የተፈናቃዮች መብት እዲከበር ኢሰመኮ ጠየቀ
ረቡዕ፣ ጥቅምት 16 2015
የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን ከየቀያቸዉ የሚያፈናቀሉ እርምጃዎችንና ችግሮችን ለመከላከል እንዲጥር፣ የተፈናቃዮችን መብት እንዲያስጠብቅና ለየችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልግ የሐገሪቱ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ።ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በየአካባቢዉ የሚደረግ ግጭት፣ድርቅና የረሐብ ስጋት በብዙ ሚሊዮንየሚቆጠር ሕዝብ ከየቀየዉ አፈናቅሏል።ኢሰመኮ ከሐቻምና ሰኔ እስከ አምና ሰኔ በነበረዉ አንድ ዓመት ዉስጥ በ6 ክልልሎችና በአንድ የከተማ አስተዳደር የተጠለሉ ተፈናቃዮችን ሁኔታ አጥንቶ ባወጣዉ ዘገባ እንደሚለዉ ኢትዮጵያ የተፈናቃዮችን የሚመለከት ግልፅ ሕግ፣ ተቋዋም፣የተፈናቃዮችን ዝርዝር መረጃ የሚጠናቀርበት ሥርዓት የላትም።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከሰኔ 2013 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2014 ዓ. ም ባለው አንድ ዓመት በ 6 ክልሎች እና በአንድ ከተማ አስተዳድር ውስጥ የሚገኙ 1.5 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ፣ 52 መጠለያ ጣቢያዎችን እና ተቀባይ ማህበረሰቦች የሚገኙበትን ሁኔታ ክትትል እና ምርመራ ያደረገበትን ባለ 37 ገጽ ዘገባ ይፋ ሲያደርግ ነው ጥያቄው የቀረበው።
በሰነዱ ከሰፈረት ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ተፈናቃዮችን የሚመለከት ግልጽ የሕግ እና ተቋማዊ ማዕቀፍ አለመኖር፣ ተፈናቃዮች በዝርዝር የሚመዘገቡብት አሰራር አለመኖር፣ የተፈናቃዮች የመንቀሳቀስ መብቶች መገደብ ብሎም የፀጥታ ፣ የደኅንነት እና ፍትሕ የማግኘት መብቶች አለመከበር ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ተቋማቸው ያወጣው ዘገባ ላይ "መንግሥት መፈናቀልን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በምርመራው የቀረቡትን ምክረ ሀሳቦች እንዲፈጽም እና እንዲያስፈጽም" ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማሳሰቢያ
ተፈናቃዮች በቂ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ አለመደረጉን ለ ዶቼ ቬለ (DW) የተናገሩት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ እነዚህን የተወሳሰቡ ችግሮች የሚፈታ ተቋም አስፈላጉ መሆኑን ገልፀዋል።
ሪፖርቱ ይፋ ያደረገው መረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ከ 4.5 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ያሳያል። "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ ኃይል በተሞላበት ግጭት ምክንያት የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ መጥቷል" ብለዋል ሪፖርቱ።
በተለይ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለመሰደድ መገደዳቸውንም አብራርተዋል።
የአንድ ዓመት የተፈናቃዮች ሁኔታን የዳሰሰው ሪፖርቱ "የተፈናቃዮች የተሰባጠረ ምዝገባ አለመኖሩ ፍላጎትን ማእከል ያደረገ ድጋፍ እንዳይሰጥ አድርጓል" ይሏል።
የመሰረታዊ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች አቅርቦት እጥረት ፣ የመጠለያ ፣ የውኃ፣ የንጽሕና እንዲሁም የህክምና አገልግሎት ተደራሽ አለመሆን መሰረታዊ ችግሮች መሆናቸው ተዘርዝሯል።
ሪፖርቱ ቀያቸውን ትተው ከሚፈናቀሉ ሰዎች መካከል ግማሽ የሚሆኑት ሕፃናት እንደሆኑ ዓለም አቀፍ መረጃዎች ያሳያሉ ሲል ጠቅሷል። ይህም በመሆኑ ሕፃናትና ሴቶች ለአልሚ ምግብ እጦት እና ከትምህርት ገበታ ለመፈናቀል ብሎም ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ፣ ያለ እድሜ ጋብቻ ፣ ለልመና ፣ ለጉልበት ብዝበዛ እንዲሁም ለወሲብ ንግድ እንዲጋለጡ ማድረገን አትቷል።
መንግሥት ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው ለመመለስ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ለማስፈር የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የጠቀሰው ኢሰመኮ የተፈናቃዮች ፍላጎት ፣ ከመፈናቀላቸው በፊት የነበራቸው የአኗኗት ዘይቤ ፣ በሚኖሩበት አካባቢ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ግምት ውስጥ ባለመግባቱ በዘላቂነት ራሳቸውን ችለው ለመቋቋም ይቸገራሉ ብሏል። "ለግጭት ምክንያት በሆነው ጉዳይ የተሟላ እና አሳታፊ የሰላምና እርቅ ሥርዓት ሳይፈፀም ፣ ፀጥታና ደህንነታቸው ባልተረጋገጠባቸው አካባቢዎች እንዲሁም ሰዎች መፈናቀል ባላቆሙበት ሁኔታ ተፈናቃዮችን ያለፈቃዳቸው እንዲመለሱ ማድረግ ለዳግም መፈናቀል የሚዳርግ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም" ብሏል ሪፖርቱ። የስደተኛ ተፈናቃይ ቁጥር ማየል
ኢሰመኮ ባወጣው ሪፖርት ካስቀመጣቸው ምክረ ሀሳቦች መካከል ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚደረገውን የመብቶች ጥበቃ በኃላፊነት ወስዶ የሚተገብር ተቋማዊ አደረጃጀት በሕግ እንዲደነገግ የሚለው ይገኝበታል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ