የተፎካካሪነት መለኪያው ምንድን ነው? | ኢትዮጵያ | DW | 03.12.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የተፎካካሪነት መለኪያው ምንድን ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን “ተፎካካሪ” ብለን እንጠራቸዋለን ብለው ከተናገሩ በኋላ ብዙኃን መገናኛዎች እና ብዙዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይቀሩ ቃሉን ወርሰው እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ይሁንና ተቃዋሚዎቻቸው የተፎካካሪነት ተክለ ቁመና ለማዳበር ሥማቸው ብቻ ሊበቃቸው አልቻለም፡፡

በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ

ባሳለፍነው ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፖለቲካ ድርጅቶቹ ጋር ያደረጉትን ውይይት ስመለከት የታሰበኝ ነገር ቢኖር፥ ኢሕአዴግ የተቃዋሚዎቹን ድክመት ለማሳየት ከፈለገ ለግልጽ ውይይት ጋብዞ በቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ማስተላለፍ ብቻ ይበቃዋል የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ ለዚህ የተቃዋሚዎች ድክመት ኢሕአዴግ ራሱም መልሶ ከተወቃሽነት አይድንም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን “ተፎካካሪ” ብለን እንጠራቸዋለን ብለው ከተናገሩ በኋላ ብዙኃን መገናኛዎች እና ብዙዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይቀሩ ቃሉን ወርሰው እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ይሁንና ተቃዋሚዎቻቸው የተፎካካሪነት ተክለ ቁመና ለማዳበር ሥማቸው ብቻ ሊበቃቸው አልቻለም፡፡ ባሳለፍነው ማክሰኞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፖለቲካ ድርጅቶቹ ጋር ያደረጉትን ውይይት ስመለከት የታሰበኝ ነገር ቢኖር፥ ኢሕአዴግ የተቃዋሚዎቹን ድክመት ለማሳየት ከፈለገ ለግልጽ ውይይት ጋብዞ በቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ማስተላለፍ ብቻ ይበቃዋል የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ ለዚህ የተቃዋሚዎች ድክመት ኢሕአዴግ ራሱም መልሶ ከተወቃሽነት አይድንም፡፡

“ተፎካካሪ” በሚል የቀረቡት 81 ፓርቲዎች መካከል ጥቂቶቹ ከስደት በመመለሳቸው እና ገና መደበኛ ምዝገባ ለማድረግ በዝግጅት ላይ በመሆናቸው አልተመዘገቡም፤ ነገር ግን ከተመዘገቡት መካከልም ቢሆን ምርጫ ቦርድ ሙሉ ማጣራት ቢያደርግ ብዙዎቹ የምርጫ አዋጁ የሚጠይቃቸውን ቅድመ ሁኔታ የማያሟሉ እና የራሳቸውንም መመሪያ የማያከብሩ ናቸው፡፡ እነዚህ የሥራ አስፈፃሚ አባላቶቻቸው የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም ፕሮግራም የሌላቸው መሆናቸውን በኩራት በሕዝብ ፊት ይናገራሉ፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥም ይህ ነገር ይታወቃል፤ እንዲያውም ለይስሙላ የተቋቋሙ ፓርቲዎችን “ሱቅ በደረቴ” እያሉ የሚጠሩበት ቋንቋ አላቸው፡፡

ውይይት “ከሱቅ በደረቴዎች” ጋር

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት እነዚህን ፓርቲዎች ለውይይት ሲጋብዝ ፓርቲዎቹን ሁሉ በእኩል ዓይን ለመመልከት እንደሞከረ ግልጽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የምርጫ ቦርድ እና የፖለቲካ ድርጅቶች አመዘጋገብ ሒደት በራሱ በፖለቲካ ሙስና የተሞላ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ፓርቲዎች ምንም የመፎካከር አቅም የሌላቸው፣ ሌላው ቀርቶ ቋሚ ጽ/ቤት የሌላቸው እና ምርጫ ወይም ስብሰባ ሲኖር ብቻ በአደባባይ የሚታዩ እና የማይቀየሩ መሪዎች ያሏቸው፣ ሕዝባዊ ቅቡልነታቸውም እጅግ በጣም ዝቅተኛ የሆኑ፣ ምርመራ ቢደረግባቸው የፖለቲካ ፓርቲ ተብለው ለመመዝገብ የሚያስችለውን ሕጋዊ ቅድመ ሁኔታ የማያሟሉ ናቸው፡፡

ኢሕአዴግ ከዚህ ቀደም እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲኖሩ የፈቀደላቸው መድብለ ፓርቲ ስርዓት በኢትዮጵያ መኖሩን ለማስረጃነት ቁጥራቸውን እና በመከፋፈላቸው አቅመ ደካማ በመሆናቸው አውራ ፓርቲ ሆኖ እንደወጣ ለማስመሰል እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም ትልልቆቹ ተፎካካሪዎች ውስጥ ጥቂት እሰጣ አገባ ሲከሰት ያንን ተጠቅሞ በገላጋይነት ሥም ፓርቲዎቹን ሲሰነጥቅ፣ ተቀባይነት ያላቸውን ቡድኖች ዕውቅና ነፍጎ ለአንጃዎች ሲሸልም፥ እነዚህን “ሱቅ በደረቴ” ፓርቲዎች ግን ቁጥራቸው እንዲበዛ ያለምንም እንቅፋት፣ ያለ ምንም ሥራ ሳይነኩ እንዲቆዩ አድርጓቸው ነበር፡፡

አሁን በኢትዮጵያ እየተካሔደ ያለውን ለውጥ እየዘወረ ያለው ኢሕአዴግ ራሱ ቢሆንም የቀደሙ ጥፋቶቹን በሙሉ አምኗል፡፡ ኢሕአዴግ ቀደምት ስህተቶቹን እና ድክመቶቹን ማመኑ ካልቀረ፣ የይስሙላ ፖለቲካ ድርጅቶቹንም ጉዳይ መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል፡፡ አለበለዚያ በመጪው ምርጫ ችግር መፍጠሩ አይቀርም፡፡

የመጀመሪያው ችግር ከምርጫ ሕጉ ነው የሚመነጨው፡፡ የምርጫ ሕጉ ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች አነስተኛም ቢሆን በጀት ይመድባል፡፡ ይሁን እንጂ የበጀቱ አንበሳ ድርሻ የሚተላለፈው የሕዝብ ተወካዮች ውስጥ መቀመጫ ላላቸው ፓርቲዎች ነው፡፡ እንደሚታወቀው ከኢሕአዴግ እና አጋሮቹ በስተቀር ፓርላማው ውስጥ መቀመጫ ያለው ሌላ ድርጅት የለም፡፡ ይህ ጉዳይ በኢሕአዴግ እና “ተፎካካሪዎቹ” መካከል ጉልህ ልዩነት ይፈጥራል፡፡ ልዩነቱ በበጀት ብቻ አይደለም፤ በደጋፊዎች ማንቀሳቀስ አቅምም ጭምር ነው፡፡

የድምፅ ሽሚያ

መራጩ ሕዝብ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ፖለቲካ የተቃዋሚዎች እና የገዢው ፓርቲ ደጋፊ ተብሎ በጥቅሉ ለሁለት ሊከፈል ይችላል፡፡ ተቃዋሚዎችን የሚመርጠው ሕዝብ ድምር ኢሕአዴግን ከሚመርጠው ሕዝብ ድምር ቢበልጥም ባይበልጥም የተቃዋሚዎች ድምፅ ሕጋዊ ቅድመ ሁኔታ የሚያሟሉትም፣ የማያሟሉትም ፓርቲዎች በተሰበሰቡበት ምኅዳር ውስጥ ለብዙ መከፋፈሉ ስለማይቀር፣ አሁን ባለው የምርጫ ስርዓት ኢሕአዴግ ማሸነፉ ቀድሞ የተጻፈ ጉዳይ ነው፡፡ የምርጫ ሕግጋቱ አሁን እየተከለሱ ቢሆኑም፣ የመንግሥት በጀት ክፍፍሉን ፍትሐዊ ማድረግ ቢቻል እንኳን “የሱቅ በደረቴ” ድርጅቶችን፣ ሕጋዊ ቅድመ ሁኔታ ከሚያሟሉት ድርጅቶች ጋር እኩል እንዲሻሙ፣ ብሎም የሕዝብን ንብረት ለቤተዘመድ የፖለቲካ ጫዋታ እንዲባክን ያደርጋል፡፡

ለውጡ ዴሞክራሲያዊ ይሆን ዘንድ ካስፈለገ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ኦዲት ጉዳይ በቸልታ ሊታይ አይገባም፡፡ “ውይይት” ተብሎ በተጠራው እና በመንግሥት ቴሌቪዥን በቀጥታ በተላለፈው በዚህ ሳምንት ውይይት፣ የአንዳንድ ድርጅት ኃላፊዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ 81ዱ ፓርቲዎች ተዋሕደው ሁለት ወይም ሦስት ፓርቲዎች እንዲሆኑ እንዲረዷቸው ተማፅነዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር እንደመሆናቸው “ተፎካካሪዎቻቸውን” በማደራጀት እና በማስተባበር የሚያጠፉት ጊዜም ይሁን ጉልበት የሚኖራቸው አይመስለኝም፡፡ ይሁን እንጂ “እሺ” ብለዋቸዋል፡፡ በእውነተኛ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ሊኖር የሚችለው እውነተኛ ውይይት ወይም ድርድር የፖለቲካ ምኅዳሩን፣ የምርጫ ሒደቶች እና ተዛማች ጉዳዮችን ሊያነሳ ይችላል፡፡ አንዱ ሌላውን በማደራጀት እና በማስተባበር እንዲረዳው መጠየቅ ግን “በፉክክር” ውስጥ ካሉ ፓርቲዎች በፍፁም የማይጠበቅ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ራሳቸውን ኦዲት ያድርጉ፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካልም (ምርጫ ቦርድ) ከተመረጥን ሕዝብ እናስተዳድራለን የሚሉ ድርጅቶች እውነትም ሕጋዊ ቅድመ ሁኔታዎችን ያሟሉ እንደሆን የማጣራት ኃላፊነት አለበት፡፡

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ« DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።