የተባባሰዉ የእስራኤል የፍልስጤም ግጭት | ዓለም | DW | 10.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የተባባሰዉ የእስራኤል የፍልስጤም ግጭት

የእስራኤል የጦር አዉሮፕላኖች በፍልስጤም ግዛት ጋዛ ላይ ዛሬ ደጋግመዉ ባደረሱት ድብደባ የተጎዱ ሲቪሎች ቁጥር መጨመሩን ዘገባዎች ያመለክታሉ። የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት እስራኤል ከሃማስ ጋ የገጠመችዉን ፍጥጫ ለመመልከት አስቸኳይ ስብሰባ ያደርጋል።

የፍልስጤም ፕሬዝደንት ማህሙድ አባስ እስራኤል ጋዛ ዉስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመች ነዉ ሲሉ ከሰዋል። እስራኤል ግን ድብደባዉን የምታቆም አይመስልም። የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ እስራኤልና ሃማስ ከጥቃት እንዲታቀቡ ጠይቀዋል። የተኩስ አቁም እንዲደረግ ዓለም ዓቀፍ ግፊት ቢኖርም ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔትንያሁ ሃማስ ላይ ጠንካራ ርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል። እስካሁን የእስራኤል ወገን የጠፋ ህይወት ስለመኖሩ የተሰማ ነገር የለም። ሃማስ ኢየሩሳሌም፣ ቴልአቪቭን ጨምሮ ወደተለያዩ የእስራኤል ከተሞች ሮኬቶችን ማስወንጨፉን አጠናክሯል።

የአደጋ ማስጠንቀቂያዉ ደዉል ሲሰማ ሁሉም መሸሸጊያ ፍለጋ ይሮጣል። ከጋዛ እስከ ቴልአቪቭ እስራኤላዉያንም ሆኑ ፍልስጤማዉያን ከሁለቱም ወገን ከሚወነጨፍ አረር ለማምለጥ። በዚህ ምክንያትም ቴልአቪቭ ከተማ ለወትሮዉ በሰዎች የሚጨናነቁ አካባቢዎች ጭር ማለታቸዉን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ከስፍራዉ ዘግቧል። ጋዛ ዉስጥ የዓለም ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ለመመልከት በአንድ ቡና መጠጫ ቤት ከተሰበሰቡ ስምንቱ በእስራኤል የአየር ጥቃት ሲገደሉ 15 ተጎድተዋል። የእስራኤል ታንኮች በሁለቱ ግዛቶች መለያ ድንበር አካባቢ እየተርመሰመሱ በሚታዩበት በዚህ ወቅትም ጠ/ሚ ቤንያሚን ኔትንያሁ ከመንግስታቸዉ ጋ ከተጣመሩት ወግ አጥባቂ ኃይሎች ግፊቱ አይሎባቸዋል። ወትሮ እንደነበረዉ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል በአካባቢዉ እንዲያሰማሩ።

ሁኔታዉ በአካባቢዉ እየተባባሰ መምጣቱን ያስተዋሉም የመካከለኛዉ ምሥራቅ የሰላም ተስፋ መጥፋቱን በማሳሰብ ላይ ናቸዉ። የእስራኤል ጥቃት ያሰጋቸዉ ወገኖች የእስራኤል ርምጃ የፍልስጤሞችን ሶስተኛ ኢንቲፋዳህ/ሕዝባዊ አመፅ/ ይቀሰቅስ ይሆን በማለት ጠይቃሉ። በበርሊን የፍልስጤም አምባሳደር ኮሁሉድ ዳይበስ አሁን ጎልቶ የወጣዉ ግጭትና ጥቃት ለጋዛ የየዕለት ኑሮ ነዉ ይላሉ፤

«በወረራ በተያዘ አካባቢ በየዕለቱ የሚፈፀም አረመኔያዊ እና ጋዛ የሚገኝ ህዝባችን ላይ የተከፈተ ጦርነት ነዉ። ባለፉት ቀናት ደግሞ እየተጠናረ መጥቷል፤ ሆኖም ግን ፍልስጤም በእስራኤል ስር እስካለች ድረስ በየቀኑ የሚከሰት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ሰብዓዊነት መራቁ፣ መብቶች መገፈፋቸዉ፣ እንዲሁም የጋዛ ወረራና የድርድሩ መሰናከል ይህን አመፅ አስከትሏል።»

እስራኤል ከትናንት ማምሻ ጀምሮ ጋዛ ላይ ባደገችዉ የአየር ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሃማስ ይዞታዎችን ደብድባለች። የእስራኤል ጦር ኃይል ቃል አቀባይ ሌተናል ኮሌነል ፒተር ለርነር ዒላማ መሬት ዉስጥ ያሉ መተላለፊያዎች እና ሮኬት ማስወንጨፊያ ቦታዎች መሆናቸዉን ገልጸዋል። ዛሬን ጨምሮ ባለፉት ሶስት ቀናት ከ700 በላይ የታለሙ ቦታዎች መደብደባቸዉን፤ በጥቃቱም 80 ፍልስጤማዉያን መገደላቸዉን አሶሴትድ ፕረስ ዘግቧል። ቃል አቀባዩ ለምናልባቱ እስራኤል 20 ሺህ እግረኛ ሠራዊት ወደአካባቢዉ ማንቀሳቀሷንም አመልክተዋል። እንዲያም ሆኖ እስራኤል ለጊዜዉ ግን የአየር ጥቃቷን እንደምታጠናክር ነዉ የተገለጸዉ። በተመድ የፍልስጤም ልዑክ ሪያድ ማንሱር የፀጥታዉ ምክርት ቤት መፍትሄ ለመፈለግ ባስቸኳይ እንዲሰበሰብ ጥሪ አቅርበዋል። ጋዛ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ የገለፁት የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ጊ ሙን ችግሩ ተባብሶም በፍጥነት ከቁጥጥር ዉጭ እንዳይሆን አሳስበዋል። ጋዛም ሆነች አካባቢዉ ከእንግዲህ ሌላ መዘዝ የሚያስከትል ጦርነት ለማስተናገድ አቅሙ እንደማይኖራቸዉም አስገንዝበዋል።

«ምስራቅ ኢየሩሳሌምን ጨምሮ፤ ጋዛን፣ ደቡባዊ እስራኤልና የዮርዳኖስ ወንዝን ምዕራባዊ ዳርቻ አካባቢ ያስጨነቀ አዲስ ተከታታይ ጥቃት መኖሩን ሰምቻለሁ፤ ይህ አካባቢዉ በቅርቡ ከገጠሙት እጅግ አሳሳቢ ፈተናዎች አንዱ ነዉ። እናም በድጋሚ በተደጋጋሚ ከጋዛ ወደእስራኤል የሚደረገዉን የሮኬት ጥቃት አዉግዣለሁ፤ እንዲህ ያለዉ ጥቃት ተቀባይነት የለዉምና መቆም አለበት። ጠቅላይ ሚኒትር ኔትንያሁም ከፍተኛ አደብ በመግዛት ሲቪሎችን የመከላከል ዓለም ዓቀፍ ግዴታቸዉን እንዲወጡ እማፀናለሁ።»

የኃይል ርምጃዉ ጋዛን እንደተቆጣጠረ ከሚነገርለት ሃማስ ወገን መጀመሩን ያመለከተችዉ ዩናይትድ ስቴትስ እስራኤል በምትሰነዝረዉ አፀፋ ሲቪሎችን እንዳይጎዳ ግጭቱ እንዲበርድ ለማደረግ እንደምትጥር የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጃን ፓሳኪ ገልጸዋል፤

«እርግጥ ነዉ፤ ማንኛዉም ሀገር ከአሸባሪዎች ድርጅቶች በሚሰነዘር የሮኬት ጥቃት ንፁሃን ሰላማዊ ዜጎች እየተጎዱ እጁን አጣምሮ እንዲቀመጥ አይጠበቅበትም። ሆኖም ግን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋ እንደተናገሩት ሁለቱም ወገኖች ግጭቱን እንዲያበርዱ እያበረታቱ ነዉ፤ ሲቪሎችም ሲጎዱ ማየት አንፈልግም። እናም በቦታዉ የሚታየዉ ሁኔታ እንዲበርድ ከምናደርግባቸዉ ምክንያቶች ዋነኛዉም ይህ ነዉ።»

እንዲያም ሆኖ ከእስራኤል የሚወጡ ዘገባዎች ሁለቱም ወገኖች ከኃይል ርምጃቸዉ የመታቀብ ምንም ፍንጭ አለማሳየታቸን ያመለክታሉ። እስራኤልና ፍልስጤም በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012 ዓ,ም በተመሳሳይ ለ8 ተከታታይ ቀናት ተዋግተዋል።ይህ በእንዲህ እንዳለም እስራኤል ዉስጥ በሚታየዉ የግጭትና ጥቃት ምክንያት አንድ የጀርመን አገር አስጎብኚ ድርጅት ወደዚያ የሚደረጉ ጉዞዎቹን እስከሐምሌ ወር ማለቂያ ድረስ መሠረዙን አመልክቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic