የተረጂዎች ማዕከል እና በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች | ባህል | DW | 28.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የተረጂዎች ማዕከል እና በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች

የወጣቶቹ አላማ ጧሪ የሌላቸውን፣ ከጎዳና ላይ የተነሱ አረጋውያንንና የአዕምሮ ህሙማንን መርዳት ነው። ለዚህ ደግሞ 65 በጎ ፍቃደኞች አዲስ አበባ የሚገኘው «ሜቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከልን ተቀላቅለዋል።ሶስቱን አነጋግረናቸዋል።

ከጓደኞች ጋር መገናኘት፣ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ ፊልም መመልከት ሥፖርት መስራት እና መዝናናት በርካታ ወጣቶች የሚመርጡት ነው። በተለይ እንደ አዲስ አበባ ባለ ትልቅ ከተማ የሚኖሩ ወጣቶች ትርፍ ጊዜያቸውን የሚያጠፉበት ቦታዎች አያጡም። የዛሬ እንግዶቻችን ግን ከመዝናናት ይልቅ በበጎ አድራጎት ስራ ላይ ጊዜያቸውን ቢያሳልፉ ይመርጣሉ። ይህም በሜቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ውስጥ ነው።

ከእነዚህ አንዷ የ25 ዓመቷ ኤልሳቤጥ ናት። ኤልሳቤጥ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች በግል ሥራ ተሰማርታ ትሠራ ነበር። ነገር ግን ይህ የበጎ አድራጎት ስራ የበለጠ እርካታ ሰጥቷታል። ኤልሳቤጥ ለማዕከሉ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ታስፈፅማለች። ወጣቷ አልፎ አልፎ ተረጂዎቹ ከሚገኙበት ወጣ ብላ ብትሰራም ከአረጋውያኑ እና የዓዕምሮ ህሙማኑ ጋር በየቀኑ ትገናኛለች።

ሌላው ወጣት ማሞ ታደሰ ይባላል። ማዕከሉን የተቀላቀለው በ27 ዓመቱ ነው። ከዛን ጊዜ ጀምሮ በየጎዳናው ያሉ ተረጂዎችን እያሰባሰበ ወደ ማዕከሉ ያመጣል። ቢንያም በለጠ ደግሞ ይህንን ማዕከል ያቋቋመው ነው። እኔ አቋቋምኩ ከማለት ይልቅ እኛ ማለቱን ይመርጣል። ቢንያም ሰውን መርዳት ከ8ኛ ክፍል ጀምሮ ይመኘው የነበረው ነው።የ37 ዓመቱ ጎልማሳ፤ አሜሪካ ለ7 ዓመታት ኖሯል። ወላጆቹን ጨምሮ እህት ወንድሞቹ አሁንም እዛው አሜሪካ ነው የሚኖሩት። እሱ ግን ከአራት ዓመት ተኩል በፊት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ወሰነ።

ማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵውያን ድጋፍ እንደሚንቀሰቀስ እና እስካሁንም ምንም አይነት የውጭ ሀገር ድጋፍ እንዳላገኙ ቢንያም ገልፆልናል። እሱ እንደሚለው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊረዳ እና የአቅሙን ሊያደርግ ይችላል ። ማዕከሉ በየቀኑ አዳዲስ ተረጂዎችን ይቀበላል። እስከ ሰኔ ወር 1000 ተገልጋዩችን መቀበል የሚችሉበትን መንገድ እያመቻቸን ነው ይላል ቢንያም። እስካሁን ከ450 በላይ የሚሆኑት አረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን የሚኖሩት ለነሱ በተዘጋጁ አራት ቤቶች ውስጥ ነው።የ 22 ዓመቷ መሰረት ታደሰ ደግሞ በማዕከሉ ብዙ ሰዎች የሚፈፀሙትን ስራ ትሰራለች። በዚህ ማዕከል ውስጥ የሚያገለግሉ 65 በጎ ፍቃደኞች አሉ።

የማዕከሉን አላማ እና የበጎ ፍቃደኞቹን ሥራ ከድምፅ ዘገባው ያገኙታል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic