የተፈናቃዮች ይዞታ እና አፋጣኙ መፍትሄ  | ኢትዮጵያ | DW | 19.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የተፈናቃዮች ይዞታ እና አፋጣኙ መፍትሄ 

ተፈናቃዮች ከሚሰጧቸው ልዩ ልዩ እርዳታዎች ጎን ለጎን ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸው ቢነገርም በአመዛኙ አዝጋሚ ሆኖ ቆይቷል። በአንዳንድ አካባቢዎች ከተፈናቀሉ ከአንድ ዓመት በላይ በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ዜጎች መኖራቸው ይነገራል።ለአብዛኛዎቹ መፍትሄ ሳይገኝ በተለያዩ አካባቢዎች አዳዲስ መፈናቀሎች መድረሳቸው አልቆመም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 30:29

የተፈናቃዮች ይዞታ

ዞሮ መግቢያ ቤታቸውን ብቻ ሳይሆን ለዓመታት ያፈሩትን ሌሎች ንብረታቸውንም ትተው ነፍሳቸውን ለማትረፍ ቀዬአቸውን ለቀው የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት ይገኛሉ።ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ እና ከዚያም በፊት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች ሰበብ  ይህ እጣ የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን በርካቶች ናቸው። ሁለት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በቅርቡ ባቀረቡት ዘገባ መሠረት  በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓም በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች በተቀሰቀሱ ግጭቶች የተፈናቀሉት ቁጥር 2.9 ሚሊዮን ደርሷል። በዚሁ ዘገባ መሠረት በኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በዚሁ ዓመት ተመሳሳይ ችግር ከተፈጠረባቸው ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛው ነው ተብሏል። ተፈናቃዮች በተጠለሉባቸው አካባቢዎች ከሚሰጧቸው ልዩ ልዩ እርዳታዎች ጎን ለጎን ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸው ቢነገርም በአመዛኙ አዝጋሚ ሆኖ ቆይቷል። በአንዳንድ አካባቢዎች ከተፈናቀሉ ከአንድ ዓመት በላይ በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ዜጎች መኖራቸው ይነገራል። ከተፈናቃዮቹ አብዛኛዎቹ ወደ ቀዬቸው አልተመለሱም፣ ወደ አካባቢያቸው የተመለሱ እና በመመለስ ላይ ያሉ እንዳሉ ቢገለጽም ከቀሩት ጋር ሲነጻጸር ቁጥራቸው አነስተኛ መሆኑ ነው የሚነገረው። ለአብዛኛዎቹ መፍትሄ ሳይገኝ በተለያዩ አካባቢዎች አዳዲስ መፈናቀሎች መድረሳቸው አልቆመም። በየመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች እርዳታ የሚያቀርቡ እና በሙያቸው የበጎ አድራጎት አገልግሎቶችን የሰጡ ባለሞያዎች እንደሚሉት በተለይ ህጻናት ሴቶች እና አረጋውያን ከደረሰባቸው እንግልት በተጨማሪ ለተለያዩ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳቶች ተዳርገዋል። የተፈናቃዮች ይዞታ እና አፋጣኙ መፍትሄ  የዛሬ እንወያይ ትኩረት ነው። በዚህ ውይይት ላይ የሚካፈሉ አራት እንግዶችን ጋብዘናል። እነርሱም አቶ ደበበ ዘውዴ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የኮምኒኬሽን ጉዳዮች እና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ  ፣አቶ መሱድ ገበየሁ የኢትዮጵያ የመብት ድርጅቶች ህብረት ሃላፊ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ፣አቶ ሮባ በንቲ በዓለም አቀፉ የህጻናት አድን ድርጅት የአስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ ከፍተኛ አስተባባሪ እንዲሁም አቶ ሙሉጌታ አበበ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት በምህጻሩ መኢአድ  ምክትል ፕሬዝዳንት ናቸው። ከታች የሚገነውን የድምጽ ማዕቀፍ በመጫን ሙሉውን ውይይት መከታተል ይችላሉ።

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic