የተዘነጉ የሞቃታማ አካባቢ በሽታዎች በአፍሪቃ | ጤና እና አካባቢ | DW | 25.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የተዘነጉ የሞቃታማ አካባቢ በሽታዎች በአፍሪቃ

በአፍሪቃ በተለይም ከሰሃራ በታች በሚገኙ ሃገራት በሞቃታማ አካባቢወች በሚከሰቱ በሽታወች ብቻ በየ አመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞትና ለአካል ጉዳት ይዳረጋሉ ተባለ።  አህጉሪቱ በሽታወቹን ለመከላከል ትኩረት ሰጥታ ባለመስራቷም ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ የሆነዉን አምራች የሰዉ ሀይል እያጣች ነዉ ሲል የአለም አቀፉ የጤና ድርጅት አመለከቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:48

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይሞታሉ


በአፍሪካ በተለይም ከሳሃራ በታች በሚገኙ ሃገራት በሞቃታማና በወንዞች አቅራቢያ በሚኖሩ ሰዎች ላይ የሚከሰቱ በሽታወችን መከላከል፣ መመቀነስና ማሰወገድ የሚቻል ቢሆንም ተገቢዉን ትኩረት ባለመሰጠቱ የአህጉሪቱ አምራች ሀይል ለአካለ ጉዳት በሎም ለሞት እየተዳረገ ነዉ ሲል አለማቀፉ የጤና ድርጅት በምህጻሩ ደብሊዉ ኤች ኦ አመለከተ።
የድርጀቱ የአፍሪካ ተጠሪ ዶክተር ማትሺዶስ ሞየቲ አንደገለጹት  እንደ ዝሆኔ ፣የዉሻ በሽታ፣የቆዳ በሽታ ፣የእንቅልፍ በሽታ፣ የአይነማዝ እና ሌሎችም የአይን ብርሃን የሚያሳጡና ለሞት የሚዳርጉ የሞቃታማ አካባቢ በሽታወችን መከላከል ይቻላል። ይሁን አንጅ በሽታወቹን ለመከላከል ትኩረት ባለመሰጠቱ በአህጉሪቱ በየአመቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለሞት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ለአካል ጉዳት አየተዳረጉ መሆናቸዉ ነዉ የተገለፀዉ። 
በተለይ በወንዞች አካባቢ በሚገኙ ጥቋቁር ዝንቦች አማካኝነት በሚከሰተዉና የአይን በርሃንን በሚያሳጣዉ በሽታ በአፍሪካ ወደ 26 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች መጠቃታቸዉ ተገልጿል።  
እንደ አለም ባንክ ዘገባ ደገሞ እነዚህ በሽታወች የሚያመጡት ጉዳት 50 በመቶዉ  አፍሪካ ላይ የወደቀ ነዉ ።ከዚህ ዉስጥም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አትዮጵያና ናይጀሪያ 39 በመቶዉን አንደሚይዙ ተጠቅሷል።
ድህነትንና ኋላ ቀርነትን በአህጉሪቱ በማባባስ ረገድ በሽታወቹ የሚያሳድሩት ጫና ቀላል ባለመሆኑ  መንግስታት ተገቢዉን ትኩረት ሰጥተዉ መጣር ይገባቸዋል ሲሉ ዶከተር ሞየቲ ያሳስባሉ።
«ልብካላችሁአቸዉ አብዛኛወቹ  በሽታወች የማይድኑና የእድሜ ልክ ችግር የሚያመጡ በመሆናቸዉ ከፍተኛ ጫና ያሳድራሉ።ተመልከቱ የዓይን ብርሃንን የሚያሳጣዉ በሽታ ለም በሆኑና ለግብርና ምርት በጣም አስፈላጊ በሆኑ ቦታወች ያሉ  ሰወችን  ነዉ የሚያጠቃዉ ።   የግብርና ምርት አሁንም ድረስ ለአፍሪቃ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ነዉ። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸዉን  ሰዎች ህይወት በተመለከተ፣ እነዚህ ትኩረት ያልተሰጣቸዉ የሞቃታማ አካባቢ በሽታወች የሚያሳድሩት  ጫና ቀላል አይደለም።
የአፍሪቃ መንግስታት አቅማቸዉንና ሃብቶቻቸዉን በሽታወቹን በመከላክልና በመቆጣጠር ላይ ቢያዉሉ ችግሩን በመፍታት ረገድ ዉጤታማ ስራ ሊሰሩ ይችላሉም ተብሏል። የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለዚህ ስራ  ድጋፍ ይቸራል ሲሉም ተጠሪዋ አብራርተዋል።
« እንደማስበዉ ፤እነዚህ በሽታወች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ  በተለዬ ሁኔታ  ሳቢ የሚያደርገዉ  አገሮች ሀብቶቻቸዉንና አቅማቸዉን   ለዚሁ ስራ ካዋሉና  በርትተዉ  ከሰሩ  በሽታወቹን ማስወገድ የሚቻል መሆኑ ነዉ።በአሁኑ ጊዜ   አንዳንድ  በሽታዎችን   ለማጥፋት ከአለም አቀፉ ህብረሰብ  ዘንድ  ድጋፍ የማቅረብ  ትልቅ  ፍላጎት ስላለ   አብሮ  መስራትም ይቻላል።»
መንግስታቱ አብዛኛዉን የሀገር ዉስጥ በጀት መከላከል ላይ ቢያዉሉት በበሽታወቹ ሳቢያ የሚወጣዉን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ  ማስቀረት እንደሚቻልም ይመክራሉ።
«እሳቤዉ፤ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸዉ አገሮች  የዘላቂ ልማት ግቦችን መስመር የሚከተሉ ከሆነ በአማካኝ  በነፍስ ወከፍ 28 ዶላር ለጤና አገልግሎት  ወጪ  ማድረግ ያስፈልጋቸዋል ። ይህን በማድረግ  የአካባቢዉ አገሮች ወደ 700 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገደማ ከብክነት ሊታደጉ ይችላሉ ።»

ባለፉት ጥቂቂት አመታት በአህጉሪቱ የጤና ችግር በመጠኑ ቀንሷል ቢባልም መድሃኒት ከሚያስፈልጋቸዉ ሰዎች ዉስጥ ግማሽ ያህሉ ብቻ ያገኛሉ ነዉ የተባለዉ። 

ንጹህ የመጠጥ ዉሃ፣ የተመጣጠነ ምግብ ፣የተሟላ መሰረተ ልማትና በሽታን መከላከል ላይ ያተኮረ መረጃና ትምህርት እጥረት አሁንም ድረስ የአህጉሪቱ ፈተናወች መሆናቸም ተመልክቷል።
ያም ሆኖ ግን አሉ ዶ ክተር ሞየቲ ፤መንግስታትና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጠንክረዉ ከሰሩ አፍሪቃንና ህዝቦቿን ከድህነትና በሽታ የማዉጣቱ ስራ ይሳካል።አለም አቀፉ የጤና ድርጅት በጎርጎሮሳዊዉ የዘመን ቀመር በ2020 አሳካዋለሁ ያለዉ 17 ዋናዋና የሞቃታማ አካባቢ በሽታወችን የማስወገድ ግብም እንዲሁ።

ፀሐይ ጫኔ /ኢማኑኤል ላንዲስ

አርያም ተክሌ

 

Audios and videos on the topic