የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ግልፅነት | ኢትዮጵያ | DW | 20.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ግልፅነት

ጽሕፈት ቤቱ ኦስሎ ኖርዌይ የሚገኘዉ የሃገራት የተፈጥሮ ሃብት አስተዳደር ይዞታ ግልፅነት ሊኖረዉ ይገባል የሚለዉ በእንግሊዝኛ ምህፃሩ EITI የተሰኘዉ ስብስብ ኢትዮጵያ ለአባልነት ያቀረበችዉን ማመልከቻ ተቀበለ። በአንፃሩ መንግስት የሲቪል ማኅበራትን እንቅስቃሴ ማረጋገጥ እንደሚኖርበት የEITI ቦርድ በአፅናኦት አሳስቧል።

በአንድ ሀገር የሚገኙ እንደነዳጅ ዘይት፣ ጋዝ፣ ብረታብረትና ማዕድናት ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶች የዜጎች ሃብት ናቸዉ ይላል በእንግሊዝኛ ምህፃሩ EITI የተሰኘዉ መንግስታት፣ ካምፓኒዎች እና ሲቪክ ማኅበራት በጋራ ያካተተዉ ስብስብ። እነዚህን የተፈጥሮ ሃብቶች ከያሉበት ማዉጣቱ ለየሃገራቱ የኢኮኖሚ እድገትንና ማኅበራዊ ልማትን ሊያስከትል ይችላል። ሆኖም የዚህ ሃብት አስተዳደር ግልፅነትን ተላብሶ በአግባቡ ካልተያዘ ወደሙስና ሊያመራ ብሎም የግጭቶች መንስኤ ሊሆን እንደሚችል EITI ያመለክታል። ከተቋቋመ ከ10 ዓመታት በላይ ያስቆጠረዉና 20 የቦርድ አባላት ያሉት ይህ ስብስብ አመሠራረቱ የየሃገራቱ የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ ለብዙሃን ዜጎች ጥቅም ሳይሆን እንደዉም ለብዙዎች ድህነት ጉስቁልናና የጤና ጠንቅ የሆኑበትን ሁኔታ ያመላከቱ ጥናቶችን መሠረት በማድረግ ነዉ። ከዚህ በመነሳትም ያላቸዉን የተለያዩ ማዕድኖችና ሃብቶች ምን ሃይል በግልፅነትና ብዙሃኑን በሚጠቅም መንገድ ሥራ ላይ እያዋሉት ነዉ የሚለዉን የሚመረምርበትን መመሪያ አረቀቀ።

ከ25 በላይ ሃገራትንም የEITIን መስፈርቶች ያሟሉ በማለት እስካሁን በአባልነት ይዞም ላለፉት ዓመታት ከየሃብታቸዉ ያገኙትን ጥቅም በደረሰዉ መረጃ መሰረት በድረገጹ ላይ አስፍሯል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ደግሞ 17 ሃገራት ደግሞ መስፈርት ያላሟሉ ከተባሉት ተርታ ተሰልፈዋል። ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፣ የመን፣ ማዳጋስካርና ማዕከላዊት አፍሪቃ ሪፑብሊክ ለጊዜዉ የታገዱ መሆናቸዉ ተመልክቷል። የመን ሀገር ዉስጥ የአረቡን ዓለም አብዮት ተከትሎ በተከሰተዉ አለመረጋጋት ሳቢያ ከ2011 አንስቶ እስከአሁን የየዓመቱን የነዳጅ ዘይትና ጋዝ ሽያጭ ገቢ ባለማቅረቧ ለጊዜዉ መታገዷ ተገልጿል።

በሃገራት የማዕድና የተፈጥሮ ሃብት አስተዳደር ግልፅነት ኅብረተሰቡ ማለትም ዜጎች የልማት ተካፋይ የሚሆኑበት መንገድ ያመቻቻል በሚል የሚንቀሳቀሰዉ ስብስብ ትናንት ኦስሎ ላይ ባካሄደዉ 25ኛ ጉባኤዉ ኢትዮጵያ ለድርጅቱ ያቀረበችዉን በአባልነት የመታቀፍ ማመልከቻ ተቀብሏል።

የEITI የቦርድ አባላት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ባካሄዱት ዉይይት በሀገሪቱ የሲቪል ማኅበራት እንቅስቃሴ እንዲረጋገጥ እና የስብስቡ መመሪያ ጋ እንዲጣጣም አፅንኦት መስጠታቸዉ ተዘግቧል። ኢትዮጵያ ከሰሃራ በስተደቡብ በፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ ሃገራት አንዷ መሆኗ ያመለከተዉ ዘገባ፤ የተቃዉሞ ፖለቲከኞች እና የመብት ተሟጋቾች መንግስት በዜጎች ላይ ይዞታዉን እንደሚያጠብቅና የፖለቲካ እስረኞችን ቁም ስቅል እንደሚያሳይ ያመለክታሉ። መንግስት ይህን አጥብቆ ያስተባብላል። ዓለም ኦቀፍ የመብት ተሟጋች የሆነዉ ሂዉመን ራይትስ ዎች EITI የኢትዮጵያን ማመልከቻ መቀበሉን አጥብቆ ተዋዉሟል። የድርጅቱ ከፍተኛ ተመራማሪ ሊዛ ሚሶል፤ EITI በሀገር ዉስጥ የተሻለ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለዉ መንግስት እንዲኖር የሚሟገቱ ዜጎችን ያስራል እንዲሰደዱም ያደርጋል ያሉትን የኢትዮጵያ መንግስት ተገቢ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ ሳይገፋፋ ማመልከቻዉን መቀበሉን ተችቷል። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2010ዓ,ም የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበዉን ተመሳሳይ ማመልከቻ ዉድቅ ተደርጎባታል።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic