የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድና ዕጣው | ኤኮኖሚ | DW | 29.11.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድና ዕጣው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልማትን በማራመድ ድህነትን በከፊል መቀነሱን የሚሌኒየም ግቡ አድርጎ ካወጀ ከስድሥት ዓመታት በኋላ ዛሬ በየጊዜው የተገባው ቃል ሁሉ ገቢር አለመሆኑ ጎልቶ የሚታይ ሃቅ ነው። ለብዙዎች የማይደረሰበት ግብ ይሆን?

ኮፊ አናን

ኮፊ አናን

በቅርቡ ከድርጅቱ ዋና ጸሐፊነት ሥልጣን የሚሰናበቱት ኮፊ አናን ሰሞኑን በጠቅላይ ጉባዔው ላይ ሲናገሩ ልንደርስበት ካሰብነው ግብ ገና ብዙ ርቀን ነው የምንገኘው፤ የልማት መሠረት ከመጣል ባሻገር የበለጠ ያደረግነው ነገር የለም ብለዋል። ጉዳዩ የበለጠ ጥረትን የሚጠይቅ መሆኑ ነው። ከስድሥት ዓመታት በፊት ገሃድ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድ እስከ 2015 ድረስ ድህነትና ረሃብን በከፊል መቀነስ፤ ትምሕርት ለሁሉ እንዲዳረስ ማድረግ፤ በዓለም ላይ በአጭር የሚቀጩትን ሕጻናት በሁለት ሶሥተኛ መቀነስና ኤይድስን የመሳሰሉ ገዳይ በሽታዎችን መቋቋምን የመሰሉትን ግቡ ያደረገ ነው። ሆኖም እስካሁን የታየው ሂደት ዕቅዱ በተጣለው የጊዜ ገደብ ገቢር ይሆናል የሚል ተሥፋን የሚያዳብር አይደለም።

ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናንና ሌሎች ታዛቢዎች በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላይ ጉባዔ ላይ እንደተናገሩት በወቅቱ ዕቅዱን በተሟላ ሁኔታ በጊዜው ማጠናቀቅ በሚያስችል ጎዳና የሚያመራ አንድም የዓለም አካባቢ አይገኝም። እስካሁን የተገኘው ዕድገት ከፊል፤ ወይም በአንድ አካባቢ ብቻ የተወሰነ ነው። ድህነትን በመቀነሱ በኩል የምሥራቃዊው እሢያ አገሮች ተገቢውን ዕርምጃ ሲያደርጉ በአንጻሩ በደቡባዊው እሢያ ይህን መሰሉ ለውጥ ጠርቶ አይታይም። በላቲን አሜሪካም ዕርምጃው በጥቂት አካባቢዎች ብቻ የተወሰነ ነው።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት ዛሬ በዓለም ላይ ከአንድ ቢሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ከአንዲት ዶላር ባነሰች የቀን ገቢ ነው የዕለት ከዕለት ኑሮውን የሚገፋው። ሌላ 2,7 ቢሊዮን ሕዝብ ደግሞ ከሁለት ዶላር ዝቅ ባለ የዕለት ገቢ ይተዳደራል። ሌላው አስከፊ ሃቅ በያመቱ ፈውስ ሊገኝላቸው በሚችል ወባንና ተቅማጥን በመሳሰሉ በሽታዎች በያመቱ 11 ሚሊዮን ሕጻናት የሚያልቁ መሆናቸው ነው። ይህ ሁሉ የሚሌኒየሙን ዕቅድ ገቢር በማድረጉ በኩል ችግሩን የበለጠ ያጠነክረዋል።

ለተባበሩት መንግሥታት የልማት ጉዳይ ባለሥልጣናት ይበልጥ አሳሳቢ ሆኖ የሚገኘው ደግሞ፤ በተለይ ከሚሌኒየሙ ሥምንት ግቦች በየትኛውም አቅጣጫ ዕርምጃ የማይታይበት ከሣሃራ በስተደቡብ ያለው የአፍሪቃ ክፍል ሁኔታ ነው። የድርጅቱ የልማት ዕቅድ ባለሥልጣን ከማል ደርቪስ እንዳሉት በአፍሪቃ ዕቅዱን ዕውን ማድረጉ ከሌሎች የዓለም አካባቢዎች ሲነጻጸር የበለጠ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ምንም እንኳ ባለፉት ዓመታት አጠቃላይ የኤኮኖሚ ዕድገት መታየቱ ባይቀርም በመንግሥታት መካከልና በውስጣቸውም ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ ሌላው ሃቅ ነው። ለዚያውም ይህ በወቅቱ ይታያል የሚባለው የአፍሪቃ ዕድገት የብዙሃኑን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻሉ ረገድ ይህ ነው የሚባል አስተዋጽኦ ባለማድረጉ ዕድገት ተብሎ መጠራቱ ራሱ በኤኮኖሚ ጠበብት ዘንድ ብዙ ማከራከር መያዙ አልቀረም።

ተጨባጩ ሃቅ ሃብታሙ ይበልጥ ሃብታም፤ ድሃው የባሰ ድሃ መሆኑን መቀጠሉ ነው። በበለጸገው ሰሜናዊ የዓለም ክፍልና በታዳጊው ደቡብ መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ እየሰፋ ነው የመጣው። ዓለም የሁለት የተለያዩ ክፍለ-ዘመናት ገጽታ ነጸብራቅ ሆና ቀጥላለች። ከ 19ኛው ክፍለ-ዘመን የኢንዱስትሪ ዓብዮት ወዲህ ቀደምቱ አሥር የዓለም ሃብታም መንግሥታት ከዝቅተኞቹ አሥር አገሮች ሲነጻጸር በሃምሣ ዕጅ በሚበልጥ መጠን ነው ያደጉት። ይህ እጅግ ትልቅ ልዩነት ነው፤ የፍትሃዊ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ሥርዓትን አስፈላጊነትንም አጣዳፊ ጉዳይ ያደርጋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን የበለጸጉት አገሮች የሚሌኒየሙን ዕቅድ ከግቡ ለማድረስ የገቡትን ቃል ዕውን ሳያደርጉ በመቅረታችው አጥብቀው ነው የወቀሱት። እርግጥ ታዳጊ አገሮችም ግዴታቸውን መወጣት አለባችው ባይ ናቸው። አናን እንዳስገነዘቡት ታዳጊዎቹ አገሮች የገዛ ቤታቸውን ለማስተካከል እስካልተነሱ ድረስ ልማት ዝም ብሎ ሊመጣ የሚችል ነገር አይደለም። ይህ ደግሞ በጎ አስተዳደርን፣ ፍትሃዊ ማሕበራዊ ሥርዓትን ማስፈን ማለት ሲሆን የአፍሪቃ የልማት ችግር በተለይ ጎልቶ የሚታየው በዚህ መስክ ነው።

ለነገሩ ብዙዎች የበለጸጉ መንግሥታት ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው 0,7 ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ ለልማት ዕርዳታ ለማዋል ቃል ከገቡ አሠርተ-ዓመታት አልፈዋል። ግን ጥቂቶቹ ናቸው ቃልን ወደ ተግባር ተርጉመው የሚገኙት። ሆኖም የወቅቱ የበለጸገው ዓለም ይፋ የልማት ዕርዳታ የሚሌኒየሙን ዕቅድ ከግቡ ለማድረስ አያብቃ እንጂ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት እንደሚሉት አንዳንድ አበረታች ዕርምጃዎች መታየታችው አልቀረም። የድርጅቱ ጠቅላይ ጉባዔ ፕሬዚደንት ራሼድ-አል-ካሊፋ ሁኔታውን ሲያስረዱ እርግጥ ድህነትን ያለፈ ታሪክ ለማድረግ አልበቃንም። ግን እየተራመድን ነው ብለዋል።

የበለጸጉት መንግሥታት የልማት ዕርዳታ በወቅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ መቶ ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነው የሚገኘው። በቅርቡም አበዳሪ መንግሥታት እስከ 2010 ዓ.,ም. ተጨማሪ 50 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ ለማቅረብ ተስማምተዋል። ከዚህም 25 ቢሊዮኑ የተመደበው ለአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ነው። ሃያ ገደማ ለሚጠጉ የድሃ-ድሃ ለሚባሉ አገሮች 81 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚጠጋ የዕዳ ስረዛ ማድረጋቸውም ይታወቃል። ባለፈው ሰኞ ደግሞ ሳውዲት አረቢያ ላይ ተቀማጭ የሆነው Islamic Development Bank የተሰኘው የእሥላም አገሮች የልማት ባንክ በአሥር ቢሊዮን ዶላር መነሻ የድህነት መቀነሻ ተግባር ፕሮዤ ለማቆም መዘጋጀቱን አስታውቋል።

በባንኩ ተግባር ምክትል ፕሬዚደንቱ የኒጀሩ ተወላጅ አማዱ-ቡባካር-ሢሤ እንዳሉት አሁን ከወዲሁ ከ 56ቱ የባንኩ ዓባል መንግሥታት ዕርዳታው ይበልጥ በሚያስፈልጋቸው አገሮች ለሚካሄዱ መሠረታዊ የማሕበራዊ አገልግሎት ፕሮዤዎች ሶሥት ቢሊዮን ዶላር ተመድቦ እየሰራ ነው። ዓላማው ኋላ የቀሩት አገሮች፤ ከነዚሁ መካከል ለምሳሌ ሤኔጋልን፣ ኒጀርንና ማሊን የመሳሰሉት ይገኙበታል፤ የሚሌኒየሙን ዕቅድ ከግቡ እንዲያደርሱ መደገፍ ይሆናል። የባንኩ ጥረት በውጭ ዕርዳታ ላይ ጥገና ሣይሆን የራሱን የልማት ችግር በራሱ ለመፍታት የተወጠነ ሲሆን ፕሮዤዎቹ ከአፍሪቃ ባሻገር፤ መካከለኛ ምሥራቅንና የቀድሞ የሶቪየት እሢያ ሬፑብሊኮችን ጭምር የሚጠቀልል ነው።
የዕርዳታው ዕቅድ ገሃድ የሆነው ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ሳውዲት አረቢያ ውስጥ በተካሄደ የእሥላም መንግሥታት ድርጅት የመሪዎች ጉባዔ ላይ እንደነበር ይታወሣል። የግሉ ኤኮኖሚ ዘርፍ አስተዋጽኦም የሚሌኒየሙን ዕቅድ ከግቡ በማድረሱ በኩል ክብደት እየተሰጠው የመጣ ጉዳይ ነው። ከእሥላማዊው ባንክ ሌላ ለምሣሌ የሶሮስ በጎ አድራጎት ድርጅት ባለቤት ጆርጅ ሶሮስንና የኩዌይትን የኤኮኖሚ ልማት የዕርዳታ ተቋም የበላይ ሂሻም አልዉጋያንን የመሳሰሉ ዓለምአቀፉን የልማት ጥረት ለማጠናከር የተነሱ ወገኖች ይገኙበታል። በተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት አባባል የግሉ ዘርፍ አስተዋጽኦ ወሣኝ ደረጃ እየደረሰ በመሄድ ላይ ነው። የጠቅላይ ጉባዔው ፕሬዚደንት ራሺድ-አል-ካሊፋ እንዳሉት የግሉ ዘርፍ ድርጅቶች ባለፈው አሠርተ-ዓመት በዓለምአቀፍ ደረጃ ልማትን በማራመዱ በኩል ጠቃሚ ሃይል እየሆኑ መጥተዋል።