የተጠለፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን | ኢትዮጵያ | DW | 17.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የተጠለፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን

ዛሬ ጠዋት ጄኔቫ - ዚውዘርላንድ ላይ ለማረፍ የተገደደው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጠላፊ ራሱ የአይሮፕላኑ ረዳት አብራሪው መሆኑ ተረጋግጧል። በርካታ መንገደኞችን አሳፍሮ ከአዲስ አበባ ወደ ሮም ይበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን ጄኔቫ አየር ማረፊያ ሲራርፍ በመንገደኞቹ ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።

ከአዲስ አበባ ወደ ሮም በጉዞ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን እንደታቀደው ሮም ሳይሆን ዛሬ ጠዋት በስዊዘርላንድ የጄኔቫ የአየር ማረፊያ ለማረፍ መገደዱን ነው የሲውዘርላንድ ፖሊስ የገለፀው። የአይሮፕላን ማረፊያ ቃል አቀባይ ቤርትሮ እሽቴምፍሊ ለዶይቸ ቬለ እንደገለፁት፤ « ረዳት አብራሪው ራሱ ከበረራ ክፍል በገመድ ነው የወረደው፤ ኃላም አብራሪው እና የአይሮፕላኑ ጠላፊ እሱ ራሱ እንደሆነ ነው የተናገረው። በ1983 የተወለደ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ነው የምናውቀው። በአሁኑ ሰዓት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ይገኛል። ቃሉን እየሰጠ ነው። በሚቀጥሉት ሰዓታት አብራሪውን ለዚህ ድርጊት የገፋፋው ምን እንደሆነ እናውቃለን ብለን እናምናለን። »

ቃል አቀባዩ ስለጠላፊው የበለጠ መረጃ እንደሌላቸው ቢገልፁልንም ለጊዜው ማንነታቸው ያልተጠቀሰው የአይሮፕላን ጠላፊ እና አብራሪ፤ ጥገኝነት ለመጠየቅ እንደሚፈልጉ በትዊተር ከተላከ የድምፅ መልዕክት ይደመጣል። «በሰዓቱ ጥገኝነት እናገኝ እንደሆን ያውቃሉ? እኛ ጥገኝነት ወይንም ማረጋገጫ እንፈልጋለን፤ ለኢትዮጵያ መንግሥት እንደማንሰጥ። »

ፖሊስ እያንዳንዱን መንገደኛ እጁን ጭንቅላቱ ላይ አድርጎ ከአይሮፕላኑ እንዲወርድ አስገድዷል። ቀደም ሲል በሰማነው ድምፅ ላይም « ጥገኝነት እንፈልጋለን» የሚለው ስለሚደመጥ፤ በርግጥ በዚህ የአይሮፕላን ጠለፋ አንድ ሰው ብቻ ነበር የተሳተፈው ለሚለው ጥያቄ ቃል አቀባዩ ምላሽ ሰጥተውናል።

« እስከምናውቀው ድረስ ብቻውን ነበር። ፖሊስ ዛሬ ጠዋት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ዋናው አብራሪ ከማብረሪያው ክፍል ወጥቶ ነበር ምናልባትም ወደ መፀዳጃ ቤት መሄድ ፈልጎ ነበር። ያኔም ረዳት አብራሪው የበረራ ክፍሉን እንደቆለፈ ፣ እና ብቻውን ወደጄኔቫ ለማብረር እንደወሰነ ነው የሰማነው። የበረረውም አይሮፕላኗን ያሳረፈውም ብቻውን ነው። ስለዚህ ብቻውን ነበር ለማለት ይቻላል።»

ትናንት ከሌሊቱ አስር ሰዓት ተኩል አይኖፕላኑ በደቡብ ኢጣሊያ በመብረር ላይ ሳለ ስለመጠለፉ የሰሙት ቃል አቀባይ፤ የኢጣሊያ የበረራ መቆጣጠሪያ (ሲቪል አቪዬሽን) ከጄኔቭ ጋር ከተነጋገረ በኋላ አይኖፕላኑ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ጄኔቫ እንደሚያርፍ መወሰኑን ገልፀውልናል። አክለውም፤« በፖሊስ አልተረጋገጠም ግን እስከምናውቀው ድረስ የኢጣሪያ 2 የጦር አይኖፕላኖች እስከ ፈረንሳይ ተከትለውት በረዋል ከዛም እንዲሁ 2 አይሮፕላኖች ከፈረንሳይ ተነስተው አይሮፕላኑ ጄኔቫ እስኪያርፍ ደረስ ተከትለውት በረዋል። »

የአይሮፕላኑ ተሳፋሪዎች በሰዓቱ በርግጥ ስለ አይሮፕላኑ መጠለፍ ያውቁ ይሁን አይሁን እስካሁን መረጃ ባይኖርም፤ ሁሉም መንገደኞች በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እሽቴምፍሊ አረጋግጠውልናል። መንገደኞቹም ለፖሊስ ቃል ከሰጡ በኋላ አየር ማረፊያው ቀጣይ በረራቸውን እንደሚያመቻች ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች