የተባባሰው የየመን ሰብዓዊ ቀውስ | ዓለም | DW | 12.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የተባባሰው የየመን ሰብዓዊ ቀውስ

የመን ለዘመናት በዘለቀው የርስ በርስ ጦርነት ሰብዓዊ ቀውስ እየገጠማት መሆኑን ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታወቀ። በአገሪቱ የሚካሄደው የርስ በርስና ጦርነትና የምግብ እጥረት እንዲሁም የጤና ተቋማት መዳከም በበርካታ ንጹሃን ዜጎችን ስጋት ላይ መጣሉን ኮሚቴው አስታውቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:01
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:01 ደቂቃ

የተባባሰው የየመን ሰብዓዊ ቀውስ

የመን ስር እየሰደደ በመጣው ሰብዓዊ ቀውስና የርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በአስጊ ሁኔታው ውስጥ መሆኗን ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታውቋል። የመንን ለሶስት ቀናት የጎበኙት የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ፒተር ማውረር አገሪቱ የምትገኝበትን ሰብኦዊ ቀውስ ለመታደግ ምግብ፤መድሐኒትና ውሃ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ማቅረብ የሚቻልበት መንገድ እንዲፈለግ ጠይቀዋል። በየመን የተፋጠጡት ተፋላሚ ኃይላት በድርድር መፍትሄ እንዲፈልጉም አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሶስት ቀናት ጉብኝታቸው የየመን የጤና ተቋማት ያሉበትን ሁኔታ እና የገጠማቸውን ቀውስ ተመልከተው ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል።
«ወደ ሆስፒታል ስመጣ የድንገተኛ ክፍሉ ባዶ ነበር። ከ30 ደቆቃ በኋላ ስመለስ በፍንጥርጣሪ ቦምብ ፍንዳታ ክፉኛ የተጎዱ ሁለት ቁስለኞች ተመልክቻለሁ። የተገረፉ፤ በመንገድ ላይ የተጎተቱና ከፍተኛ ካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም አሉ። ይህ በርስ በርስ ጦርነቱ በየቀኑ ስቃይ የሚገጥማቸውን ሰዎች ለማገዝ ብዙ መስራት እንደሚኖርብን የሚጠቁም አሰቃቂ ሁናቴ ነው።»


የዓለም ጤና ድርጅት ባለፉት አምስት ወራት 4,345 ሰዎች ሲሞቱ ከ22,110 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቋል። በርስ በርስ ጦርነቱ ከ1.3 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በአገሪቱ የሚካሄደው ውጊያ እና በወደቦች ላይ የተጣለው ገደብ መድሃኒቶች ለማስገባትም ሆነ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ፈተና መሆኑን ፒተር ማውረር ተናግረዋል። የነዳጅ እጥረት በህክምና ተቋማት የሚገኙ ቁሳቁሶች ከስራ ውጪ እንዳደረጋቸውም ጠቁመዋል። በሰንዓ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ባልደረባ የሆኑት አድናን ሂዛም የየመን የጤና አገልግሎት ከውድቀት አፋፍ ደርሷል የሚል ስጋት አላቸው።
«ሁኔታው ሁሉ አሳሳቢ ቀውስ ነው። ከፍተኛ የምግብ፤መድሐኒት፤የመጠጥ ውሃና የነዳጅ እጥረት አለ። አብዛኞቹ የአገልግሎት አቅራቢ ተቋማት ከውድቀት አፋፍ ላይ ይገኛሉ። በተለይ የጤናው ዘርፍ። በመላ አገሪቱ ብዙ ሆስፒታሎች ሙሉ በሙሉ አሊያም በከፊል ወድመዋል። አሁን እየተካሄደ በሚገኘው የርስ በርስ ጦርነት ችግር የገጠማቸውና ከፍተኛ የምግብና የውሃ እርዳታ የሚሹ ሰዎች አሉ።»
«ይህ ሊቀጥል አይችልም። የመን እየፈራረሰች ነው፣» ያሉት የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ፒተር ማውረር የሰዎች እንቅስቃሴ ሊገደብ እንደማይገባ ተናግረዋል። ለየመን ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንደሚያሻም አጽንዖት ሰጥተው የተናገሩት ማውረር «ዓለም ሊነቃ ይገባል።» ባይ ናቸው። አድናን ሂዛም የፕሬዝዳንቱ ንግግር ለዓለም የቀረበ ጥሪ እንደሆነ ይናገራሉ።
«የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዓለም በየመናውያን ስቃይና መከራ ላይ እንዲነቃ ያቀረቡት ጥያቄ ለሁሉም የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶችና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የቀረበ ጥሪ ነው። ጥሪው በየመን ላይ ትኩረት እንዲደረግና አስፈላጊ የእርዳታ ቁሳቁስ በመላክና ለእውነተኛ የፖለቲካዊ መፍትሄ መንገድ በመፈለግ የየመን ዜጎችን መከራ ለማብቃት የቀረበ ነው።»


በየመን ቀውስ ከእርዳታ ባሻገር መፍትሄ ሊያመጣ የሚችለው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የፕሬዝዳንቱን ጥሪ በምን መንገድ እንደሚያደምጠው ለጊዜ አልታወቀም። እስከዚያው ግን የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በየመን ከሰማይ ቦምብ ያዘንባሉ። ዛሬ እንኳ በሰው አልባዎቹ አውሮፕላኖች ጥቃት የአልቃይዳ አባላት ሳይሆኑ አይቀሩም የተባሉ አምስት ታጣቂዎች መገደላቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። ሳዑዲ አረቢያ ከ 3,000 በላይ እግረኛ ወታደሮቿን ኤደን አዝምታለች። የስደተኛውን አብድራቦ ማንሱር ሐዲ ታማኞች እያስታጠቀችም ትገኛለች። በኢራን ይታገዛሉ የሚባሉት የሺዓ አማጽያን እስኪሸነፉም ድረስ የምታቆምም አይመስልም።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምግብ የማግኘት መብት ልዩ ልዑክ ሂላል ኤልቨር 12.9 ሚሊዮን ዜጎች መሰረታዊ የምግብ አቅርቦት ማጣታቸውንና ከእነዚህ መካከል 850,000 ህጻናት ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ተናግረዋል።
አነስተኛ ገበያዎችና የምግብ ማመላለሻ መኪኖች በአየር ጥቃቶች ዒላማ በመሆናቸው በኤደን፤አል-ዳሊ፤ላሃጅና ታዒዝ ለእርዳታ ፈላጊዎች ምግብ ማቅረብ አለመቻሉን ሮይተርስ ሂላል ኤልቨርን ጠቅሶ ዘግቧል።
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic