂ የፍትህና ልማት ፓርቲ፣ በምህፃሩ «ኤ ኬ ፒ» 49,3 ከመቶ የመራጩን ድምፅ በማግኘት አሸንፏል። ፓርቲዉ ባለፈዉ የሰኔ ወር በተካሄደ ምርጫ ብቻዉንም ሆኖ በጥምረት መንግሥት መመሥረት ባለመቻሉ ነበር ትናንት ዳግም ምርጫ የተካሄደዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:00
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:00 ደቂቃ

የቱርክ ምርጫ

ከ550 የምክር ቤት መንበሮች 315 ን ያገኘው « » አሁን ካለ ተጣማሪ ቀጣዩን መንግሥት ሊመሠርት እንደሚችል ተገልጿል። የተቃዋሚው ሬፓብሊካዊው የሕዝብ ፓርቲ 26 ከመቶ፣ መፍቀሬ ኩርዳውያኑ ፓርቲ ደግሞ 10,7 ከመቶ አግኝተዋል። በምርጫው ጠንካራ የሆነው « » የፕሬዚደንት ሬቼፕ ጠይብ ኤርዶኻንን ስልጣን ለማጠናከር ያስቀመጠውን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ ሲል ሕገ መንግሥቱን ለመቀየር ጥረቱን እንደሚቀጥል የቱርክ ጠቅላይ ሚንስትር አህመት ዳቩቶጉሉ አስታውቋል። የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ይቀየር ዘንድ ሁለት ሶስተኛ፣ ማለትም፣ 330 የምክር ቤት እንደራሴዎች ድምፅ ያስፈልጋል።

« አስተማማኝ የምርጫ ሥርዓት፣ ግልጽ የሆነ መንግሥት እና ቢሮክራሲ አልባ የሆነ ፖለቲካ ለመፍጠር ሲባል አንድ አዲስ ሲቪል ሕገ መንግሥት እንድናቋቁም በአዲሱ ምክር ቤት ለሚወከሉት ፓርቲዎች በጠቅላላ ጥሪ አቀርባለሁ። »

አዲሱ ሕገ መንግሥት አስተያየት በነፃ የመግለጽን እና የሰብዓዊ መብት መከበርን ይበልጡን ይገድባል ሲሉ የተቃዋሚ ቡድኖች እና ብዙ ደጋፊዎቻቸው ተችተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ምክር ቤታዊው ምርጫ ትክክለኛ አልነበረም ሲሉ የመፍቀሬ ኩርዳውያን ፓርቲ ሊቀ መንበር ሴልሃቲን ዴሚርታስ ወቀሳ አሰምተዋል።

«ብዙም ጥረት ሳናደርግ ወደ 11 ከመቶ የመራጩን ድምፅ አግኝተናል። ሁነኛ የምርጫ ዘመቻ ልናካሂድ አልቻልንም። ምክንያቱም ፣ ሕዝባችንን እና ደጋፊዎቻችንን ከጥቃት በመከላከሉ ተግባር ላይ ማተኮር ነበረብን። »

የአውሮጳ ፀጥታ እና ትብብር ድርጅት በምክር ቤታዊው ምርጫ ዘመቻ ወቅት የታየውን የኃይል ተግባር፣ እንዲሁም፣ እጩዎች በመገናኛ ብዙኃን በነፃ እንዳይጠቀሙ በገዢው ፓርቲ ገደብ አርፎበታል ሲል ዛሬ በቱርክ መዲና አንካራ ከአውሮጳ ሕብረት የሚንስትሮች ምክር ቤት እና ከአውሮጳ ምክር ቤት ታዛቢዎች ጋር በአንደነት ያዘጋጀውን ዘገባ ባቀረበበት ጊዜ ተችቷል።

በቱርክ መንግሥትና ለኩርዶች የተሻለ መብት እታገላለሁ በሚለዉ የኩርዶች የሠራተኞች ፓርቲ «ፒ ኬ ኬ» ተጀምሮ የነበረዉ የሰላም ሂደት ባለፈዉ ሐምሌ ወር ከተቋረጠ በኋላ፤ በሀገሪቱ ዉጥረት ነግሶና የጦርነትና ያለመረጋጋት ሥጋትም ሰፍኖ ከርሟል። እራሱን እስላማዊ መንግሥት በምሕፃሩ የ«አይ ኤስ» አሸባሪ ቡድኖች ያደረጉዋቸዉ ጥቃቶች ሳይሆኑ አይቀሩም በተባሉ ሁለት ፍንዳታዎች ከ 100 ላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸዉና ሀገሪቱ በሶርያና በኢራቅ የገባችበት ጦርነት እንዲሁም ከ ሁለት ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ቱርክን በማጥለቅለቃቸዉ ሕዝቡን ለሽብር ሥጋት ዳርጓል። ፕሬዚዳንት ሬቼፕ ጠይብ ኤርዶኻን ይህን የተፈጠረ ሥጋት ለምርጫ ቅስቀሳ በመጠቀም ለድል እንደበቁ ነዉ የሚነገረዉ። የብራስልሱ ወኪላችን ገበያዉ ንጉሴ ዝርዝር ዘገባዉን ልኮልናል።

አርያም ተክሌ/ገበያዉ ንጉሴ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic