የቱርክ ሕዝበ-ውሳኔ ውጤት እና አንድምታው  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 18.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የቱርክ ሕዝበ-ውሳኔ ውጤት እና አንድምታው 

በቱርክ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ጥያቄ ላይ የተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ውጤት የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡበት ነው። ተቀራራቢው የድጋፍ እና የተቃውሞ ድምጽ የቱርክ ኅብረተሰብ መከፋፈል ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል። በሌላ በኩል ውጤቱ ሀገሪቱ ከአውሮጳ ኅብረት ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽእኖም እያነጋገረ ነው ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:48

የቱርክ ሕዝበ-ውሳኔ ውጤት


ባለፈው እሁድ ቱርክ ያካሄደችው ህዝበ ውሳኔ የቱርክ ፕሬዝዳንት ጠይብ ሬቼፕ ኤርዶሃን የሚፈልጉትን ውጤት አስገኝቷል ። ድምጽ ለመስጠት ከወጣው ህዝብ 51.41 በመቶው በቱርክ ህገ መንግሥት ላይ ማሻሻያ እንዲደርግ ተስማምቷል።ውጤቱ  ኤርዶሀንን እና ደጋፊዎቻቸውን አስፈንጥዟል።ማሻሻያው የቱርክን አስተዳደር ከፓርላሜንታዊ ወደ ፕሬዝዳንታዊ የመንግሥት ስርዓት የሚቀይር ነው ። በማሻሻያው ሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አይኖራትም ። አዳዲስ የምክትል ፕሬዝዳንቶች የሃላፊነት ቦታዎች ይፈጠራሉ ። የፕሬዝዳንቱም ሥልጣን  ይጠናክራል። ፕሬዝዳንቱ ቀድሞ ያልነበረውን ሚኒስትሮች የመሰየም፣ በጀት የማዘጋጀት እና አብዛኛዎቹን ከፍተኛ ዳኞች የመሾም ሥልጣን ያገኛል። ለብቻው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግና ፓርላማውንም መበተን ይችላል።

የሀገሪቱ ምክር ቤት ቀድሞ የነበረውን በሚኒስትሮች ላይ ምርመራ የማካሄድ ወይም እንዲካሄድ የመጠየቅ መብትን ይነጠቃል ሆኖም ከምክር ቤቱ አባላት ሁለት ሦስተኛው ከተስማሙ ፕሬዝዳንቱ ክስ ሊመሰረትባቸው የሚያስችል ሂደት እንዲጀመር ማድረግ ይችላል።48.59 በመቶ ድምፅ ሰጭዎች   ማሻሻያው ፕሬዝዳንቱ ሥልጣኑን በሙሉ ጠቅለው እንዲይዙ ስለሚያደርግ  ህገ መንግሥቱ እንዳለ ይቀጥል ሲሉ ነበር ድምጻቸውን የሰጡት ። ተቃዋሚዎች የእሁዱ ምርጫ ላይ ቅሪታ አቅርበዋል።በተለይ በመጨረሻ ሰዓት ላይ ማህተም ያልተደረገባቸው የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የተሰጠው ውሳኔ ህገ ወጥ ነው ሲሉ አቤቱታቸውን በማቅረብ የህዝበ ውሳኔው ውጤት ውድቅ እንዲደረግ ህጋዊ ሂደት ጀምረዋል።የህዝበ ውሳኔው ውጤት ይፋ እንደተደረገ ከተቀራራቢው ውጤት በመነሳት በህገ መንግሥታዊው ማሻሻያ ላይ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር የጠየቀው የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ዛሬ ደግሞ ቱርክ የቀረበባትን አቤቱታ እንድታጣራ ጠይቋል።የህዝበ ውሳኔውን ሂደት የታዘቡት ቱርክ አባል የሆነችበት የአውሮጳ ምክር ቤት እና በአውሮጳ የፀጥታ እና የጋራ

ትብብር ድርጅት በምህፃሩ OSCE ተወካይ ሴዛር ፍሎሪን ፕሬዳ  መጨረሻ ላይ የተቀየረው የድምጽ አሰጣጥ ህግ ተጽእኖ አሳድሯል ብለዋል ። ከዚህ ሌላ ህዝቡ ስለ ህዝበ ውሳኔው ምንነት አስቀድሞ በቂ መረጃ እንዲያገኝ አልተደረገም ሲሉም ተችተዋል።
«በህገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ጥያቄ ላይ የተካሄደው የሚያዚያ 8 ቱ ህዝበ ውሳኔ በተመጣጣኝ የመፎካከሪያ ሜዳ ላይ አልተካሄደም ። የማሻሻያው ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች እኩል እድል አልነበራቸውም ። ድምጽ ሰጭዎች ስለ ማሻሻያው ቁልፍ ጉዳዮች ገለልተኛ የሆነ መረጃ አልተሰጣቸውም። የሲቪል ማህበራት መሳተፍ አልቻሉም ። በሐምሌ 2016 ከከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለዴሞክራሲያዊ ሂደት ወሳኝ የሆኑ መሠረታዊ ነጻነቶችን ገድቧል።»
ቱርክን ከአውሮጳ ህብረት ጋር ካቃቃሯት ጉዳዮች አንዱ የአውሮፓ ህብረት አባል ለመሆን ስታካሂድ የነበረው ድርድር  መገታት ነው። ህብረቱ ሀገሪቱ ማሟላት አለባት የሚላቸውን በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ያተኮሩ መስፈርቶችን ለድርድሩ አለመቀጠል አንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል።ይህን የማይቀበሉት ኤርዶሀን ከአሁን በኋላ በኛ መንገድ ሂዱ የሚሉትን አውሮጳውያንን ሳይሆን ህዝባችን የሚለንን ነው የምናደምጠው ብለዋል ከእሁዱ ህዝበ ውሳኔ በኋላ ።ኤርዶሀን ሀገራቸው ለአውሮጳ ህብረት አባልነት በጀመረችውና ከተወሰነ ዓመታት ወዲህ በተገታው ድርድር እና  የሞት ቅጣትን መልሶ በመደንገግ ላይ ህዝበ ውሳኔ ሊካሄድ እንደሚችልም ጠቁመዋል።የዶቼቬለ የኢስታንቡል ዘጋቢ ዶርያን ጆንስ እንዳለው የአውሮጳ ታዛቢዎች አስተያየት እና የኤርዶሀን ዛቻ በድርድሩ ተስፋ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም። 

«አሁን ሁሉም ነገር ባለበት ነው ያለው ። የአውሮጳ ምክር ቤት እና ኦ.ኤስ.ሲ.ኢESCO ህዝበ ውሳኔው የተካሄደበትን መንገድ በጥብቅ አውግዘዋል።ይህ ደግሞ በአውሮፓ ያለውን ስጋት ያጠናክረዋል ። እናም ቱርክ ኤርዶጋን በሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ የአውሮጳ ህብረት ህብረት አባል መሆን አትችልም የሚለው አስተሳሰብ በአውሮፓ እንዲሰፍን አድርጓል ። ቱርክ ውስጥም ያለው ስሜት ተመሳሳይ ነው አውሮጳውያን ከቀድሞ በባሰ ሀገሪቱ በመጓዝ በምትፈልግበት አቅጣጫ ላይ ጣልቃ እየገቡ ነው የሚል ስሜት አለ ። እንደሚመስለኝ ከአውሮጳ ህብረት ጋር ስታካሂድ የቆየችው ድርድር ወደፊት የመራመዱ ተስፋ አናሳ ነው ። ግን እንደማይታገድ ተስፋ አለ።»
ጋዜጠኛ ዶርያን ይህን ቢልም ኦስትሪያን የመሳሰሉ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ከህዝበ ውሳኔው ውጤት በኋላ ቱርክ ጋር ለህብረቱ አብልነት የሚካሄደው ድርድር በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል ።  የጀርመን ፖለቲከኞችም ተመሳሳይ  ጥሪ አቅርበዋል።የጀርመን ጥምር መንግሥት አካል የሆነው የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ በምህፃሩ CSU ሊቀመንበር ማንፍሬድ ቬበር ይህን ካሉት የጀርመን ፖለቲከኞች አንዱ ናቸው።   

«ቱርክ አሁን በአውሮጳ ህብረት እይታ የተሳሳተ መንገድ ለመከተል ከመረጠች ከቱርክ ጋር ያለንን ግንኙነት እንደገና መፈተሽ አለብን ።ያ ማለት በቱርክ የአውሮጳ ህብረት አባልነት ማመልከቻ ላይ የምናካሂደው ድርድር በረዥሙ ጊዜ ሊቀጥል አይችልም።ለንግግር መቅረብ ያለበት የሁለቱንም ወገኖች ጥቅም የሚያስጠብቅ  አጋርነት ነው።ሆኖም የቱርክ ሙሉ አባልነት ከአሁን በኋላ

እንደ ግብ መያዝ የለበትም» የቱርክ ህዝበ ውሳኔ ተቀራራቢ ውጤት ህዝቡ ጥልቅ ክፍፍል ውስጥ እንደሚገኝ አመላካች ተደርጎ ተወስዷል ። ይህን መታዘቡን ያሳወቀው የጀርመን መንግሥት ክፍፍሉን ለማስወገድ በቱርክፖለቲካዊ ውይይት እንዲካሄድ ጠይቋል።አሜሪካንም የዜጎች መብት እንዲከበር አሳስባለች።ይሁንና እና ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን ከድሉ በኋላ ትናንት ባሰሙት ንግግር ማሳሰቢያዎቹን ከቁብ የቆጠሩት አይመስልም ።ከአሁን በኋላ ትችትም ሆነ ተቃውሞ ሊቀርብ አይገባም ሲሉ ያስጠነቀቁት ኤርዶሀን  ክፍፍሉን የሚያባባስ እንጂ የሚያቀል ሀሳብ አላቀረቡም ይላል ጋዜጠኛ ዶርያን ጆንስ ።
«ፕሬዝዳንቱ ትናንት ጠንከር ያለ ንግግር ነው ያደረጉት ።ስለ ህዝበ ውሳኔው የሚደረገው ውይይትም ሆነ ውዝግቡ አብቅቷል ትችቱም መቆም አለበት ብለዋል ። የህዝበ ውሳኔው ውጤት የተቃወሙትንም   «ተመልከቱ እንዴት ሽንፈታቸውን እንደሚያከበሩ» ሲሉ አሹፈውባቸዋል።ለእርቀ ሰላም የሚደረግ እንቅስቃሴ የለም ። ኤርዶሀን ከዚያ ይልቅ የሚከፋፍል ንግግር ነው ያደረጉት።ምንም እንኳን ከአንድ በመቶ በላይ በሆነ ድምጽ ቢያሸንፉም ትችቱ መቆም አለበት የሚል እምነት ነው ያላቸው።እናም ፕሬዝዳንቱ በተቃዋሚዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው።»
ጋዜጠኛ ዲርያን እንደሚለው ኤርዶሀን  ከሁለት ዓመት በኋላ ማለትም በጎርጎሮሳዊው 2019 በቱርክ ለሚካሄደው ምርጫ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ከአሁን መንገዱን እያመቻቹ ነው።ፀረ አውሮጳ

ንግግራቸውም ሆነ ዛቻቸው በህዝበ ውሳኔ ያጡትን ድምጽ ለማግኘት የሚጠቀሙበት ዘዴም ነው ይላል። 
« ከቱርክ ብሔረተኞች አብዛኛዎቹ በህዝበ ውሳኔው ልደገፏቸውም  የሚል ግምት አለ ።ለዚህም ነው ውጤቱ ተቀራራቢ የሆነው ። በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በሚካሄደው ምርጫ ኤርዶሀን የብሔረተኞች ድምጽ ያስፈልጋቸዋል ። እናም የሞት ቅጣት ተመልሶ ህጋዊ ይሁን አይሁን የሚለው ጉዳይ እና በአውሮጳ ህብረት ላይ የሚያነሱት ጥያቄ የብሔረተኞችን ቀልብ ለመሳብ ይጠቅማቸዋል ። እናም በዚሁ ይገፉበታል።ግን ጥያቄው እነዚህ ጉዳዮች ለህዝበ ውሳኔ ይቀርባሉ ወይ ነው ። ያን ካደረጉ የቱርክ እና የአውሮፓ ህብረት ግንኙነት አበቃለት።ከአውሮፓ ምክር ቤትም ሆነ ከአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትጋር የሚኖራት ግንኙነትም ጥያቄ ውስጥ ይገባል።እነዚህ ደግሞ ኤኮኖሚያዊ ተጽእኖም ይኖራቸዋል።»

የእሁዱ ህዝበ ውሳኔ ውጤት በቱርክ እና በአውሮፓ ህብረት እንዲሁም በቱርክና በጀርመን ግንኙነቶች ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ እንደማይቀር ቢገመትም ቱርክ በልዩ ልዩ መስኮች ለአውሮጳ አስፈላጊ መሆንዋ አውሮጳም ለቱርክ ጠቃሚ አጋር መሆኗ ግልጽ ነው። ስደተኞች ወደ አውሮጳ እንዳይገቡ ለመከላከል ከህብረቱ ጋር የደረሰችበት ውል ሁለቱን ወገኖች ከሚያስተሳስሯቸው ጥቅሞች አንዱ ነው ። ቱርክ የአውሮፓ ህብረት ዋነኛ የንግድ አጋር መሆንዋም ሌላው የጋራ ጥቅማቸው መገለጫ ነው።የነዚህ  ትስስሮች የወደፊት እጣ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው አሁንም ማነጋገሩ እንደቀጠለ ነው። 

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ 

Audios and videos on the topic