የተረሳዉ ጦርነት | ዓለም | DW | 21.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የተረሳዉ ጦርነት

የኃይል ሚዛን በተለዋወጠ ቁጥር ከአረቦች ሁሉ እጅግ ደሐይቱ ግን ጥንታዊ፤ታሪካዊቱ ሐገር  ለእብሪተኞች ሽኩቻ ዜጎችዋን ገባሪ መሆንዋ ነዉ አሳዛኙ ድቀት።የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን  እንዳስታወቀዉ ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር የመንን መደብደብ ከጀመረ ወዲሕ የሞተዉ ሰላማዊ ሰዉ ከ6 ሺሕ በልጧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:39

የተረሳው ጦርነት

የሳዑዲ አረቢያ ገዢዎች እና ለሳዑዲ አረቢያ ያደሩት የዓረብ መንግሥታት «ግፋ ቢል ሰወስት ወር» ባሉት ጦርነት የመን ዛሬም ትንጨረጨራለች።ሰወስተኛ ዓመቷ።የመኖች ያልቃሉ። ሳዑዲ አረቢያንዎች በረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳዬል ይለበለባሉ፤ይሸማቀቃሉ።የዩናይትድ ስቴትስ እና የብሪታንያ የጦር መሳሪያ ኩባንዮች ዓረቦች ከሚተላለቁበት ጦርነት ዶላር ይዝቃሉ።የተቀረዉ ዓለም የመንን ረስቶ ሶሪያ፤ፍልስጤም-እስራኤል፤ አሜሪካ-ኮሪያ ይላል። 

ገሚስ ዓለምን ይገዙ የነበሩት የኦስማን ቱርኮች በ15ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ የመንን ለማስገበር የፈለጉበት ሁለት ምክንያት ነበረባቸዉ።አስቀድመዉ የተቆጣጠሩትን የሙስሊሞችን ቅዱስ ሥፍራዎች መካ እና መዲናን ከጥቃት ለመከላከል-አንድ፤ የሕንድን ቅመም እና የቻይኖችን ሐር-ከምስራቅ፤ የአፍሪቃን የማዕድን እና የዱር ሐብት ከምዕራብ የሚሸጋገርበትን ሥልታዊ አካባቢ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር-ሁለት።

ይሕን ዕቅድ ለማስፈፀም ከግብፁ ገዢ ከሐዲም ሡሌይማን ፓሻ የተሻለ ሰዉ አልነበረም።ሡሌይማን ፓሻ የቆስጠንጥንያ አለቆቻቸዉን ፍላጎትም፤የመን ያለችበትን ሁኔታም ጠንቅቀዉ ያዉቁት ነበር።

ሱሌይማን ፓሻ  ጦራቸዉን «ንሳ» አሉ። በዘጠና መርከብ የተጫነ ጦርቸዉም ቀይ ባሕርን ይቀዝፍ ገቡ።ጦሩ አደንን ጨምሮ የደቡባዊ የመን የባሕር ዳርቻ ከተሞችን ለመቆጣጠር አንድ ዓመት አልፈጀበትም።1539 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)።ድል።

ድል አድራጊዉ ጦር ወደ ደጋማዉ የመን ለመዝለቅ ከአካባቢዉ ገዢዎች ጋር የገጠመዉ ዉጊያ ግን ፈታኝ ነበር።ስምንት ዓመት ተዋጋ።የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ ለቆስጠንጥኒያ አለቆቻቸዉ ባቀረቡት ዘገባ፤-

«ለወታደሮቻችን የየመንን ያክል አደገኛ ነገር አጋጥሞን አያዉቅም።ከግብፅ የምናዘምተዉ  ወታደር ሁሉ ዉኃ እንደገባ ጨዉ ቀልጦ ይቀራል።»

በእዉነትም ቱርኮች የመንን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ከ1539 እስከ 1547 በነበረዉ ስምንት ዓመት  ካዘመቱት  80ሺሕ ጦር በይሕወት የተረፈዉ 7 ሺሕ ብቻ ነበር።

ከ4መቶ ዓመታት በኋላ የካሮዉን አብዲን ቤተ-መንግሥትን የተቆጣጠሩት ኮሎኔል ገማል አብድናስር የቱርኮችን ሥሕተት፤የየመኖችን ፅናት፤ ወይም የመልከዓ ምድሩን ክፋት አዉቀዉ፤ አስተንትነዉ፤ አጥንተዉ ሊሆን-ላይሆንም ይችላል።ወይም አያስፈልጋቸዉምም ይሆናል።

በ1962 የሰሜን የመን ነገስታትን ከሥልጣን ያስወገዱ አብዮታዊ ወታደሮችን ከጥቃት እንደሚከለካሉ ግን ዛቱ።ታሕሳስ 1962።

«የየመን ጦርነት የኔ ጦርነት ነዉ።የየመን አብዮት የኛ አብዮት ነዉ።አብዮቱ የጀመረዉ መስከረም 26 ነዉ።በማግሥቱ ወፈፌዉ የሳዑዲ አረቢያ ንጉስ ወደ ኒግራን እና ጂዛን ጦር መሳሪያ ያግዙ ጀመር።»ናስር የመስከረም 26 ዓብዮት የተባለዉን ለዉጥ አራማጆችን ደግፎ የሚዋጋ 70ሺሕ ወታደሮች አዘመቱ።ግብፅ፤ ሪፐብሊካን የሚባሉትን አብዮታዉያንን በመደገፍ፤ ሳዑዲ አረቢያ እና ዮርዳኖስ ከስልጣን የተወገዱትን ንጉስ ኢማም መሐመድ አል ባደርን ደግፈዉ የመን ዉስጥ ይተላለቁ ገቡ።

አረቦች እርስ በርስ የሚፋጁበትን ጦርነት ሶቬየት ሕብረት ከግብፅ፤ ብሪታንያ፤ ኢራን፤እና እስራኤል ከሳዑዲ አረቢያ ጀርባ ሆነዉ ያቀለጣጥፉት ነበር።በሰወስት ዓመት ዉስጥ 2 መቶ ሺሕ የሚጠጋ የመናዊ አለቀ።ግብፅም የአስራ-አምስት ሺሕ ወታደሮችዋን ሕይወት ገበረች። ግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያን ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር አከሰረ።አሸናፊም-ተሸናፊም ሳይኖረዉ ተጠናቀቀ።በዚያ ዘመን ቬትናም ለዩናይትድ ስቴትስ የሽንፈት፤ዉርደት፤ ኪሳራ ምሳሌ እንደነበረች ሁሉ የመን የግብፅ ሆነች።1965።

ከዕድሜ፤ ልምድ እዉቀታቸዉ በላይ ሥልጣን የተሸከሙት የሳዑዲ አረቢያ አልጋወራሽ መሐመድ ሰልማን በየመኑ የርስ በርስ ጦርነት ተንደርድረዉ የተሞጀሩት የግብፅ ሽንፈት፤ዉርደት፤ኪሳራ ሐምሳኛ ዓመት ሲዘከር ነበር።መጋቢት 2015።

የሪያድ ገዢዎች በኢራን ይደገፋሉ ያሏቸዉን የየመን ሁቲ ሸማቂዎችን ቢዘገይ በሰወስት ወር ዉስጥ እንደሚያጠፉዋቸዉ ፎክረዉ ነበር።የሪያድ ነገስታት፤ከግብፅ እስከ ሴኔጋል፤ ከሱዳን እስከ አረብ ኤሚሬቶችን ያሉ ታዛዦቻቸዉን አስከትለዉ ያዘመቷቸዉ ዘመናይ የጦር ጄቶች ዕለት-በዕለት የመንን በቦም-ሚሳዬል ያርሳሉ።ሕዝብ ይፈጃሉ።ድሉ ግን ዛሬም በሰወስተኛ ዓመቱ የለም።የመኖች ሙታኖቻቸዉን ቀብረዉ እራሳቸዉ የሚቀበሩበትን ጊዜ ያሰላሉ።የዕለት-ከዕለት ዑደት።

«በሚሳዬል ከተመታዉ ቤት ፍርስራሽ ዉስጥ አራት ልጆችን ማዳን ችለናል።አራቱም ቆስለዋል።እናትዬዋ ሞታለች።አጠገቧ የነበረች ልጇም ሞታለች።ልጅ እና እናት።ሌላ ክፍል ዉስጥ የነበሩት አባት እና ልጅም ተገድለዋል።የሞቱትም-የዳኑትም አራት-አራት ናቸዉ።ልናድናቸዉ ሞክረን ነበርን ግን ሞተዋል።»

ይላሉ የሰዓዱ-ሰሜን የመኑ ነዋሪ።የጦርነቱ ዳፋ ለሳዑዲ አረቢያ ሕዝብም ተርፏል።የሪያዱ ወኪላችን ሥለሺ ሺብሩ እንደሚለዉ የሳዑዲ አረቢያ ሕዝብ ከየመን በሚተኮሰዉ ሚሳዬል በየዕለቱ ይሸማቀቃል።ጦሩ ባንጻሩ ሚሳዬል ሊያከሽፍ በተጠንቀቅ እንደቆመ ነዉ።

 

በ1960ዎቹ ሰሜን የመን ላይ በተደረገዉ ጦርነት ኢራን ከሳዑዲ አረቢያ፤ ከዮርዳኖስ፤ ከብሪታንያ እና ከእስራኤል ጎን ቆማ ግብፅን ትወጋ ነበር።ባሁኑ ጦርነት ግብፅ እና ኢራን ቦታ ተቀያይረዋል።ግብፅ የሳዑዲ አረቢያዎችን ጎራ ስትቀየጥ ኢራን «ጠላት» ናት።

አንዳድ ምዕራባዉያን የፖለቲካ

ተንታኞች  የኢራን እና የሳዑዲ አረቢያን ጠብ የሺዓ እና የሱኒ ሙስሊሞች ጠብ ዉጤት ባዮች ናቸዉ።ቴሕራኖች እንደ ሳዑዲ አረቢያ ሁሉ የዋሽግተን-ለንደን ታዛዥ፤ በነበሩበት ዘመን ከሪያዶች ጋር መወዳጀታቸዉን ያላነቀፈ የሐይማኖት ሃራጥቃ አሁን የጠብ ምክንያት የሆነበትን ምክንያት ለሚጠይቅ እኒሕ ተንታኞች አሳማኝ መልስ ማጣታቸዉ ነዉ አስተዛዛቢዉ።

በመሠረቱ የቴሕራን አያቱላሆች-ከሞስኮ ኦርቶዶክሶች፤ የሪያድ አሚር ሼኾች  ከዋሽግተን-ለንደን ፕሮቴስታንት- ካቶሊኮች ከልብ መወዳጀት ከቻሉ የአንድ ኃይማኖት ሁለት ሐራጥቃ የጠላትነት ምክንያት ሊሆናቸዉ የሚችልበት ምክንያት ግራ-አጋቢ ነዉ።

የሪያድ ገዢዎች በ1960ዎቹ ሰሜን የመን ዉስጥ ከግብፅ ጋር የተዋጉት የናስርን አስተሳሰብ የሚያራምዱ  የየመን የጦር መኮንኖች የሰነዓ ንጉሳዊ አገዝዝን በማሰወገዳቸዉ «ነግ በኔ» በሚል ሥጋት እንደነበር አላከራከረም።

ከቴሕራኖች ጋር ከ1979 ወዲሕ ጠብ የገጠሙትሙትም የኢራንን ንጉስ ከዙፋን ያስወገዱት እስላማዊ አብዮተኞች ሪያድም ተመሳሳዩን ለማድረግ የሚፈልጉ ኃይላትን ያጠናክራል በሚል ሥጋት እና ከዋሽግተኖችን  የሚሰጣቸዉን «የቤት ሥራ» ለመወጣት ነዉ።

የኃይል ሚዛን በተለዋወጠ ቁጥር ከአረቦች ሁሉ እጅግ ደሐይቱ ግን ጥንታዊ፤ታሪካዊቱ ሐገር  ለእብሪተኞች ሽኩቻ ዜጎችዋን ገባሪ መሆንዋ ነዉ አሳዛኙ ድቀት።የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን  እንዳስታወቀዉ ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር የመንን መደብደብ ከጀመረ ወዲሕ የሞተዉ ሰላማዊ ሰዉ ከ6 ሺሕ በልጧል።ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ።

«ከመጋቢት 26, 2015 እስከ ግንቦት 10, 2018 ድረስ 16, 385 ሰላማዊ ሰዎች መጎዳታቸዉን መስሪያ ቤታችን መዝግቧል።ከነዚሕ ዉስጥ 6385ቱ የሞቱ፤ 10,045ቱ የቆሰሉ ናቸዉ።ከሟች-ቁስለኞቹ አብዛኞቹ የተገደሉ እና የቆሰሉት ሳዑዲ አረቢያ በምትመራዉ ጦር የአዉሮፕላን ድብደባ ነዉ።»

ጦርነቱ የፈጀዉ ወታደር እና ታጣቂ ሲታከልበት የሟቾቹ ቁጥር ከ10 ሺሕ እስከ 12 ሺሕ ይገመታል።የቁስለኛዉ ቁጥር ከሐምሳ ሺሕ ይበልጣል።ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ አንድም ተፈናቅሏል ወይም ተሰድዷል።ከ22 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ለረሐብ እና በሽታ አጋልጧል።ከሳዑዲ አረቢያ በኩል ከአምስት መቶ በላይ ሰዉ ተገድሏል።የሪያዱ ወኪላችን ስለሺ ሽብሩ እንደሚለዉ በሰወስት ወር ይጠፋሉ የተባሉት የየመን ሸማቂዎች ዛሬ በአራተኛ ዓመታቸዉ ድንበር አሻግራዉ የሳዑዲ አረቢያን ሰማይ በሚሳዬል እየሰነጠቁት ነዉ።

ዛሬም የተተኮሰ ሚሳዬል ጂዛን አዉሮፕላን ማረፊያ አካባቢ መክሸፉን የሳዑዲ አረቢያ ጦር አዛዦች አስታዉቀዋል።ወደ ሳዑዲ አረቢያ  የሚተኮሰዉ ሚሳዬል እስካሁን በሰዉ ሕይወት ላይ ያደረሰዉ ጉዳት ትንሽ ነዉ።ይሁን እና አንድ ቀን ዒላማዉን ስቶ የመንገደኞች አዉሮፕላን ቢመታ፤ ወይም መኖሪያ አካባቢ ቢያርፍ ሳዑዲ አረቢያም እንደየመን የሰላማዊ ዜጎችዋን አስከሬን ለመቁጠር ትገደዳለች።

የሳዑዲ አረቢያ ገዢዎች የሶሪያዉን ፕሬዝደንት የበሽር አል አሰድን መንግስት ለማስወገድ  ቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር ይከሰክሳሉ።በጦርነቱ ለድል የተቃረቡት ግን ጠላቶቻቸዉ ናቸዉ።ከትሺቱ የቅርብ ጎረቤታቸዉ ቀጠር ጋር ሽኩቻ ገጥመዋል።ኢራንን ለማዳከም ያላደረጉ እና የማያደርጉት የለም።

ይሁንና በሊባኖስ ምርጫ፤ በኢራቅ ምርጫ፤ በሶሪያዉ ጦርነት የበላይነቱን የያዙት የኢራን ወዳጆች ናቸዉ።

በየመኑ ጦርነት የሁቲ አማፂዎች እንዲሕ እንደዋዛ የሚጠፋ እንዳልሆኑ አስመስክረዋል።አሸናፊ እና ተሸናፊዉ ያልተለየበት ጦርነት የሚያደርሰዉን ተጨማሪ ጥፋት ለማስቀረት ብዙዎች እንደሚመክሩት አብነቱ ድርድር ነዉ።ሳዑዲ አረቢያዉ የፖለቲካ ተንታኝ ሱላይማን አል አቂል እንደሚሉት ግን የሪያድ ገዢዎች እስካሁን ከያዙት አቋም ፈቅ የሚሉ አይመስሉም።«ሶሪያ ወይም የመን ያለዉን ሁኔታ በተመለከተ ሳዑዲ አረቢያ ከያዘችዉ አቋም ፈቅ የምትል አትመስልም።የዉጪ መርሕዋ በጣም አረጋጋጭ እየሆነ ነዉ።»

አረጋጋጩ መርሕ ሐብታሚቱን አረቢዊት ሐገር የሚያደርስበትን ሥፍራ ለመገመት ጥቂት ጊዜ መጠበቅ ግድ ነዉ።ለመካከለኛዉ ምሥራቅ ግን እስካሁን በሚያዉቀዉ እልቂት ጥፋት ላይ ተጨማሪ ጥፋት ከማቀጣጠል ባለፍ የተከረዉ ነገር የለም።

 

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች