የተፈጥሮ አደጋ ግጭት ጦርነት | ጤና እና አካባቢ | DW | 30.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የተፈጥሮ አደጋ ግጭት ጦርነት

የተፈጥሮ አደጋዎች ብቻ ሳይሆኑ ግጭት ጦርነቶችም በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸዉ አያጠያይቅም። በአሁኑ ጊዜ 12 ሚሊዮን ሶርያዉያን እርዳታ ፈላፊዎች ሆነዋል። በዮርዳኖስ፤ ሊባኖስ እና ቱርክ የተሰደዱት ሰባት ሚሊዮኖች በጦርነት ግጭት ምክንያት ያላቸዉን ያጡ ይኖሩበት ይሠሩበት የነበረዉ አካባቢ ለአደጋ የተጋለጡ ወገኖች ናቸዉ።

ጦርነት ግጭት ወትሮ ይኖሩበት የነበረዉን አካባቢና የተፈጥሮ ይዞታ የቀየረባቸዉ በርካታ ሃገራት ሕዝቦች ለስደትና መፈናቀል ሲዳረጉ ማየት እየተዘወተረ የመጣ ጉዳይ ከሆነ ሰነባበተ። በግጭት ጦርነትም ሆነ በተፈጥሮ ቁጣ ምክንያት ለችግር ለተዳረጉ ወገኖች የምግብ ርዳታ በማቅረብ የሚታወቀዉ የጀርመኑ መንግሥታዊ ያልሆነ ግብረ ሠናይ ድርጅት ቬልት ሁንገር ሂልፈ፤ ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በሚንቀሳቀስባቸዉ ሃገራት በቅርበት ያስተዋለዉን ባቀረበበት ዘገባ በተለይ ሶርያ ዉስጥ የሚካሄደዉ የእርስ በርስ ጦርነት አስራ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን እርዳታ ፈላጊ አድርጓል። በአጎራባች ሃገራት ጭምር ለመሰደድ የተገደዱት ሚሊዮኖች ኑሯቸዉ ተመሰቃቅሏል። የቦምብ ፍንዳታዎች አካባቢያቸዉን ሲያተረማምሱ፤ ቤቶቻቸዉም ሲፈራርሱ በዐይናቸዉ አይተዋል። ተፋላሚ ኃይሎችም ሲታኮሱ እነሱ በመሃል ቤት ማምለጫ አጥተዉ ተሰቃይተዋል። ያኔም ሕይወታቸዉን ለማትረፍ መሸሽ መሰደድን መረጡ። ቱርክ ዉስጥ ብቻ በአሁኑ ጊዜ ሶስት ሚሊዮን ገደማ የሚገመቱ የሶርያ ስደተኞች ይገኛሉ። ከእነዚህ ዉስጥም አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት ሕፃናትና ወጣቶች ናቸዉ።

የጀርመኑ ቬልት ሁንገር ሂልፈ ፕሬዝደንት ቤርበል ዲክማን የድርጅታቸዉን ዓመታዊ ዘገባ ባለፈዉ ሳምንት በርሊን ላይ ሲያቀርቡ እራሳቸዉ በየስደተኞቹ መጠለያ ተገኝተዉ ያስተዋሉትን ስሜት በተቀላቀለዉ መንገድ ነበር የተናገሩት። እሳቸዉን እጅግ ያስገረማቸዉ ደግሞ የስደተኞቹ ሶርያዉያን ከኖሩበት አካባቢ ጋ እጅግ የተቆራኙ መሆናቸዉ ነዉ።

«በጣም ያስደነቀኝ ነገር ቢኖር፤ ስደተኞቹ በሙሉ ወደሶርያ መመለስ መፈለጋቸዉን ማስተዋሌ ነዉ። ወደሀገሩ መመለስ የማይፈልግ በፍፁም አላጋጠመኝም። ሶርያዉያን ከትዉልድ አካባቢያቸዉና ቤተሰቦቻቸዉ ጋ እጅግ የተሳሰሩ ሰዎች ናቸዉ።»

የቬልት ሁንገር ሂልፈ ፕሬዝደንት ስደተኞቹ የሚገኙበትን ሁኔታ ለመመልከት ወደስፍራዉ በአካል በመጓዝ ጊዜ ወስደዉ ተመልክተዋል። እንደአዎንታዊ ነገር የተመለከቱት ከምንም በላይ ቱርካዉያን የእነሱን ድጋፍና ከተለላ የሚፈልጉትን ስደተኞች ተቀብለዉ ለማስተናገድ ያሳዩትን ቀና ትብብር ነዉ። ምንም እንኳን የቱርክ መንግሥት ድጋፍ ከፍተኛ ቢሆንም 15 በመቶ የሚሆኑት ተሰዳጆች አሁንም በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ መቆየት ይኖርባቸዋል። ምንም እንኳን ቱርክ የኤኮኖሚ ጥንካሬዋ ከዜጎቿ አልፎ ለስደተኞቹ እጇን መዘርጋት የሚያስችላት ቢሆንም ያልተጠበቀና ያልታሰበ ወጪ እንደመሆኑ ዓለም ዓቀፍ ድጋፍ የግድ እንደሚያስፈልጋት የቬልት ሁንገር ሂልፈ ፕሬዝደንት ዲክማን መጠቆማቸዉ አልቀረም። ባለፈዉ ዓመት ድርጅታቸዉ ስደተኞቹን ለመርዳት ለሚንቀሳቀሱ ፕሮጀክቶች የ19 ሚሊዮን ዮሮ ድጋፍ አድርጓል።

ሶርያ ዉስጥ የፖለቲካ አለመግባባት ያስከተለዉ የእርስ በርስ ጦርነትና ግጭት በአካባቢዉ ሰብዓዊ ቀዉስ ማስከተሉን ያመለከቱት ዲክማን መዘዙም በቀላሉ የሚለቅ እንደማይሆን ነዉ የሚናገሩት። መፍትሄዉ በቀላሉ የሚገኝ ስለማይስልም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተጠናክረዉ በአካባቢዉ ለሚያስፈልጉ የእርዳታ ተግባራት ፈጥነዉ መድረስ እንደሚኖርባቸዉም ያምናሉ። ሶርያ ዉስጥ አሁን የሚታየዉን ሁኔታ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በኋላ ጀርመን ዉስጥ ከነበረዉ ጋ መመሳሰሉን በማመልከትም ሌሎች ዓለም አቀፍ የእርዳታ ሠራተኞች አስቸጋሪ በሆነዉ በዚህ አካባቢ፤ ድርጅታቸዉ በስፍራዉ ከሚገኙ ኃይሎች ጋ ተባብሮ ለተቸገሩ ወገኖች እየደረሰ መሆኑንም ጨምረዉ ገልጸዋል።

Deutschland Welthungerhilfe Bärbel Dieckmann

ባርቤል ዲክማን የቬልት ሁንገር ሂልፈ ፕሬዝደንት

ድርጅት ባለፈዉ ዓመት ቱርክ ዉስጥ የሚገኙ ሶርያዉያንን መርዳትና፤ በሰሜን ኢራቅና ጦርነት በሚያምሳት ሶርያ ዉስጥ ለችግር የተጋለጡትን በመርዳት ተግባር ተጠምዶ እንደከረመ ነዉ በዓመታዊዉ ዘገባዉ ያመለከተዉ። በተፈጥሮ አደጋ በአየር ንብረት መለዋወጥ በድርቅና ለሚጎዱና ኋላ ቀር አካባቢዎች የእርዳታ ተግባራትን የሚያከናዉነዉ ይህ ድርጅት የቬልት ሁንገር ሂልፈ ዋና ጸሐፊ እንደሚሉት በቀዉስ የተጎዱ አካባቢዎች የመርዳቱ እንቅስቃሴ ባለፈዉ ዓመት ዋነኛ ተግባር ሆኖ ከርሟል። የረዥም ጊዜ ፕሮዤዎች በአንድ በኩል እንዳሉ ሆነዉ ከተሠራዉ 40 በመቶዉ ሥራ መልሶ መገንባት ላይ ያተኮረ ነበር። ለዚህም አሁን ድርጅቱ ለሚከሰት ቀዉስ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ መርሃግብርም ዘርግቷል። በዲሱ ስልቱ አማካኝነትም ለመጀመሪያ ጊዜ በኔፓል የመሬት መንቀጥቀጥ ለተጎዱ ወገኖች አፋጣኝ ርዳታ መለስጠት ችሏል። የመሬት መንቀጥቀጡ ዓርብ ቀን ነበር የተከሰተዉ፤ ቬልት ሁንገር ሂልፈ ሰኞ ዕለት በስፍራዉ በመገኘት የአስቸኳይ ጊዜ የእርዳታ ዕቅዱን ቀርጾ ተግባራዊ አድርጓል።

ቬልት ሁንገር ሂልፈ ያለፈዉን ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በዳሰሰዉ ዘገባዉ ምንም እንኳን በወቅቱ ከፍተኛ ርዳታ የሚያስፈልጋቸዉን አካባቢዎች ችግር ቢያስቀድምም፤ ከነበሩበት አስከፊ ይዞታ እየወጡ አዎንታዊ ገፅታቸዉ መታየት የጀመሩ አካባቢዎች መኖራቸዉንም ሳያመላክት ዘገባዉን አላጠናቀቀም። የድርጅቱ ፕሬዝደንት እንደገለፁትም በተለይ በላቲን አሜሪካ የሚገኙ ሃገራት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከነበሩበት አሉታዊ ይዞታ ተላቀዋል። ማሌዢያ፣ ሲሪ ላንካ እና ቬየትናምም ታላቅ የልማት ርምጃ አሳይተዋል። በአፍሪቃ አህጉርም የተሻለ መረጋጋት በሚታይባቸዉ ሃገራት በልማቱም መሻሻሎች መኖራቸዉ ነዉ የተጠቀሰዉ። ሴራሊዮንና ላይቤሪያ የኤቦላ ወረርሽኝ ባያዳክማቸዉ ኖሮ የመሻሻል ርምጃዎችን እያደረጉ እንደነበር የጠቀሱት የቬልት ሁንገር ሂልፈ ፕሬዝደንት ዲክማን፤ በአዎንታዊ መሻሻሎቻቸዉ ማሊ፣ ቡሪኪናፋሶ፣ ሩዋንዳ፣ ማላዊና ኢትዮጵያን በምሳሌነት አንስተዋል።

UNICEF Jahresbericht zur Lage von Kindern in Konfliktgebieten

ድህነትና ሕፃናት

«ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሀገር ባትሆንም ከፖለቲካ አኳያ ያልተረጋጋች የምትባል ሀገር አይደለችም። በነገራችን ላይ እዚህ ጋ መነሳት ያለበት ሴራሊዮን እና ላይቤርያ እጅግ አሰቃቂ የእርስበርስ ጦርነት ካሳለፉ በኋላ በጥሩ ጎዳና ላይ የነበሩ ሃገራት ናቸዉ፤ ከሁለት ዓመት በፊት ሴራሊዮንን ጎብኝቻለሁ። ከእርስበርሱ ጦርነት ያገገመችበት ጠባሳ ቢታይም ወደአንድ ሀገርነት የሚያሸጋግራትን የተሻለ መንገድ ለመሄድ እየሞከረች ነዉ፤ ላይቤሪያም እንዲሁ፤ እነዚህ ሃገራት ናቸዉ በኤቦላም በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድተዉ ወደኋላ የተጎተቱት።»

ጽሕፈት ቤቱ እዚህ ቦን ከተማ የሚገኘዉ ቬልት ሁንገር ሂልፈ ከተቋቋመበት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 1962ዓ,ም አንስቶ ችግር በጠናባቸዉ አካባቢዎች ረሃብና ድህነትን ለመዋጋት የሚንቀሳቀስ ድርጅት መሆኑን በድረገጹ ላይ በግንባር ቀደምትነት ያስነብባል። በ70 ሃገራት ዉስጥ ከ7,733 የሚበልጡ ዓለም አቀፍ ፕሮዤዎችን በመደገፍም እንቀሳቀሳል። ፕሮዤዎቹም በተፈጥሮ ቁጣም ሆነ በግጭት ጦርነቶች በሚከሰቱ ጥፋቶች የተጎዱትን ከመርዳት አንስቶ፤ መልሶ የማቋቋምና ረዥም ዓመት ከድህነትና ረሃብ ነፃ የሆነች ዓለምን ለመገንባት ለሚደረገዉ ጥረትም 2,84 ሚሊዮን ዩሮ መድቦ ይሠራል። በዓመታዊዉ ዘገባ ፕሬዝደንቷ ኢትዮጵያ ዉስጥ አሉ ስላሏቸዉ መሻሻሎች ዘርዘር ያለ ማብራሪያ እንዲሰጡን የድርጅቱን ቃል አቀባይ ዚሞነ ፖትን ጠይቀናቸዉ ነበር።

«ቬልት ሁንገር ሂልፈ ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለፉት አስር ዓመታት በተለያዩ መስኮች መሻሻሎች በግልፅ መኖራቸዉን አስተዉሏል። ከእነዚህ ዘርፎች አንዱ የኤኮኖሚዉ ሁኔታ ነዉ፤ ይህም ከአፍሪቃ በሰባተኛ ደረጃ የሚገኝ ነዉ። የኤኮኖሚዉ እድገት ሰፋ ያለዉን የሕብረተሰብ ክፍል የሚያዳርስ ከሆነ ከደግሞ በእግጥም አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ባለፈዉ የተመድ ዓመታዊ ዘገባ ላይ የሕጻናት ሞት ኢትዮጵያ ዉስጥ በተጨባጭ መቀነስና መሻሻሉ ታይቷል። የአምዓቱን የልማት ግብ ብንመለከትም የድህነት ይዞታዉ እየቀነሰ መሄዱም አንዱ ነዉ። በ1990ዎቹ ግማኅ በግማሽ ሕዝቡ በድህነት ይኖር የነበረዉ አሁን ይህ ቁጥር ቀንሶ ታይቷል። ይህ ማለትም ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ መሻሻል መኖሩን ያመለክታል።»

እንደቬልት ሁንገር ሂልፈ ቃል አቀባይ ከሆነ የድህነቱ ይዞታ ከዕለት ወደዕለት መሻሻል ታይቶበታል። ዚሞነ ፖት ሀገሪቱም ድህነትና ረሀብን ለመዋጋት የምታደርገዉ ጥረት ዉጤት እያሳየ ነዉ ባይ ናቸዉ።

«ኢትዮጵያ ዉስጥ የድህነቱ ሁኔታ በተጨባጭ እየቀነሰ ነዉ። አሁን 30 በመቶ የሚሆነዉ ሕዝብ ነዉ በድህነት ዉስጥ የሚገኘዉ። ይህም ቀደም ብዬ እንዳልኩት በ1990ዎቹ ከነበረዉ ጋ ሲነፃፀር ማለት ነዉ። ከዚህ ጋ ተያይዞም ረሀብ ቀንሷል። ድህነትና ረሀብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፆች ናቸዉ። እርግጥ ነዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በድህነት ደረጃ ያለዉ አስቸጋሪ ጉዳይ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጡ ነዉ።»

በማያያዝም ቀደም ባሉት ጊዜያት ቬልት ሁንገር ሂልፈ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ በስፋት መሥራቱን ቃል አቀባይዋ ጨምረዉ ገልጸዋል።

«ለበርካታ ዓመታት የተጠናከረ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጫ ፕሮጀክት ነበረን። አሁን እዚያ የምናከናዉነዉ ተግባር በመጠኑ ተለዉጧል። ዉኃና የመጸዳጃ ሁኔታዎችን በሚመለከት ዘርፍ ላይ አተኩረን እየሠራን ነዉ። ይህም ንፁህ የመጠጥ ዉኃ፤ የተሻለ የንፅህና መጠበቂያ ስልት የመሳሰሉት ላይ ማለት ነዉ። ሙሉ በሙሉ በገጠር አካባቢ ነዉ የምንንቀሳቀሰዉ።»

ንፁህ የመጠጥ ዉኃ ለማቅረብ በሚንቀሳቀሰዉ ፕሮጀክትም 150,000 ሰዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መታቀዱን የድርጅቱ ድረገጽ ላይ የሰፈሩ መረጃዎች ያስረዳሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic