የተገን ጠያቂዎች የሥራ ሁኔታ በጀርመን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 11.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የተገን ጠያቂዎች የሥራ ሁኔታ በጀርመን

ጀርመን ሐገር ጥገኝነትጠይቀው፣ጥያቄያቸው ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ በጊዜያዊነት እንዲቆዩ የተፈቀደላቸው የውጭ ዜጎች ለብዙ ዓመታት በስራ አጥነት ለመኖር ይገደዳሉ። የጀርመን ሕግ ተገንጠያቂዎች ፈልገው ባገኙት ክፍት የሥራ ቦታ በቀጥታ እንዳይሰማሩ ይገድባቸዋል ። ይህንየሚለውጥ አዲስ ህግ በቅርቡሥራ ይይውላል ።

የ20 አመትዋሚትራና ወላጆቿ ከአፍጋኒስታኑ ጦርነት ሸሽተውከ3 ዓመት በፊት ወደ ጀርመንዋ  ከተማ በርሊን  የተሰደዱ የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው ። በርሊን የመጡትም ትልቅተስፋ ሰንቀው ነበር  ። በአዲሲቷ መኖሪያቸው በርሊን መጀመሪያ ላይ ሥራ በቀላሉ በኢንተርኔት ተፈልጎ የሚገኝ ነበር የመሰላቸው ። ጀርመን ሥራይጠፋል አለያም መስራትይከለላልየሚልግምትአልነበራቸውም። የሚትራ አባት አማን ሃሼሚበአገራቸው በአፍጋኒስታን ከኢራን እቃየሚያስመጡ ነጋዴ ነበሩ።ጀርመን ከመጡ በኋላ አፍጋኒስታን ያደርጉ እንደነበረውመነገድ ባይችሉም በተገኘው አነስተኛ ሥራ ለመሰማራት ያለመታከት በስራ ፍለጋ ሲባዝኑ ከርመው ከብዙ ልፋትና ሙከራ በኋላ በአንድ የጨርቃ ጨርቅ ድርጅት ውስጥ በልብስ ተኳሽነት ሥራ አገኙ። ሥራማግኘታቸውአስደሳች ቢሆንም የስደተኞች

ጉዳይ ቢሮ ግን እንዲሰሩ አልፈቀደላቸውም ። እንደ ሃሺም  ቤተሰብ ሁሉ ተገን ጠያቂ የውጭ ዜጎች  መሥራት የሚችሉት ሲፈቀድላቸው ብቻ ነው ።   ጀርመን ፍራንክፈርት ነዋሪ የሆኑት የህግ ባለሞያ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ  እንደሚያስረዱት፣ሥራው ለተገን ጠያቂው ከመሰጠቱ በፊት የፌደራል ጀርመን የአሰሪና ሰራተኞች  ጉዳይ መስሪያ ቤት በቅድሚያ  የማጣራት ሥራዎችን ያከናውናል ።

መስሪያ ቤቱ ይህን ለማከናወን በመላ ጀርመን ለተገኘው ክፍት የሥራ ቦታ በመላ ጀርመን ማስታወቂያ እንዲወጣ ያደርጋል ። ይህ አሰራር  በተዘዋዋሪ መንገድ እነዚህ ስደተኞች እንዳይሰሩ መከልከል  ነው ሲሉ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የህግ ባለሞያዎች  ይተቻሉ ። ጀርመንኛ የማይችሉ ወይም  ጥቂት የጀርመንኛ ቋንቋ ችሎታ ያላቸው ተገን ጠያቂዎች ብዙውን ጊዜ ሊያገኙ የሚችሉት አነስተኛ ሥራዎችን ነው ። እነዚህን ሥራዎችም ቢሆን ከስራ አጥ ጀርመናውያን ከተረፉ ብቻ ነው መሥራት የሚፈቀድላቸው ። የህግ ጠበቃ ቤርኒስ ቦህሎ መጀመሪያ ለጀርመናውያን ከዚያም ለአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ዜጎች ቅድሚያ የሚሰጠው ህግ  ይፋ ያልሆነ ነገር ግን ተገን የጠየቁም ሆነ አስተያየት ተደርጎላቸው ጀርመን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆዩ የተደረጉ የውጭ ዜጎች እንዳይሰሩ የሚያግድ አሰራር ነው ይላሉ ።

« ብዙውን ጊዜ ፅዳት ወይም የፒሳ ቤቶች ሥራ ነው የሚያገኙት ። ለነዚህ ሥራዎች ደግሞ ርግጥ ነው ስራ አጥ ጀርመኖች ወይም የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ዜጎች አሉ  ።  እነርሱ ለስራ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ። ቢያንስ በበርሊንና በአዳዲሶቹ የፌደራል ግዛቶች እንዲህ ነው የሚሰራው ። በደቡብ ግን በመጠኑ ይለይ ይሆናል ። በመሰረቱ በህግ ባይሰፍርም  እነዚህ ስደተኞች እንዳይሰሩ የሚያግድ አሰራር ነው ያለው መባል አለበት ።  »

ከዚህ ሌላ ተገን ጠያቂዎችን ለመቅጠር  ግዴታ የሆነው አሰልቺ የፈቃድ ጥየቃና ፈቃድ እስከሚገኝ ድረስ በርክታ ቀጣሪዎችን የሚያስበረግግ እንደሆነም ነው ጠበቃ ቦህሎ የሚናገሩት ። አስተያየት ተደርጎላቸው ጀርመን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆዩ ለተፈቀደላቸው የውጭ ዜጎች ፣ የሥራ አጡ ቁጥር ከፍተኛ በሆነባቸው በበርሊንና  በምስራቅ ጀርመን የስራ ፈቃድ ማግኘት አስቸጋሪ ነው ። ለተገን ጠያቂዎች ደግሞ ፍፁም የማይቻል ነው።  ከቦህሎ ደንበኞች አብዛኛዎቹ የሥራ ማመልከቻ ቅጾችን ሞልተው ሥራ ከማግኘት ተስፋ ጋር ወደ ስደተኞች ጉዳይ ቢሮ  ከመሄድ ቦዝነው አያውቁም ። ቦህሎ እንደሚሉት ከመካከላቸው 10 በመቶው እንኳን ከአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ መስሪያ ቤቶች የሚያስፈልጋቸውን ፈቃድ አያገኙም ።  የፌደራል  ጀርመን መንግስት ጀርመን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆዩ የተፈቀደላቸው የተገን ጠያቂዎች ስራ ማግኘት የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ለማቅለል ውሳኔ አሳልፏል ። በዚሁ መሰረት በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከሐምሌ 1 ,2013 ዓም አንስቶ አዲስ ህግ ሥራ ላይ ይውላል ። አዲሱ ህግ ከቀደመው በምን እንደሚለይ ዶክተር ለማ ያብራሩልናል

ይሁንና በቦህሎ እምነት ይህ እርምጃ ብቻውን በቂ አይደለም ። ህጉ ቢሻሻልም ወደፊት ያን ያህል ለውጥ  ይመጣል ብለው አይጠብቁም ። እስካሁን ሲሰራበት በቆየው ህግም መንግስት በተዘዋዋሪ መንገድ ተገን ጠያቂዎች እንዳይሰሩ ባደረገበት አሰራር ተስፋ ለማስቆረጥ እየሞከረ ነው ይላሉ ።  መርሁ ተቃራኒ ውጤት ማምጣቱን ነው ቦሆሎ የሚናገሩት  ።

« ከህግ አውጭዎቹ እይታ አኳያ « የተስፋ ማስቆረጫ » መርሃ ግብር አንድ አካል  ነው ። ሰዎቹ እዚህ ተደላድለው እንዲቀመጡና እንዲሰሩ እንዲሁም ከሰው ጋር እንዲገናኙ አይፈለግም ።  ተገን ጠያቂዎቹ በፍራቻ ወደ ጀርመን እንዳይገቡ የሚከላከለውን መርሃ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ ሰዎቹ ራሳቸውን በገንዘብ እንዲደግፉ ከማድረግ ይልቅ ለነሱ ገንዘብ ይሰጣል ።  ወጪው ሲታይ ግራ የሚያጋባ ነው ። »

ሰዎቹ ጀርመን ብዙ በቆዩ ቁጥር ጀርመንኛ የመማር ፍላጎታቸውና ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ አቅማቸው  እየደከመ ሞራላቸውም እየቀነሰ ይሄዳል ። አፍጋናዊቷ ሚትራ እንደምትለው አባትዋ ያለ ሥራ በመቀመጣቸው ቅስማቸው ተሰብሯል ። ስራ ፍለጋውና  ደብዛው የጠፋው ስራ የማግኘት ተስፋ በኖ የቀረ መምሰሉ ና ቢያንስ የጀርመንኛ ቋንቋ መማር አለመቻላቸው ተደራራቢ ችግሮች ሆነውባቸዋል ። በዶክተር ለማ እምነት አዲሱ ህግ እሰየው የሚያሰኝ ቢሆንም የውጭ ዜጎችን ሥራ የማግኘት ችግር ግን መሉ በሙሉ የሚያቃልል አይሆንም ።

የሚትራ አባት አማን ለሰዓታት ቴሌቪዥን በማየት በተለይም ስለአፍጋኒስታን ዜና በመከታተል ነው ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ይህም ይበልጡን ተስፋ ያስቆርጣቸዋል ።  ከጦርነት ማምለጥ መቻላቸው ቢያስደስታቸውም መሥራት እየቻሉ እንደ ደካማ ገንዘብ መቀበላቸው አያስደስታቸውም ። ሰርተው ባገኙት ገንዘብ ነው መተዳደር  የሚፈልጉት ። ምናልባት በአዲሱ ህግ ይህ ምኞታቸው ይሳካ ይሆናል ።

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic