የተገኘዉ የአዉሮፕላን ስባሪ ከየት መጣ? | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 05.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የተገኘዉ የአዉሮፕላን ስባሪ ከየት መጣ?

ከማሌዥያ ኳላላምፑር ወደ ቻይና ፔኪንግ 239 ሰዎችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረ የመንገደኞች ማመላለሻ አዉሮፕላን ከጠፋ አንድ ዓመት ከመንፈቅ ግድም አስቆጠረ። ከማዳጋስካር 700 ኪሎ ሜትር ርቀት ሪዩኒየን ደሴት የባህር ጠረፍ ላይ የተገኘዉ የአዉሮፕላን ስባሪ የጠፋዉ የማሌዢያ አዉሮፕላን አካል እንደሆን ተረጋግጦአል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:53
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:53 ደቂቃ

የተገኘዉ የአዉሮፕላን ስባሪ ከየት መጣ?

ሪዩኒየን ደሴት የባህር ጠረፍ የተገኘዉ የአዉሮፕላን ስባሪ ምናልባት የጠፋዉ የማሌዢያ አዉሮፕላን አካል ሳይሆን እንዳልቀረ ተነግሮ ነበር። የዉቅያኖስ ዉኃ ዝዉዉር አጥኚዎች እንደሚሉት ደግሞ የተገኘዉ የአዉሮፕላን ስባሪ ይወድቃል ተብሎ ከታሰበበት በ 17 ወራት ጊዜ ዉስጥ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ መገኘቱ የሚታመን ነዉ ። በዕለቱ ዝግጅታችን የተሰወረዉን የማሌዥያ አዉሮፕላን MH370 ጉዳይ የባህር ዉኃ ንቅናቄ አጥኝዎች ትንታኔን እንቃኛለን።ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት በበራራ ላይ ሳለ የገባበት ያልታወቀዉ የማሌዥያ የመንገደኞች ማመላለሻ አዉሮፕላን MH370 ግንጣይ ሳይሆን እንዳልቀረ የተነገረለት ስባሪ በህንድ ዉቅያኖስ ሪዩኒየን በተሰኘ ደሴት ላይ መገኘቱ ይታወቃል። እስከዛሬ የደረሰበት በዉል ያልታወቀዉ የማሌዥያ አዉሮፕላን ላይ ተሳፍረዉ የነበሩ ሰዎች ቤተ-ዘመዶች እና ወዳጆቻቸዉ የት እንደገቡ ሳያዉቁ አንድ ዓመት ከመንፈቅ በእንጥልጥል ሃሳብ ላይ መሆናቸዉ ይታወቃል። 239 ሰዎችን አሳፍሮ የነበረዉ የማሌዥያ አዉሮፕላን ሊሰወር ወይም ሊከሰከስ ይችላል የተባለበት ቦታ ሁሉ በረቀቀ የቴክኖሎጂ ዉጤት እየተለካና በከፍተኛ ቴክኒካዊ የምርምር መሳሪያ በመታገዝ ተፈትሾአል። በህንድ ዉቅያኖስ ከምስራቃዊ ማዳጋዝካር 700 ኪሎ ሜትር ከሞሪሸስ ደግሞ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘዉ የፈረንሳይ ደሴት ሪዩኒየን ጠረፍ ላይ የተገኘዉ የአዉሮፕላን ስባሪ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የጠፋዉ የማሌዥያ አዉሮፕላን አካል ይሁን አይሁን ለማወቅeባሪዉ ወደ ፈረንሳይ በተላከ በአንድ ሳምንቱ MH370 አዉሮፕላን ስባሪ መሆኑ ተረጋግጦአል።

ስባሪዉ እንደተገኘ አዉሮፕላኑን በግንባር ቀደምትነት የምትፈልገዉ የአዉስትሬሊያ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ዎረን ትረስ ስባሪዉ እስካሁን ከተገኙት ምልክቶች ሁሉ በጣም አሳማኝ ምልክት መሆኑን ገልፀዉ ነበር።

«ይህ በእዉነት ትልቅ እመርታ ነዉ። አሁን የተገኘዉ የአዉሮፕላኑ ስባሪ ሊሆን እንደሚችል ጠንካራ መረጃ የሚሆን ነዉ። ስባሪዉ የአዉሮፕላኑ ነዉ ብሎ ለመናገር በርግጥ ጊዜዉ ገና ነዉ። ይሁንና አሁን የተገኘዉ መረጃ እስካሁን የተደረገዉ ፍለጋ ሁነኛ ደረጃ ለመድረሱና MH370 ድንገት የተሰወረበትን ምክንያት ለማወቅ ለሚደረገዉ ጥረት ፍንጭ ሊሰጥ የሚችል ነዉ።»የዉቅያኖስ ዉኃ ዝዉዉር ጥናት ባለሞያ ጀርመናዊዉ ፕሮፊሰር አርነ ቢያስቶች በበኩላቸዉ የተገኘዉ የአዉሮፕላን ግንጣይ የደረሰበት ያልታወቀዉ አዉሮፕላን ወድቆ ይሆናል ተብሎ ከተገመተበት አካባቢ በጣም ርቆ ያልተረበሸ የዉቅያኖስ እንቅስቃሴን ተከትሎ ሕንድ ዉቅያኖስን አቋርጦ ትንሽዋ ደሴት ሪዩኒየን አካባቢ ተንሳፎ ሊመጣ ይችላል ሲሉ ነዉ የገለጹት። ይህ ከሆነ በሕንድ ዉቅያኖስ ላይ ያለዉ ማዕበል ፍጥነት በሰዓት ከአንድ ኪሎ ሜትር ያነሰ ይንቀሳቀሳል። አዉሮፕላኑ ከጠፋበት ጊዜ ከታሰበ ደግሞ በ17 ወራት ዉስጥ ወደ 4000 ኪሎ ሜትር ሊጓዝ እንደሚችል ነዉ ፕሮፊሰር አርነ ቢያስቶች የገለፁት።

እንደ ባለሞያዎች ትንተና የዉቅያኖስ እንቅስቃሴ አቅጣጫ ምናልባትም የጠፋዉን አዉሮፕላን ወዴትነት ሊያመላክት አዲስ ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል።

የማሌዥያ ትራንስፖርት ምክትል ሚኒስትር አዚዝ ካፓራዊ የአዉሮፕላኑ ስባሪ ወደ ፈረንሳይ ለምርመራ ከተላከ በኋላ በሰጡት መግለጫ ምርመራዉ ጥቂት ቀናት ብቻ እንደሚፈጅ ነዉ የገለጹት፤

«እንደኔ ግምት ምርመራዉ የሚቆየዉ አንድ ሁለት ቀን ብቻ ነዉ የሚዘልቀዉ፤ ምክንያቱም የተገኘዉ ስባሪ ትልቅ የሚባል እቃ አይደለም። በሌላ በኩል እተገኘዉ የአዉሮፕላን ስባሪ ላይ የመለያ ቁጥር ስለሚኖር ለይቶ ለማወቅ አይከብድም ጊዜም አይፈጅምም»

የጠፋዉን የማሌዥያ MH370 አዉሮፕላን በተመለከተ የዉቅያኖስ ዉኃ እንቅስቃሴ ምሁራን የስከዛሬ ግምት አዉሮፕላኑ የታቀደለትን መንገድ ይዞ ሳይሆን በሌላ አቅጣጫ በሺዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትርን አቋርጦ ምናልባት ህንድ ዉቅያኖስ ላይ ሳይወድቅ አይቀርም የሚል ነበር። አዉሮፕላኑ ከራዳር ከተሰወረ በኋላ ደቡባዊ የህንድ ዉቅያኖስ አካባቢ ሰፊ በሆነዉ

የዉቅያኖስ ጠለል አዉሮፕላኑን ለማግኘት መርከብና ሳተላይትን ጨምሮ በርካታ ሃገሮች የተሳተፉበት ለወራቶች የዘለቀ እጅግ ብዙ ወጭን የጠየቀ አድካሚ ፍለጋ መካሄዱም ይታወቃል። በፍለጋዉ ወቅት ምሁራን በዉቅያኖስ ጠለል ላይ በሳተላይት በመደገፍ የተለያዩ ቆሳቁሶችን፤ በተለያዩ ጊዜያት አይተዉ በተደጋጋሚ እቃዉን እጃቸዉ ቢያስገቡም የጠፋዉ የአዉሮፕላን አካል ግንጣይ ሆኖ ግን አላገኙትም።

ዓለም አቀፉን ፍለጋ በተመለከተ፤ በኢትዮጵያ ባህር ኃይል ለ 26 ዓመት ያገለገሉት ኮማንደር መላኩ ዳኘ በባሕር ኃይል አገልግሎት ለማንኛዉም ሰላማዊ ስራ ለመተባበር የዓለም ሃገራት በተመድ ስምምነት መፈራረማቸዉን ተናግረዋል።

ባለፈዉ ሳምንት አጋማሽ የተገኘዉ የአዉሮፕላን ስባሪ ምናልባት ፍለጋዉን እስከዛሬ በተፈለገበት በደቡባዊ አቅጣጫ ሳይሆን ወደ ሰሜናዊ አቅጣጫ ሳይቀይረዉ እንደማይቀር ተመልክቶአል። የዉቅያኖሱ እንቅስቃሴ አቅጣጫ ከተገኘዉ የአዉሮፕላን ስባሪ ጋር በማነፃጸር የጠፋዉ አዉሮፕላን ሊኖር ይችላል የተባለበት ቦታ እንደ እስካሁኑ በአዉስትራሊያ የባህር ዳርቻ ሳይሆን በሰሜናዊ የዉቅያኖስ ክልል መሆኑ ተጠቅሶአል። የዉቅያኖስ ጉዳይ ተመራማሪዉ ጀርመናዊ እንደ ፕሮፊሰር አርነ ቢያስቶች እንደሚሉት የዉቅያኖሱ እንቅስቃሴ አቅጣጫ የተገኘዉ የአዉሮፕላን ስባሪ የመጣዉ ከኤንዶኔዥያ በኩል አልያም ከሰሜናዊ አዉስትራልያ የባህር ዳርቻ በኩል ነዉ። የዉቅያኖሱ ማዕበል ወደ ደቡባዊ አዉስትራልያ አቅጣጫ ቢሆን ኖሮ ይህ አዉሮፕላን ስባሪ በሌላ አቅጣጫ ተንሳፎ ይገኝ ነበር ፤ ይህ ማለት የተገኘዉ አዉሮፕላን ስባሪ በላሪዮ ደሴት አካባቢ ባልተገኘ ነበር ።

የዚህን የማዕበል አቅጣጫ ሳይንሳዊ ትንታኔ ለማጎልበት ፕሮፊሰር አርነ ቢያስቶች ከዓለም ከተሰባሰቡ ምሁራኖች ጋር በመሆን የባህር ላይ ጉዞ አቅጣጫ ለማየት አንድ ሙከራ አደረጉ። ከሳተላይት ጋር የተገናኘ የኮምፒዉተር መረጃ ማቀበያ ክፍልን ወደ ባህር በመወርወር መረጃን ሰበሰቡ ፤ ይህ መረጀ ማስተላለፍያ እቃ ለአንድ ዓመት ተኩል መረጃን ሲቀብል ቆይቶአል ሳተላይቱ ከሰበሰበዉ መረጃ የባህር ጠለል ከፍተኛ እና ዝቅተኛ የሆነበትን አጋጣሚ ሲመትር ቆይቶአል።እንደ ኮማንደር መላኩ ዳኘ የአዉሮፕላኑ ስባሪ ሪዮኒዮን ደሴት የተገኘዉ ምናልባት አዉሮፕላኑ ጭቃ አልያም አሸዋማ በሆነ የባህር ጠለል ላይ ተሸንቅሮ ከዝያ ላይ ማዕበል ከፍ ዝቅ ሲያደርገዉ ተገንጥሎ የወጣ የአዉሮፕላን ስባሪ ይሆናል።

የባህር ጠለል ከፍታና ዝቅታን በመለካት የዉኃዉን እንቅስቃሴ ፍጥነት መለካትና ማወቅ እንደሚቻል ተመልክቶአል። አዉሮፕላኑ ከተሰወረበት ጊዜ አንስቶ ሳተላይት ላይ ከሚገኘዉ መረጃ በመነሳትም የባህሩን ፍሰት ፍጥነት ማግኘት እንደሚቻልም ነዉ የተመለከተዉ። በዚህም ባህር ላይ ከተወረወረዉ የሙከራ መረጃ መሰብሰብያ መሳሪያ የሰበሰበዉን መረጃ ከሳተላይት ከተገኘዉ ዉጤት ጋር በማነፃፀር አዉሮፕላኑ የትኛዉ አካባቢ የባህር አልያም የዉቅያኖስ ጠለል ላይ እንደወደቀ በማወቅ የፍለጋ ሥራዉ እንደሚጀምር ተመልክቶአል። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫዉን ማዕቀፍ በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic