የተጠናከረው የግብፅ ህዝባዊ አመፅ | ዓለም | DW | 31.01.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የተጠናከረው የግብፅ ህዝባዊ አመፅ

ሳምንት ሊደፍን አንድ ቀን የቀረው የግብፅ ህዝባዊ አመፅ ዛሬም እንደቀጠለ ነው ። መንግስት ህዝባዊ ተቃውሞውን ለማገድ የሰዓት እላፊ ቢያውጅም ያካበረው አልተገኘም ። ይልቁንም አመጹ ተባብሶ ወደ አጠቃላይ የስራ ማቆም አድማ መሸጋገር ይዟል ።

default

በህዝባዊ ሰልፎች ስልጣን እንዲለቁ የተጠየቁት የግብጹ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ አዲስ ምክትል ፕሬዝዳንት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሾሙና የካባኒ ሹም ሽር ቢያካሂዱም እርምጃቸው አመጹን ሊያስቆም አልቻለም ። አመፅ እንደ ሰደድ እሳት በተቀጣጠለባት በግብፅ ስርዓተ አልበኝነትም የዚያኑ ያህል እየተስፋፋ ነው ። ምዕራባውያን መንግስታት ሙባረክ ሀገሪቱን ከገባችበት ቀውስ እንዲያወጡ መጠየቃቸውን ቀጥለዋል ። የግብፅ ህዝባዊ ንቅናቄ ባስከተለው አለመረጋጋት መንስኤ በርካታ የውጭ ዜጎች ሀገሪቱን ለቀው በመውጣት ላይ ናቸው ።
Ägypten Proteste

ህዝባዊው ማዕበል

ድህነት ሙስናና እና ስራ አጥነት የወለደው የግብፅ ህዝባዊ ንቅናቄ ተጠናክሮ ቀጥሏል ። የአመፁ ማዕከል መዲናይቱ ካይሮ የሚገኘው የጣህሪር አደባባይ ዛሬም ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ ሥልጣናቸውን ይልቀቁ በሚለው ህዝብ ተጨናንቆ ነው የዋለው ። የፕሬዝዳንት ሙባራክ መንግስት ሰዓት እላፊ ቢያውጅም ህዝቡ እዚሁ አደባባይ ነው ያነጋው ። ከማለዳ አንስቶ ወደ ጣህሪር አደባባይ የሚጎርፈው ህዝብ በፖሊስ ማንነቱ እየተጣራ ነበር የሚገባው ። የህዝባዊው ንቅናቄ ኮሚቴ አባላትም አንድነታችንን ያናጋሉ የሚሏቸው ነጭ ለባሽ ፖሊሶች ሰርገው እንዳይገቡ ፣ በፊናቸው መታወቂያ እያዩ ነበር ። የአሜሪካን የቅርብ ወዳጅ የሆኑት ሙባረክ በዋጋ ግሽበት ተቆጥቶ በአደባባይ ተቃውሞ ሊያወርዳቸው ለተነሳው ህዝባቸው የኢኮኖሚ ተሀድሶ ለማድረግ ቃል ገብተዋል ። የፈየደው ነገር የለም እንጂ ካቢያኔያቸውን ሽረው አዲስ ምክትል ፕሬዝዳንት እና አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትርም ሰይመዋል ። የግብፅ የደህንነት ሚኒስትር ኦማር ሱሌይማንን ነው ሙባረክ ምክትል ፕሬዝዳንት አድርገው የሰየሙት ። በግብፅ የ 30 ዓመት ታሪክ የመጀመሪያው ተሿሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሱሌይማን የፕሬዝዳንት ሙባራክ ፍፁም ታማኝና በእስራኤልና በአሜሪካን ተቀባይነትን ያገኙ የሙባረክ የመካከለኛው ምስራቅ ሚስጥራዊ ዲፕሎማት ናቸው ። አዲስ ምክትል ፕሬዝዳንት መሾማቸውም ሆነ አዲስ ካቢኔ መመስረታቸው አመፁን ለማስቆም የሚፈይደው ነገር እንደማይኖር ህዝቡም ሆነ ተቃዋሚዎች መናገራቸው አልቀረም ። ይህን ከሚሉት አንዱ በህዝባዊ ንቅናቄው ማግስት ግብፅ የገቡት በማግስቱ ለቁም እስር የተፈረደባቸው ተቃዋሚው መሐመድ ኤል ባራዳይ ናቸው ።

Mohamed El Baradei Mohamed ElBaradei bei Demonstration Protest gegen Mubarak Regime Regierung Ägypten Kairo

ኤል ባራዳይ

ኤል ባራዳይ ሙባረክ ከሥልጣን እስካልወረዱ ድረስ አዲስ ነገር አይመጣም ባይ ናቸው ። «እንደሚመስለኝ ሁሉም መረዳት ያለበት ሙበረክ ዛሬ ከሥልጣን እስኪሰናበቱ ፣ ከጦር ኃይሉ ጋር በብሔራዊ የአንድነት መንግሥት እስክምንስማማ እንዲሁም የጦር ኃይሉ ጎዳናውን እስከሚቆጣጠር ድረስ አያበቃም።እነዚህን ሶሶት እርምጃዎች ከወሰድን እና በሂደትም የህዝቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች ካረጋገጥን ዲሞክራሲያዊና ለዘብተኛ አቋም ወደሚኖራት ግብፅ እንከን የሌለው ሽግግር እናደርጋለን ።» አሁን ባለው ሁኔታ የሙባረክ ዕጣ ፈንታ በወታደሩ እጅ የወደቀ ይመስላል ። የሙባረክ ጀነራሎች አመፁን ከማፈን ተቆጥበዋል ፣ ሙባረክን መደገፋቸውንም አላቆሙም ። ህዝቡ ወታደሩ ሚናውን እንዲለይ እየጠየቀ ነው ። ዛሬ በጣሂር አደባባይ ከሚነበቡት መፈክሮች አንዱ ወታደሩ ከግብፅና ከሙባራክ እንዲመርጥ የሚጠይቅ ነበር ።

NO FLASH Ägypten Proteste Zerstörung in Kairo

ሰባተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የግብፅ ህዝባዊ ንቅናቄ የሀገሪቱን ገፅታ በብዙ መልኩ ቀይሯል ። አመፁ ከ 100 የሚበልጡ ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል ። ግብፅ ዛሬ ከልተረጋጉ ሀገሮች ተርታ ገብታለች ፤ የቱሪስት መስህብነቷ ለጊዜው ተገቷል ። ስርዓተ አልበኝነት ተስፋፍቷል ። ዝርፊያው ተጧጡፏል ። እስረኞች አምልጥዋል ። ቀን አደባባይ የሚውለው ህዝብ ማታ ደግሞ ቤት ንብረቱን ከወሮበሎች ሲጠብቅ ነው የሚያድረው ። « በየጎዳናው ዘራፊዎች ትላልቅ ካራዎች ይዘው ይንቀሳቀሱ ነበር ። የአካባቢው ነዋሪዎች ስለ ነርሱ መረጃዎችን ይለዋወጡ ነበር ። የቀበሌው ነዋሪ ወጣት ወንዶች እነዚህን ዘራፊዎች ለማባረር ዱላ ይዘው ነበር የተከተሉዋቸው ። » ለ 30 ዓመታት ግብፅን የገዙት ሙባረክ እና ባለሥልጣናቶቻቸው ይውረዱ የሚለው የህዝቡ ግልፅ ጥያቄ እስከ ዛሬ ድረስ አልተመለሰም ። ዝህቡ አመፁን ወደ ስራ ማቆም እያሸጋገረው ነው ። ነገም ታላቅ ህዝባዊ ሰልፍ ተጠርቷል ። ሂሩት መለሰ ነጋሽ መሐመድ

ተዛማጅ ዘገባዎች