«የተጎዳ አካል እንጅ የተጎዳ አስተሳሰብ የለኝም»ሠዓሊ ዓለም ጌታቸው | ባህል | DW | 21.11.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

 «የተጎዳ አካል እንጅ የተጎዳ አስተሳሰብ የለኝም»ሠዓሊ ዓለም ጌታቸው

እስከ 12 ዓመቷ በኤርትራ አስመራ ዕንደ ዕድሜ እኩያዎቿ ቦርቃና ተጫውታ ያደገችው ሠዓሊ ዓለም ጌታቸው፤ ከ12 ዓመት ዕድሜዋ ጀምሮ ግን ባጋጠማት ህመም ሁለት እግሮቿ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው ቤት መዋል ጀመረች።ያኔ ነበር ለህይወቴ ተስፋ ሰጠኝ የምትለውን የመጀመሪያ ስዕል የሰራችው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:44

ቆይታ ከሠዓሊ ዓለም ጌታቸው ጋር


ሠዓሊ ዓለም ጌታቸው ወደ ስዕል ጥበብ የተሳበችው ገና በልጅነት ዕድሜዋ ነው።ከዘጠኝ እህትና ወንድሞቿ መካከል ሁለተኛ ልጅ የሆነችው ዓለም፤ በውትድርናው ዓለም በመካኒክነት ሙያ ያገለግሉት አባቷ ይሰሯቸው የነበሩ  የንድፍ ስራዎችን እያየች ማደጓ ለስዕል ጥበብ ትልቅ ቦታ እንድሰጥ አድርጓታል። ጎንደር  ተወልዳ አስመራና አዲስ አበባ ያደገችው ዓለም፤እስከ 12 ዓመቷ በኤርትራ አስመራ ዕንደ ዕድሜ እኩያዎቿ ቦርቃና ተጫውታ ያደገች ቢሆንም፤ ከ12 ዓመት ዕድሜዋ ጀምሮ ግን ባጋጠማት ህመም  ሁለት እግሮቿ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው  ቤት መዋል ጀመረች።ያኔ ነበር ለህይወቴ ተስፋ ሰጠኝ የምትለውን የመጀመሪያ ስዕል የሰራችው።


«መጀመሪያ ቤት ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ የአርት ትምህርት ቤት ሳልገባ በፊት መጀመሪያ የሳልኩት ወደ ሁለት ዓመት የሰራሁት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስዕል ነው።ለረጅም ጊዜ የሰራሁት ስዕል ነው።በጣምም በህይወቴ ተፅዕኖ አድርጓል።ብዙ ጊዜ ስዕል እሸጣለሁ ብዬ አላስብም ነበር።እሱን ግን አንድ ካህን አጋጣሚ ሊጠይቁኝ ቤት መጥተው  እሳቸው ገዝተውኛል።ያን ጊዜ በጣም ትልቅ ነገር ነበር የተሰማኝ።ምክንያቱም ወደ ፊት ራሴን ማገዝ  እችላለሁ።በደንብ ተምሬ  መስራት እችላለሁ።የሚለውን ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ ተስፋ የፈጠረልኝ ስዕል ነው።» በማለት ይህ ስዕል የወደፊት የህይወት መንገዷን የጠረገ መሆኑን አብራርታለች።
በዚህ ሁኔታ የጀመረችውን የስዕል ጥበብ ለማሳደግም አሰላ በሚገኘው የካቶሊክ ሚሽን  የጣሊያን የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት በመግባት  በስዕል ጥበብ በዲፕሎማ ተመረቀች።ለአምስት አመታት በተለያዩ ቦታዎች  ካስተማረች በኋላ በ2004 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ገርጂ መብራት ሀይል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ዓለም አርት ጋለሪና የስዕል ትምህርት ቤትን ከፈተች። በውሱን ተማሪዎች የተጀመረው ይህ ትምህርት ቤት፤ውሎ አድሮ ግን የአካባቢው ማኅበረሰብ ልጆቹን መላክ በመጀመሩ በአሁኑ ወቅት በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ትገኛለች።
ይህንን ቦታ ወደ ጥበብ ማዕከልነት በማስፋት ሰዓሊያንን ቀጥራ ታሰራለች የአጭርና የረዥም ጊዜ የስዕል ስልጠናዎችንም ትሰጣለች። ከስዕል በተጨማሪ ሰዎች ሻይ ቡና እያሉ መፅሀፍ የሚያነቡበት፣ የግጥም ምሽት የሚቀርብበት እና  የሀሳብ መድረክ የሚዘጋጅበትም አድርጋዋለች።


በጋለሪዋ ስዕል የሚያደንቁና የሚገዟት በአብዛኛው የውጭ ሀገር ዜጎች እንደነበሩ የምትገልፀው ዓለም፤በአሁኑ ወቅት ግን በማኅበረሰቡ ዘንድ ለጥበቡ ያለው ግንዛቤ እየተለወጠ በመምጣቱ የሀገር ውስጥ ደንበኞቿም እየተበራከቱ መጥተዋል።  
ዓለም እንደምትለው  የስዕል ስራዎቿ በአብዛኛው በኢትዮጵያ ሴቶች ህይወት ላይ የሚያተኩሩ ሲሆኑ ፤ተስፋን የሚያጭሩ ደማቅ እና ብሩህ ቀለማትን መጠቀም ያስደስታታል።እነዚህን ስራዎቿን በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንስ፣በሩሲያ የባህል እና የሳይንስ ማዕከል፣በዓለም ሲኒማ እና በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በተለያዩ የስዕል አውደ ርዕዮች ላይ  አቅርባ አድናቆትን አትርፋለች። የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ሽልማቶችንና እውቅናዎችንም አስገኝተውላታል። በጎርጎሪያኑ 2019 ዓ/ም በመላው አፍሪቃ የሚታተም  የጊዜ መቁጠሪያ  ለአንድ የጀርመን በጎ አድራጎት ድርጅት ሰርታለች።
«የተጎዳ አካል እንጅ የተጎዳ አስተሳሰብ የለኝም» የምትለው ሰዓሊ ዓለም ጌታቸው  ምንም እንኳ  ያለ ዊልቸር ድጋፍ መንቀሳቀስ የማትችል  ቢሆንም  የምትወደውን የጥበብ ስራ  ከመስራት እና ውጤታማ ከመሆን አላገዳትም።ከራሷ አልፋ ለሌሎችም የስራ ዕድል ፈጥራለች። ለዚህም በወላጅ አባቷ ይደረግላት የነበረው የሞራል ድጋፍ ዓለም እንደምትለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። 
ስለሆነም፤ አካል ጉዳተኛ ልጆች ያሏቸው ወላጆች፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ማኅበረሰቡ  በተጎዳው አካላቸው  ከንፈር ከመምጠጥ ይልቅ መስራት የሚችሉትን ነገር በማበረታታት ቢደግፋቸው መልካም መሆኑን ገልፃለች።ለዚህም የሷ ህይወት ማሳያ መሆኑን  ተናግራለች።  
በዚህ ረገድ የበኩሏን ለመወጣት ልጆች በበጎ አስተሳሰብ የተቃኙ  እና በጥሩ ሥነ-ምግባር የታነፁ እንዲሆኑ የሚያግዙ ስድስት የልጆች መፃህፍትንም ፅፋለች።


«አብረን» በሚል ስም የበጎ አድራጎት ድርጅት በመክፈት አካል ጉዳተኞችን በማስተማር ላይ ነች። ይሁን እንጅ አሁን ያለችበት ቦታ  እጅግ ጠባብ በመሆኑ በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ በርካታ ተማሪዎችን ለማስተማር መገደዷን ገልፃለች። ስራዋን በስፋት ለማከናወን የሚያስችል ቦታ ለማመቻቸት በዝግጅት ላይ በመሆኗ  ድጋፍ እንደሚያሻትም አጫውታናለች። 


ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

ፀሐይ ጫኔ
ሂሩት መለሠ

Audios and videos on the topic