የተፈቱት ጋዜጠኞችና የድንበር የለሽ ጋዜጠኞች ቡድን አስተያየት | ኢትዮጵያ | DW | 21.08.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የተፈቱት ጋዜጠኞችና የድንበር የለሽ ጋዜጠኞች ቡድን አስተያየት

ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ጋዜጠኞቹ የተፈቱበት መንገድ ቅር እንዳሰኘው ጠቅሷል

default

ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኃላ ከተከሰተው ውዝግብ ጋር ተያይዞ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ የታሰሩት የአራት ጋዜጠኞች መፈታት እንዳስደሰታቸው ሁለት የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች አስታወቁ ። በእንግሊዘኛው ምህፃር አር ኤስ ኤፍ በመባል የሚጠራውና ፅህፈት ቤቱ ፓሪስ ፈረንሳይ የሚገኘው ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተመልካች ድርጅት እና መቀመጫውን ኒውዮርክ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተመልካቹ ቡድን ሲፒጄ የጋዜጠኞቹን መለቀቅ በደስታ መቀበላቸውን ትናንት ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል ። ሆኖም ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ጋዜጠኞቹ የተፈቱበት መንገድ ቅር እንዳሰኘው ሳይጠቅስ አላለፈም ። ሲፒጄም በበኩሉ መንግስት በዘጠኝ ጋዜጠኞች ላይ እንደገና ክስ ለመመስረት የሚያደርገው ሙከራ እንደሚያሳስበው አንስቷል ። የጋዜጠኞቹን መፈታት ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን እንዴት ያየዋል ?
ምርጫ ዘጠና ሰባትን ተከትሎ ከተነሳው ውዝግብ ጋር በተያያዘ ባወጡዋቸው ልዩ ልዩ ዘገባዎች ተከሰው ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ የታሰሩትና ባለፈው ቅዳሜ የተለቀቁት ጋዜጠኞች ወሰንሰገድ ገብረኪዳን ፣ ዳዊት ከበደ ፣ ጎሹ ሞገስና ታድዮስ ታንቱ ናቸው ። የነዚህን አራት ጋዜጠኞች መፈታት አስመልክቶ ሁለቱ ግንባር ቀደም የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች አር ኤስ ኤፍ እና ሲ.ፒ.ጄ ባወጡዋቸው መግለጫዎች ጋዜጠኞቹ በመፈታታቸው ደስታቸውን ቢገልፁም ሌሎች ቅር የተሰኙባቸው ጉዳዮች መኖራቸውንም ማንሳታቸው አልቀረም ። ስለሁኔታው ያነጋገርኩዋቸው በድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ውስጥ አጥኚ የሆኑት ቨንሰንት ብሮሴል እንደሚሉት ጋዜጠኞቹ ፍትሀዊ ብያኔ አግኝተው ሳይሆን በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍላጎት መለቀቃቸው ቅር የሚያሰኝ ነው ። ድርጅታቸው ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን የጠበቀው ሌላ ነበር ።
« በመጀመሪያ ደረጃ አብዛኛዎቹ ሰዎች የተያዙት በህዳር ሺህ ዘጥኝ መቶ ዘጠና ስምንት ነው።ብዙዎቹ አሁን ተፈተዋል ። ቅር የሚያሰኘው ሰዎቹ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍላጎት ምክንያት መፈታታቸው ነው ። እኛ ግን የፍትህ ስርዓቱ ተግባሩን ይወጣል ብለን ነበር ተስፋ ያደረግነው ። ለነገሩ ሰዎቹ በሙሉ ወንጀል ተብሎ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ አልነበሩም ። ስለዚህም እንዲለቀቁ በተሰጠው ትዕዛዝ በዕርግጥም ረክተናል ። በሌላ በኩል በተለቀቁበት መንገድ ግን ቅር ተሰኝተናል ።»
እንደ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት አጥኚ ሚስተር ብሮሴል ኢትዮጵያ ውስጥ ተቃዋሚዎችን ደግፈው የሚፅፉ ሚድያዎች ከፍተኛ ጫና ይደረግባቸዋል ። ሆኖም ይላሉ ሚስተር ብሮሴል በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከኤርትራ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ነው ። በኢትዮጵያ የግል መገናኛ ብዙሀን የማደግ ዕድላቸው የሰፋ ነው መሆኑ ሀቅ ነው ። ይሁንና መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት ተቃዋሚዎችን የሚደግፉ የግል መገናኛ ብዙሀን አያያዙ ፍትሀዊ አልነበረም ሲሉ አስረድተዋል መንግስት ከምርጫ ዠጠና ሰባት በኃላ ከተነሳው ውዝግብ ጋር ተያይዞ የታሰሩትን አራት ጋዜጠኞቹ መልቀቁ ቢያስደስትም አሁንም ሌሎች ስምንት ጋዜጠኞች በእስር ላይ መሆናቸው መዘንጋት የለበትም ይላሉ ሚስተር ቨንሶን
«እዚህ ላይ አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ስምንት ጋዜጠኞች ዕስር ላይ እንዳሉ ማስታወስ እፈልጋለሁ ። ከነዚህም አንዱ አዳር ለተባለው ጋዜጣ ነበር የሚሰራው ። ስለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ የፍትህ ስርዓቱ ሂደት መቀጠልና በዕስር ላይ የሚገኙት የተቀሩት ጋዜጠኞች ጉዳይም መታየት አለበት ። አቶ መለስ ዜናዊም የቀድሞዎቹ ጋዜጠኞች ወደ ስራቸው ተመልሰው በነፃነት እንዲሰሩ መፍቀድ አለባቸው። »
በድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ድርጅት ተመራማሪ የሆኑት ሚስትር ብሮሴል እንደሚሉት መንግስት ዕስረኞችን የሚለቀው የተቃዋሚ ደጋፊዎችን ነፃ አድርገናል በማለት ድርጊቱን ለህዝብ ግንኙነት ተግባር ለመጠቀም ነው ። ሆኖም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በሚያገናኘው ምክንያት ሁሉ ለሀገሪቱ የመሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ትኩረት መስጠት ይገባዋል ።
«ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በዚህ ላይ ግልፅ መሆን አለበት ። ይኽውም የፖለቲካና የፕሬስ ነፃነት በሌለበት መልካም አስተዳደር እንደማይኖር ፤ ካለነርሱ ልማት ዕውን ሊሆን እንደማይችል ፤ በተለይ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን መንግስት ጉዳዮች በሚመለከትበት ወቅት እነዚህ ነጥቦች ላይ ማተኮር አለበት ብለን ነው የምናሰበው »