የተፈናቃዮች አቤቱታ በአማራ ክልል | ኢትዮጵያ | DW | 18.01.2023
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የተፈናቃዮች አቤቱታ በአማራ ክልል

በአማራ ክልል ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አንዳንዶቹ ርዳታ ካገኙ ረጂም ጊዜ እንደሆናቸው ተናገሩ። ሌሎች ደግሞ በቂ የምግብ ድጋፍ እንደተደረገላቸው አመልክተዋል። ከትግራይ የተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቅለው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቀበሮ ሜዳ የሚገኙ ተፈናቃዮች አሁንም «ተረስተናል» እያሉ ነው።

ድጋፍ ያልደረሳቸውም የተሰጣቸውም አሉ ተብሏል

በአማራ ክልል ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አንዳንዶቹ ርዳታ ካገኙ ረጂም ጊዜ እንደሆናቸው ተናገሩ። ሌሎች ደግሞ በቂ የምግብ ድጋፍ እንደተደረገላቸው አመልክተዋል። ከትግራይ የተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቅለው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቀበሮ ሜዳ የሚገኙ ተፈናቃዮች አሁንም «ተረስተናል» እያሉ ነው። ወደ ቀያቸው ለመመለስ የሚፈልጉ ተፈናቃዮች ቀርቦ ያወያያቸው አካል እንደሌለም ተናግረዋል። የአማራ ክልል መንግስት በበኩሉ ለተረጂዎች በተቻለ መጠን ርዳታ ለማድረስ እየሠራ እንደሆነ ጠቁሟል። ተመላሾችን በተመለከተ ግን የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊነት ተከትሎ የትግራይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ ብሏል።

የሰሜኑን ጦርነትና በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ዞኖች የከሰተውን ተከታታይ አለመረጋጋትና ግጭት ተከትሎ በርካታ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለእርዳታ ተዳርገዋል። ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ ከትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በማዕካላዊ ጎንደር ዞን ቀበሮሜዳ የተፈናቃዮች መጠለያ ከሚገኙት መካከል አቶ ካሳሁን ተስፋዬ “እንዴት ናችሁ?” ያለን የለም ይላሉ፡፡  “እንዴት ናችሁ የሚለን ሰው የለም ከንቱ፣ ከንቱ ነው ያለነው፣ ያለው ችግር ይህ ነው፣ መድኃኒት አይቀርብም፣ ህክምናውም የለም ደካማ ነው ወደ ሌላ የህክምና ቦታ ነው የሚልኩህ፣ እዛም የሚያስተናግድህ የለም፡” ብለዋል፡፡ ሌላዋ ከሽሬ እንደስላሴ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያው ከሚገኙት መካከል ወ/ሮ የሺእመቤት በላቸውም እርዳታ ካገኙ ሁለት ወራት አልፈዋል፡፡ 

Äthiopien | Büro für Katastrophenschutz und Ernährungssicherheit in Amhara

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽ/ቤት

ምዕራብ ጎጃም ዞንና ሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮችም በቂ ድጋፍ አላገኘንም የሚል ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ከትግራይ የተፈናቀሉ አንዳንዶቹ ወደቀያቸው ለመመለስ ፍላጎት ያላቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ መመለሱን አይፈልጉትም፣ ወደነበሩበት የትግራይ አካባቢ ላለመመለስ ከሚፈልጉት ተፈናቃዮች መካከል አንዱ ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ “ማንም የሚመለስ የለም፣ መጀመሪያ ገና ሳንመጣ ነው፣ ሀብት ንብረታችን የተቃጠለው ማለት ነው፣ ምናለ ወደዚያ የምትሄድበት ምንም የለህም፣ እንዴት ብለህ ነው የምትመለሰው፣ ሀብትህ የለ፣ ቤትህ የለ፣መኪና የነበራቸው መኪናቸውን አጥተው ነው የመጡት፣ስለዚህ የሚመለስ አካል የለም፡፡” 

ቀደም ሲል በውትድርና ከመሀል አገር ሄደው እንደነበር የሚናገሩት አቶ ካሳሁን፣ ከውትድርና ከወጡ በኋላ ባድሜ በተባለ የትግራይ አካባቢ ሚስት አግብተው 5 ልጆች ማፍራታቸውን ይናገራሉ፣ የ2013ቱ ጦርነት በትግራይ ሲጀመር ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን ትተው ተፈናቅለዋል፣ ወደ አካባቢያቸው ለመመመለስ ቢፈልጉም ያወያያቸው አካል እንደሌሌ ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል፡፡ “የመንግስት አካል መጥቶ ሲያወያይህ ነው እኮ ሁሉን ነገር መነጋገር የምንችለው፣ ግን እድሜልካችን ያፈራነው ንብረት እዛ ነው፣ እኔ ለምሳሌ 5 ልጆች ከዚያ አሉ መንገዱ አልተከፈተልንም ሊያገናኘን እንኳ አልቻለም (መንግስት)፣ ስትወያይ፣ መንግስት ኃላፊነት ሲወስድ፣ እውቅና ሲሰጥ፣ እኮ ነው፣ ልትመለስ ነው ወይስ አትመለስም የሚለው መልስ የሚያገኘው፣ ዋስትና ከገባልን ንብረታችን፣ ቤታችን እኮ እዛ ነው፡፡” 

ከዋግሕምራ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎች እሮሮ

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በደብረብርሀን የመጠለያ ጣቢያች ጉብኝት ካደረጉ በኋላ በቂ የሚባል ድጋፍ እያገኙ መሆናቸውን በሰሜን ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮች ገልጠዋል፡፡ “ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በቅርቡ እዚህ መጥተው አናግረናቸው ነበር፣ እግዚአብሔር ይመስገን አሁን እየመጣልነ ነው (እርዳታ)፣ ለቻይና ካምፕ ብቻ ለ2000 ሰዎች 50 ኪሊ ግራም ዱቄት፣ 5 ሊትር ዘይት፣ 15 ኪሊ ስንዴ ለእያንዳንዱ ተፈናቃይ ተሰጥቷል፣ አሁን ላይ ተስፋ አለን ሰው ከሞት የሚድንበትን አጋጣሚ እያገኘን ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም በሌሎች በዞኑ በሚገኙ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ተፈናቃዮችም እርዳታ እየደረሰ እንደሆነ ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል፡፡

Äthiopien | Eyasu Mesfin

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን

 

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን የምግብ አቅርቦትን በተመለከተ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 
“የምግብ ድጋፉን በተመለከተ የተቆራረጠ ነው፣ ጊዜውን ጠብቆ (ከማዕከል) እመጣ አይደለም፣ መሰረታዊ ምክንያቶች ደግሞ ከፌደራል ድጋፉን የመላክ ውስንነት አለ፣ የትራንስፖርትና የፀጥታ ችግሮችም አሉ፣ ይህ ደግሞ ለእናቶች፣ ህፃናትና አረጋውያንን ኑሯቸውን ከባድ ደርገዋል፣ ወቅቱን የጠበቀ ድጋፍ ማቅረብ ስፈልጋል፣ በክልሉ መንግስት የተገዛ ድጋፍ አለ፣ ይህን የድጋፍ እህል በራሳችን ትራንስፖርት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች እያቀረብን ነው፣ ችግሩን እያስታገስን እንገኛለን፡” ነው ያሉት፡፡ ከትግራይ የተፈናቀሉ ወገኖችን ባለስልጣናት አላወያዩንም የሚለውን አቤቱታ በተመለከተ ግን ሀሰት ነው፣ የሰላም ሂደቱን ተከትሎ መመለስ የሚፈልጉት እንዲመለሱ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ 

“ብዙዎች ከትግራይ የተፈናቀሉ የወታደር ሚስቶችና ሌሎችም ስለሆኑ ያነጋገረን የለም የሚለው መሰረተ ቢስ አሉባልታ ነው፣ ገና የሰላም ስምምነቱ ወደ ትግበራ እየገባ ስለሆነ፣ እነሱን ሰላማዊ ወደሆነ የመልሶ ግንባታ ለማድረግ የተለየና የተረጋገጠ መያዝ አለብህ፣ እሱን እጠበቅን ነው፣ የታወቀ ነገር ሲገኝ እነሱንም ወደ ቤተሰቦቻቸው በማገናኘት ችግር ፈቺ የሆነ የመልሶ ማቋቋም ተግባር ከናወናል፡፡” 

በአማራ ክልል ከነበሩ ተፈናቃዮች መካከል ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ከ260ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው የተመለሱ ሲሆን አሁንም 650ሺህ በዋናነት ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖች በክልሉ እንደሚገኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች