የተጠናከረው የተፈጥሮ ቁጣ | ጤና እና አካባቢ | DW | 07.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የተጠናከረው የተፈጥሮ ቁጣ

የአየር ንብረት ለውጥ ውሎ እያደረ እውንነቱን እያሳየ መምጣቱን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ተመራማሪዎች ማስረጃ መጥቀስ ከማያስፈልጋቸው ደረጃ መድረሳቸውን ይናገራሉ። ባለፈው እና በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የተደረሱ ተከታታይ የተፈጥሮ ቁጣዎች በሚቀጥሉት ዓመታት በእጥፍ ተጠናክረው እንደሚከሰቱም ከወዲሁ ያስጠነቅቃሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:40

የዘንድሮው የተፈጥሮ አደጋ

ያለፉት ወራት ሐምሌ እና ነሐሴ ጠንከር ያለ የተፈጥሮ ቁጣ የታየባቸው ወራት መሆናቸው ተመዝግቧል። እሳት ያስከተለው ደረቅ አየር በደቡብ አውሮጳ ሃገራት፤ በሩሲያ እና በሰሜን አሜሪካ የሰደድ እሳት ሲቀሰቅስ፤ ለቀናት የወረደው ከባድ ዝናብ ደግሞ በምዕራብ አውሮጳ፤ አፍሪቃ እና እስያ ውስጥ አደገኛ ጎርፍ አስከትሏል። ባለፉት ወራት በተለያዩ ሃገራት የተከሰተው የተፈጥሮ ቁጣ በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ በማለፉ የበርካታ ወገኖች ኑሮ ተናግቷል፤ በየሃገራቱም የኤኮኖሚ አቅም ላይ ተጽዕኖውን አሳርፏል። በቀጣይስ?

1000 ስኩየር ኪሎ ሜትር ያዳረሰ ሰደድ እሳት ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለባት ግሪክ የአየር ንብረት ቀውን የሚመለከት አዲስ ኮሚቴ ለማቋቋም ተገድዳለች። 170 ሺህ ሄክታር መሬት ያካለለው ቱርክን ከሁለት ሳምንት በላይ ያስጨነቀው የሰደድ እሳትም በሀገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ እጅግ የከፋ መሆኑ ተመዝግቧል። በምዕራብ አውሮጳ የነበረው ከፍተኛ ሙቀትም ስፔን እና ፈረንሳይንም ለሰደድ እሳት አጋልጧል። ወደ ሰሜን አሜሪካም ካናዳ እና ዩናይትድ ስቴትስ እሳት ሲያጠፉ ነው የከረሙት፤ ከእሳቱ በተጓዳኝ የባሕር ማዕበል እና ውሽንፍር ያጀበው ከባድ ዝናብ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል። ኃይለኛው ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በምዕራብ የጀርመን ግዛት፣ በቤልጂየም፣ ኔዘርላንድ እንዲሁም ሌሎችም ሃገራት ሕይወት አጥፍቷል ከፍተኛ የንብረት ውድመት አስከትሏል።

USA Nach Hurricane Ida

አይዳ የተሰኘው ከባሕር የተነሳው ሞገድ በዩናይትድ ስቴትስ

በተለያዩ ሃገራት የታየው የተፈጥሮ ቁጣ በአመዛኙ የአየር ንብረት ለውጥ አይነተኛ ማሳያ ተደርጎ ነው የተወሰደው። የዘርፉ ባለሙያ እና በካናዳ ካልጋሪ ዩኒቨርሲቲ የአዛላቂ ምርት እና አገልግሎት ልማት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ጌታቸው አሰፋ የተመለከትነው የተፈጥሮ አደጋ ያልተጠበቀ አይደለም ነው የሚሉት።

 «በሳይንሱ ዓለም ይኽ ድንገቴ አይደለም፤ ለብዙ ዓመታት በየትኛው ወቅት በምን ሁኔታ፤ በየትኛው ቦታ ምን ሊሆን እንደሚችል ሲነገር የነበረ፤ እየተነገረም ያለ ነገር ነው።» እናም ፕሮፌሰር ጌታቸው እንደሚሉት በመከታተል የሚከሰቱት የተፈጥሮ አደጋዎች የሰዎች እንቅስቃሴ እና አካባቢው የሚሸከመው የጫና ብዛት ሚዛን የመሳቱ ማሳያ ነው።  በአሁኑ ጊዜ በተደጋጋሚ የሚታዩት የተፈጥሮ አደጋዎች ቢያንስ ላለፉት 150 ዓመታት ታይተው እንደማያውቁ ያመለከቱት የዘርፉ ተመራማሪ ትርጉም ያለው ሥራ ካልተሠራ እየባሰ ይሄዳል ባይ ናቸው።

Türkei | Waldbrände in Mugla

በቱርክ ሰደድ እሳት ያደረሰው ውድመት

የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎችም ሆኑ የዘርፉ ተመራማሪዎች በየጊዜው በተለይ በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሃገራቱ የፖለቲካ መሪዎች በየበኩላቸው ተገቢውን የበካይ ጋዞች ቅነሳ ተግባራዊ ርምጃ እንዲወስዱ ጥሪያቸውን ያቀረባሉ። ፖለቲከኞቹም በሚያገኙት መድረክ ሁሉ ቃል ይገባሉ። ተግባራዊ ርምጃው ግን ዛሬም ብዙ ይቀረዋል። ኮቪድ 19 በወርሽኝነቱ ዓለምን ባስደነገጠበት በጎርጎሪዮሳዊው 2020 ዓ,ም የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት በበርካታ ሃገራት በተደነገገው የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት መጠነኛ የብክለት ቅነሳ ታይቶ እንደነበር አይዘነጋም።  ፕሮፌሰር ጌታቸው እንደሚሉት ግን በአጭር ጊዜ ያን ያህል ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ አይቻልም።

Überschwemmung Bangladesch

ጎርፍ በባንግላዴሽ

ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመትም ሆነ ዘንድሮ የታዩት የተፈጥሮ አደጋዎች በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሃገራት የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪ አካላት የሚወስዱትን የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ቅነሳ እንዲያጤኑት ግድ ሳይላቸው የቀረ አይመስልም። ምናልባት በመጪው ጥቅምት ወር ማለቂያ ግላስጎው እንግሊዝ ላይ በሚካሄደው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ ወደ ተግባራዊ ርምጃ እንዲሸጋገሩ ገፊ ምክንያት ይኾን?  «ተስፋ መቼም አይቋረጥም፤ ግን አያደርጉም ብዬ ነው የምሰጋው። ደጋግመን እንደምንለው አሁንም እንዳልነው፤ የሳይንሱ ዓለም ድርሻው መረዳት እና መለካት ላይ ነው፤ እናም የተወሰነ ድጋፍ ካገኘ ደግሞ ከፖለቲከኞች መከወን ነው። በተግባር ያንን መግለጽ።»

USA Hurricane Ida Wirbelsturm New York

ጎርፍ ኒዉዮርክ ዩናይትድ ስቴትስ

በዚህ መሀልም ከፓሪሱ የብክለት ቅነሳ ስምምነት በቀድሞ ፕሬዝደንቷ ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ የወጣችው ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ስምምነቱ እንደምትመለስ እየተጠበቀ ነው። በኢንዱስትሪ የበለጸጉትም ሆነ ወደዚያው እየተጓዙ የሚገኙት ሃገራት በሚያካሂዱት የኤኮኖሚ እና ፖለቲካ ሽኩቻም ለብክለቱ እጅግም አስተዋጽኦ የማያደርጉ ሃገራት ሕዝቦች ዕዳ ከፋይ መሆናቸውንም አጽንኦት ሰጥተዋል። በከባቢ አየር በካይነት ቻይና ግንባር ቀደሟ ስትሆን፤ ከእሷ የምትከተለው ዩናይትድ ስቴትስ ናት። የአውሮጳ ሃገራት ብሪታያን ጨምሮ፤ ሕንድ፣ ሩሲያ እና ጃፓንም ከቀዳሚዎቹ እና ዋነኞቹ ተርታ ተሰላፊዎች ናቸው።

USA Hurricane Ida Wirbelsturm Louisiana

ሉዊዚያና የአይዳ ማዕበል ሰለባዎች

የአየር ጠባይ ይዞታው ከዓመት ዓመት ድርቅ እና ሰደድ እሳት፤ በሌላ ጎኑ ደግሞ ከባድ ዝናብና ጎርፍ እያፈራረቀ ነው። በቀጣይ ክረምቱስ እንዴት ይኾን የሚለው ስጋትም አለ። የዘርፉ ተመራማሪ ፕሬፌሰር ጌታቸው እንደገለጹን የዓለምን የሙቀት ሚዛን የሚያስጠብቁ ዋና ዋና የሚባሉ የተፈጥሮ ሞተሮች ያሏቸው ይዞታዎች እየተዳከሙ እና እየተሸረሸሩ መሄድ ከተፈጥሮ አደጋዎች ስጋት እፎይታ ሊያመጣ የሚችለውን የመሬትን የሙቀት መጠን ቅነሳ ከሚፈለገው ግብ ለመድረስ የተቀናጀ እና ዘላቂነት ያለው ጥረት ይጠይቃል። ለዚህም ለዚህ ደግሞ ታሪካዊ እና አሁናዊ ኃላፊነት ያለባቸው በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያደጉ ሃገራት ጉልህ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ፕሮፌሰር ጌታቸው አሰፋን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ

 

Audios and videos on the topic