የተሻሻለዉ የኢትዮጵያ የባህል ፓሊሲ | ባህል | DW | 28.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የተሻሻለዉ የኢትዮጵያ የባህል ፓሊሲ

የብዙ ባህልና ቋንቋ ባለቤት የሆነችዉ ኢትዮጵያ ከ 1990 ዓ/ም ጀምሮ የባህል ፓሊሲ ቀርጻ ስትሰራ ቆይታ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህ ፖሊሲ የባህል እንዱስትሪንና ሌሎች ያላካተታቸዉ ጉዳዮች አሉ በሚል የሀገሪቱ የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር ማሻሻያ ማድረጉን አመልክቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:19
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
13:19 ደቂቃ

« ባህልን የህዝቦች የግንኑነት ማጠናከሪያ በማድረግ ረገድ እጥረት ነበረ »ኢትዮጵያ የብዙ ብሄርና ብሄረሰቦች ፣የባህላዊ እሴቶች፣ የጥንታዊ የቋንቋና የታሪክ ባለቤት መሆኗን መረጃወች ያመለክታሉ።በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የተመዘገቡ የዘጠኝ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤትም ነች።
ኢትዮጵያ በየማህበረሰቡ የሚከወኑ ቀደምት ባህላዊ እሴቶችና ትዉፊቶች ፣ የሥነ- ፅሁፍ ፣የኪነ- ህንፃ ፣የሙዚቃ ና ሌሎች የኪነ-ጥበብ ስራወች መገኛ ጭምር ነች።  ለዚህም ይመስላል ሀገሪቱ በአንዳንድ የታሪክና የባህል ተመራማሪወች ዘንድ « የባህል ሙዚየም» የምትባለዉ።በዛሬዉ የባህል መድረክ ዝግጅታችን እነዚህን ባህላዊ እሴቶች የሚመለከተዉን የሀገሪቱን  የባህል ፓሊሲ እንቃኛለን ።
በኢትጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ድረ-ገፅ ያገኘነዉ የባህል ፓሊሲ ሰነድ  እንደሚያትተዉ ባህል በኢትዮጵያ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሚያከናዉኑት የማህበራዊ ፣የኢኮኖሚያዊ ና የፓለቲካዊ አስተዳደር፣ የሥነ-ምግባር፣የስነ-ልቡና ሁኔታወች፣የቋንቋ፣የታሪክ፣የስነ-ቃል፣የምግብ አዘገጃጀት ፣የአመጋገብ ስርዓት ፣ቤት አሰራር፣ አልባሳት የጥበብ ዋጋወችና አድናቆት፣ጌጣጌጦች፣ባህላዊ እምነቶች፣ ሀይማኖቶችና ሌሎችም እሴቶች  የህዝቦች የባህል አካል ተደርገዉ ይወሰዳሉ። 

ባህል ከወሊድ ከጋብቻና ከሞት ጋር የተያያዙ ስነ ስርዓቶችና ጉርብትናን የመሳሰሉ ማህበራዊ የትብብር መርሆወች ፣ባህላዊ የጤና አጠባበቅ ዘዴወች ባህላዊ የማህበረሰብ አስተዳደሮችና ሌሎች የማህበረሰብ ገፅታወችንም  ይጨምራል።በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፎክሎር ትምህርት ክፍል የዶክትሬት ዲግሪያቸዉን እየተከታተሉ የሚገኙትና« ፎክሎርና የጥናቱ አቅጣጫ» መጽሃፍ ደራሲ  አቶ ሶሎሞን ተሾመ ባህልን በአጭሩ እንዲህ ያስቀምጡታል።«  በአጠቃላይ ባህል ስንል ማህበረሰቡ የኔ የሚለዉ እና ማንነቱን የሚገልፅበት ቁሳዊ፣መንፈሳዊና ቃላዊ ሀብቶቹ ናቸዉ»

በዚህ መሰረት የተረትና አፈታሪክን የሚያጠቃልለዉ የቃላዊ ሀብት፣እደጥበብን፣ኪነ-ህንፃን፣ አልባሳትን፣ምግብና መጠጥን  የሚያጠቃልለዉ ቁሳዊ ባህል፣ሙዚቃን፣ዉዝዋዜንና ድራማወችን የሚያጠቃልለዉ ሀገራዊ ክዋኔ ዘርፍ፣ክብረ በዓላትንና የህይወት ዑደትን የሚያካትተዉ ሀገረሰባዊ ልማድ ፣የቁጥሮችን፣የቀለሞችንና የምልክቶችን ትርጓሜና አንድምታ የሚመለከተዉ ማህበረሰባዊ ዉክልና እንዲሁም የእርቅ ፣የአዉጫችኝና የገዳ ስርዓቶችን በስሩ የሚያካትተዉ ማህበረ ፓለቲካዊ ባህሎች በሚል  የዘርፉ ሙህራን  በስድስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፍሏቸዋል።
ይህንን ዘርፍ ለማበረታታትና ለመደገፍ  ሀገራት የባህል ፓሊሲ ቀርፀዉ ይተግብራሉ። ይህንን ፓሊሲ የአንድን ሀገር የኪነ ጥበብ ስራወችና በባህል ዉስጥ ያሉና ከፈጠራ ዉጤቶች ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴወችን ለመቆጣጠር ለመጠበቅ፣ ለማበረታት፣  በገንዘብም ሆነ በሀሳብ ለመደገፍ  ያዉሉታል። ለመሆኑ የባህል ፓሊሲ ምን ማለት ነዉ? አቶ ሰሎሞን ተሾመ።
«የባህል ፖሊሲ ማለት በባህል ጉዳዮች  ዙሪያ የሚሰራና ባህልን መሰረት ያደረገ ህጋዊ እዉቅና ያለዉ ሀገር አቀፍ ማዕቀፍ ነዉ»
በኢትዮጵያ  ባህልን በተመለከተ የተደራጀ ፓሊሲ የተዘጋጀዉ በ 1990 ዓ/ም ጀምሮ ቢሆንም በንጉሱ ዘመን ባህልን የሚመለከቱ አስተዳድራዊ መዋቅሮች በትምህርትና በመገናኛ ሚኒስቴር ስር እንደነበሩ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት በጎርጎሮሳዊዉ 1982 ዓ/ም የቅድመና ድህረ አብዮት ኢትዮጵያን ባህል በቃኝበት  ጥናታዊ ፅሁፍ አመልክቷል።  በደርግ ዘመንም ሶሻሊስታዊ  የባህል ግንባታን በሚያበረታታ መልኩ  የባህልና ስፓርት ሚንስቴር ከነሀሴ  1977 ዓ/ም ጀምሮ  ኢህአዲግ ሀገሪቱን እስከተቆጣጠረበት ጊዜ ድረስ  ይህንን ዘርፍ ሲመራ መቆየቱን ዩኒስኮ በዚሁ ፅሁፍ አስቀምጧል።


የኢትዮጵያ የባህል ፓሊሲ  የፌደራል መንግስት ፓሊሲወችን እንዲያወጣ በሀገሪቱ ህገ መንግስት በተሰጠዉ ስልጣን መሰረት የተቀረፀ ሲሆን   ከ1990 ዓ/ም ጀምሮ ሲሰራበት ቆይቷል። ይህ ፓሊሲ  ጥናት ተደርጎበት  ከታህሳስ 2008 ዓ/ም ጀምሮ  ማሻሻያ እየተካሄደበት መሆኑን ከኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ምኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።በሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የባህል ኢንደስትሪ ልማት ዳይሬክተር አቶ ደስታ ካሳ እንደሚሉትች የቀደመዉ ፖሊሲ በርካታ የባህል ጉዳዮች የተካተቱበት ቢሆንም የባህል ኢንዱስትሪ ልማትንና ሌሎች ጉዳዮችን  ያላካተተ በመሆኑ ማሻሻል አስፈልጓል። 
የተሻሻለዉ  ፓሊሲ የማስፈፀሚያ ስልቶቹም ቢሆኑ በግልፅ የተቀመጡ አልነበሩም።ባህልን የህዝቦች ግንኙነትና ትስስርን ማጠናከሪያ  በማድረግ ረገድም  እጥረት የነበረበት ሲሆን ማህበረሰቡ በኑሮ ሂደት ለፈጠራቸዉ ሀገር በቀል እዉቀቶች ትኩረት የሰጠ አልነበረም ሲሉ አቶ ደስታ ካሳ ገልፀዋል።
ከዛሬ 20 ዓመት በፊት  የቀደመዉ የባህል ፖሊሲ ሲወጣ በሀገሪቱ የነበሩ ነባራዊ ሁኔታዎችና  የዓለም ዓቀፍ ሁኔታ እንዲሁም ባህልን ለኢኮኖሚ ግንባታ ማዋል የሚለዉ አስተሳሰብ የቅርብ ጊዜ በመሆኑ እነዚህን ጉዳዮች በቀደመዉ ፖሊሲ ማካተት አልተቻለም ነበር ብለዋል።
የአዉሮፓ ሀገራት፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የሩቅ ምስራቅ ኤዥያ፣ የደቡብ ኮርያና የሌሎች ሀገሮች ልምድ በተቀመረበት በዚህ የባህል ፓሊሲ የከተማ ልማትና የስነ-ህንፃ ስራወችም ዘመናዊ መንገድን ተከትለዉ የሀገሪቱን ባህል በሚያነፀባርቅ ሁኔታ እንዲገነቡ ጥረት እንደሚደረግ ተገልጿል። የባህል ልማት ስራ በአንድ ዘርፍ ብቻ የታጠረና በአንድ ምንስቴር መስሪያ ቤት ብቻ የሚሰራ አይደለም የሚሉት አቶ ደስታ በባህሉ የመጡ እዉቀቶችን ለማስተላለፍና ባህሉን የኢኮኖሚ አጋዥ ለማድረግ በባህል ዙሪያ  ስልጠናወችን መስጠት የተሻሻለዉ የባህል ፓሊሲ አንድ የትኩረት አቅጣጫ  ተደርጓል።


የባህል ዘርፍን ለማበረታት በመንግስት በኩል የሚወሰዱ አንዳንድ ርምጃወች ቢኖሩም  እነዚህ ርምጃወች በተወሰኑና ስፋት በሌላቸዉ ባህላዊ ተቋማትን በማደራጀት  ብቻ ተወስኖ እንደሚታይ  የባህል ባለሙያወች ይተቻሉ።  በዚህም የተነሳ  ማህበራዊ ፣ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ይዞታ ያላቸዉ ዘመናዊ የባህል ተቋማትና ድርጅቶችን በሀገሪቱ ማፍራት አልተቻለም ።የተለያዩ ዘርፎች ስለ ባህል ያላቸዉ ግንዛቤ አነስተኛ መሆንና ለዘርፉ የተሰጠዉ ትኩረት አነስተኛ መሆንም  በአንዳንዶች ዘንድ የሚነሳ ወቀሳ ነዉ።ይህ ችግር የባህል ዘርፉ የሚገባዉን ድርሻ እንዳያበረክት እንቅፋት መፍጠሩ ይነገራል።
በሌላ በኩል ባህላዊ እሴቶችን የሚያከብርና የሚጠብቅ ፣በማንነቱ የሚኮራ ትዉልድ ለማፍራትና ሀገርንና ማንነትን የሚያሳጡ የባህል ወረራወችን ለመከላከል ትምህርት ቤቶች፣የባህሉ ባለቤቶች፣የእምነት ተቋማት በዋናነት ደግሞ የሚመለከታቸዉ የመንግስት አካላት ርብርብ ወሳኝ ይመስላል።ያ ከልሆነ ግን የባህል ፓሊሲ መመሪያወችንና የአፈፃጸም አቅጣጫወችን ከማዉጣት የዘለለ ፋይዳ ሊኖረዉ  አይችልም የሚለዉ  የበርካቶች  ስጋት ነዉ።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ መዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ

 

Audios and videos on the topic