የተመድ ጉባኤ እና የMDG ፍፃሜ | ዓለም | DW | 22.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የተመድ ጉባኤ እና የMDG ፍፃሜ

የ85 ሰዎች ገቢ ከግማሽ ከሚበልጠዉ የዓለም ሕዝብ ይበልጣል።---የዓመዓቱ ግብ ያልተሳካዉ በፖለቲካዊ ዳተኝነት፤ በዕዉቀት እጦት ብቻ አይደለም።በጥቅም ሽኩቻ እና ዕቅዱ የሐብት ክፍፍል የሚያነሳ በመሆኑም ጭምር እንጂ

የዓለም መሪዎች ለዓለም የጋራ ማሕበር አመታዊ ጉባኤ ኒዮርክ እየታደሙ ነዉ።የትልቁ ማሕበር ዋና መቀመጫ ኒዮርክ የትላልቅ እንግዶችዋን ዓመታዊ ጉባኤ፤ ቃል፤ ንግግር ከማስተናገድዋ በፊት ግን በትናንሽ ነዋሪዎችዋ ታላቅ ሠልፍ ተጥለቅላቀች።ጉባኤ፤ ሠልፉ የሚደረግና የተደረገዉ ዓለም አቀፉ ማሕበር የመዓቱ የልማት ግብ (Millennium Development Goal) MDG-በምሕፃሩ ያለዉ ዕቅድ በሚጠናቀቅበትወቅት ነዉ።የዓለምም፤የጋራ ማሕበሩም፤የሠልፈኛዉም ሕዝብ ዋና ዘዋሪዎች ዋና ትኩረት ግን ኢራቅ እና ሶሪያ የሸመቀዉ አክራሪ ቡድንን ማጥፋት ነዉ።የጉባኤ፤ ሠልፍ፤ ዕቅድ፤ የሐያላኑ ፍላጎት አንድነትና ተቃርኖ ያፍታ ዝግጅታን ትኩረት ነዉ-አብራችሁኝ ቆዩ።

ቃል ነበር።የአንድ መቶ ሰማንያ ሐገራት መሪዎች በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ MDG ብለዉ የሠየሙት፤በ2000 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በፊርማቸዉ ያፀደቁት-ዓለም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ መሪዎቹ ለየሚመሩት ሕዝብ የገቡት ቃል።«MDGS ሁሉም ሐገራት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት በ2000 የተስማሙባቸዉ የተለያዩ ግቦች ናቸዉ።ሥምምነቱ በ2015 ዓለምን የተሻለች ሥፍራ ለማድረግ ቃል የገቡበት ነዉ።»

አስራ አራት አመት ደፈነ።ባለፉት አሥራ-አራት ዓመታት ከአፍቃኒስታን እስከ ፓኪስታን፤ከፊሊፒንስ እስከ ኢንዶኔዚያ፤ ከኢራቅ-እስከ ሊቢያ፤ከፍልስጤም እስከ ሶሪያ፤ከሶማሊያ እስከ ኮንጎ፤ ከደቡብ እስከ ሰሜን ሱዳን፤ ከማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፕብሊክ እስከ ናጄሪያ፤ ከማሊ እስከ ኮትዲቯር ሌላም ጋ ጦርነት ብቻ ያረገፈዉን ሕዝብ የቆጠረ የዓለም መሪዎች የሠላም-ብልፅግና ቃል በነነ እንጂ-ዓለም የተሻለች ሥፍራ ናት ካለ በርግጥ አበለ።

«ዕቅዱ ድሕነትን ለማስወገድ፤የጤና አገልግሎትን፤ትምሕርትን ለማዳረስ፤የተፈጥሮ ሐብትን ለመጠበቅ፤የሴቶችና የልጃገረዶችን እኩልነት ለማስከበር ያለመ ነዉ።»ትናንት ኒዮርክን በሠልፍ ያጥለቀለቀዉን ሕዝብ አደባባይ ያስወጣ፤ ያስቆጣ፤ ያስጮኸዉ እኒያ ባለፉት አሥራ-አራት አመታት ብዙ የተወራ፤ የተነገረ፤ ቃል የተገባላቸዉ እቅዶች በተለይም የተፈጥሮ ሐብትን ለማስጠበቅ የተደፈዉ ገቢር አለመሆኑ ነዉ።

ባለፉት አሥራ-አራት አመታት የሐገራት መሪዎች፤ ባለሥልጣናት፤ ፖለቲከኞች፤ የድርጅቶች ተጠሪዎች የአየር ንብረት ለወጥን ለማስወገድ ያልመከሩ፤ያልተነጋገሩ ያላቀዱበት ጊዜ የለም።የኪዮቶ ሥምምነት፤ የቦኒስ አይረስ ዉል፤ የቦን የመግባቢያ ሐሳብ እየተባለ በየወረቀቱ የሚቀረዉ ዉል ሥምምነት ለቁጥር አታካች ነዉ።አብዛኛዉ ግን ገቢር አልሆነም።

ነገ ዓመታዊ ጉባኤያቸዉን ኒዮርክ የሚጀምሩት መሪዎች የመጀመሪያ የመነጋገሪያ ርዕሥም የአየር ንብረት መዛባት ነዉ።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩት ሠልፈኞች አላማም መሪዎቹ በነገዉ ጉባኤያቸዉ የአየር ንብረት መዛባትን ለመከላከል ከእስከዛሬዉ ለየት ያለ-ገቢር የሚያደርጉት ዉሳኔ እንዲያሳልፉ ማሳሰብ ነዉ።

«ሥልጣኑ ያለዉ በነዚሕ ሰዎች እጅ ነዉ።ወደየመጡበት ሐገርና ከተማ ሲመለሱ በያለበት ተጨባጭ ርምጃ መዉሰድ አለባቸዉ።የተባበሩት መንግሥታትን ዕቅድ ገቢር ማድረግ አለባቸዉ።»

ይላሉ ከሠልፈኞቹ እንዱ።የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት መሪዎች ወደየሐገራቸዉ ሲመለሱ አንድም ኤቦላን አለያም ቦኩ ሐራምን የሚዋጉበትን ሥልት ከማዉጠንጠን አልፈዉ ተፈጥሮን ሥለማስጠበቅ ይጨነቃሉ ብሎ ማሰብ በርግጥ የዋሕነት ነዉ።

ምሥራቅ አፍሪቃዎች አንድም ደቡብ ሱዳን አለያም አልሸባብ ካላሉ በስተቀር ተፈጥሮን ማስጠበቅ የጋራ ርዕሳቸዉ ያደርጉታል ብሎ የሚገምት የለም።ሊቢያዎች ሥለተፈጥሮ ጥበቃ ሊያስቡ ቀርቶ በጉባኤዉ እንደ ሐገር የሚወክላቸዉ መሪ ማግኝታቸዉ አጠራጣሪ ነዉ።ከግብፅ እስከ ቱኒዚያ፤ ከአልጀሪያ እስከ ሞሪታኒያ ያሉት የሰሜን አፍሪቃ ሐገራት መሪዎች ቅድሚያ የሚሰጡት የየራሳቸዉ ምሥቅልቅል አለ።

ደቡባዊ አፍሪቃዎች ከሌሎቹ የአፍሪቃ ብጤዎቻቸዉ የተለዩ አይደሉም።ደቡብ አሜሪካኖች የጡንቸኛ ጎረቤታቸዉን አረማመድ ወደ ሰሜን አንጋጠዉ ከማየት በፊት የአማዞን ሸለቆን ጉራንጉር የመቃኘት ዕቅድ፤ ዕድል፤ ፍላጎትም አይኖራቸዉም።

ከአፍቃኒስታን እስከ ፓኪስታን ያሉት የሩቅ ምሥራቅ ሐገራት፤ ከኢራቅ እስከ ፍልስጤም የሚገኙት የመካከለኛዉ ምስራቅ ሐገራት የጦርነት ዛር እያስደለቃቸዉ ስለ ዛፍ፤ ቅጠል፤አፈር ዉሕ፤ ጎርፍ ማሳብ ለነሱ ቅንጦት የሚቆጠር ነዉ።

ከሁሉም በላይ ዓለምን ባሻቸዉ የሚያሾሩት፤አየርን በመበከል የመጀመሪያዉን ሥፍራ የሚይዙት የዩናትድ ስቴትስ፤የሩሲ፤ የቻይና እና የምዕራብ አዉሮጳ መሪዎች ኢራቅን፤ሶሪያን፤ ፍልስጤምን፤አፍቃኒስታንን፤ ዩክሬንን በሚያነደዉ ጦርነት አሸናፊነታቸዉን ለማረጋገጥ ከመጣር አልፈዉ ከጉባኤዉ መልስ ለተፈጥሮ ሐብት መጠበቅ ይጨነቃሉ ብሎ ማሰብ ሲበዛ ከባድ ነዉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊሙን የዓለም መሪዎችን ቅድሚያ ትኩረት አያዉቁቱም ማለት አይቻልም።ግን እንደ ዲፕሎማት የአየር ንብረት ለዉጥን ለማስከበር ጊዜ ማጥፋት የለብንም ይላሉ።«እዲሕ አይነቱ ጥንካሬ፤ሐይልና የሕዝብ ድምፅ ሲበዛ አስደንቆኛል።መሪዎቹ ማክሰኞ ሲሰበሰቡ ይሕ ድምፅ በትክክል ይንፀባረቃል የሚል ተስፋ አለኝ።የአይር ንብረት ለዉጥ የዘመናችን ወሳኝ ጉዳይ ነዉ።እና (ችግሩን ለማስወገድ) የሚባክን ጊዜ የለም።»

አሉ።ማለት ማደረግ ቢሆን ኖሮ የዛሬ አስራ-አራት አመት የተገባዉ ቃል ገቢር በሆነ ነበር።የዓመአቱ ግቦች የተሰኘዉ ዕቅድ ዋና መሐንዲስ የያኔዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን እንዳሉት ባለሥምንት ነጥቡ ዕቅድ የድሆችን መሠረታዊ ፍላጎች ለማሟላት ያለመ ነበር።

ዕቅዱ የዓለም ሕዝብን እስተሳሰብና ግንዛቤ መለወጡ፤ማሳደጉ፤ወይም ማሻሻሉም አይካድም።ሕዝባቸዉን በልማት ሥም የሚያጭበረብሩ መንግሥታት ወይም መሪዎችን ሻጥርም ቢያንስ ለየዝባቸዉ ያጋለጠ ነዉ።«የዓመአቱ ግቦች በማሕበረሰባችን ዉስጥ እጅግ የደኸዩ ግለሠቦችን መሠረታዊ ፍላጎቶች አንጥሮ ያሳየ መዋቅር አለዉ።እነዚሕን ፍላጎቶች ለማሟላት መንግሥታት ከሕብረተሰቡ ጋር ተባብረዉ መስራት እንዳለባቸዉ የሚያሳስብም ነዉ።»

ዕቅዱን ገቢር በማድረጉ ሒደት አንዳድ ሐገራት ብዙ ርቀት መጓዛቸዉንም አናን ይመሰክራሉ።

«ብዙ መንግሥታት ለዉጥ አሳይተዋል።በተለይ ሕንድ፤ቻይና እና ብራዚል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸዉን ከድሕነት አላቅቀዋል።ብራዚል እና ቻይና ከዚሕም አልፈዉ የዓመአቱን ግብ የልማት ዕቅዳቸዉ አካል አድርገዉታል።(ሌሎች) ብዙ ሐገራት ግን ዕቅዱን በተገቢዉ ጊዜ ገቢር አያደርጉትም።አነዚሕ መንግሥታት የሕዝባቸዉን መሠረታዊ ፍላጎት እንዲያሟሉ ጫና ማድረግ ይኖርብናል።»

ጫና አድራጊዉ ማነዉ ነዉ-ጥያቄዉ፤ የሚደረግበትስ? የዓመአቱ ግብ ከመወጠኑ ከብዙ አመታት በፊት የበለፀጉት ሐገራት ከአጠቃላይ አመታዊ ገቢያቸዉ እጅግ ጥቂቱን የድሆቹን ሐገራት ሕዝብ ለመርዳት እንዲያዉሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠይቆ ነበር።

ድርጅቱ በ1970 ባቀረበዉ ጥያቄ መሠረት የበለፀጉት መንግሥታት ከአጠቃላይ ዓመታዊ ገቢያቸዉ 0,7 በመቶዉን የድሆቹን ሐገራት ሕዝብ ለመርዳት እንደሚያዉሉት በተደጋጋሚ ቃል ገብተዉ ነበር።የዓመአቱ ግብ በሁለት ሺሕ ሲፀድቅም ያንኑ ቃላቸዉን ደግመዉት ነበር።አርባ-አራት አመት።እስካሁን ቃላቸዉን ያከበሩት አለም አቀፉ ድርጅት እንዳስታወቀዉ አራት ሐገራት ብቻ ናቸዉ።

ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የተቀሩት ሐብታም ሐገራት ግን አንድም ቃላቸዉን አጥፈዋል።አለያም ሌላ ተጨማሪ ዘመን ይጠብቃሉ።አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ አንዲት ኢራቅን ላወደመዉ ወረራ የከሰከሰችዉ ገንዘብ ድሕነትን ለመቀነስ ዉሎ ቢሆን ኖሮ ድሕነትና ረሐብ ዛሬ የመዝገበ ቃላት ማድመቂያ ብቻ በሆኑ ነበር።

ሥልጣን ላይ የመቆየት ዋስትናቸዉ በየሕዝባቸዉ መወደድ፤ መመረጥ ሳሆን በዓለም ሐያላን ፍቃድና ፍላጎት ላይ የተመሠረተዉ የኣ,ብዛኞቹ የድሐ ሐገራት መሪዎች የሕዝባቸዉን ሕይወት ለመለወለጥ ከልብ የሚጥሩበት አስገዳጅ ምክንያት የለም።የበለፀጉት ሐገራት ቃላቸዉን ባለማክበራቸዉ የመዉቀስ መብትም የላቸዉም።

በዚሕም ሰበብ የዓመአቱ ዕቅድ ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ-ዕቅዱን የተቹት ወገኖች በተደጋጋሚ እንዳሉት ያለዉ የመስጠት ፍላጎት፤ የሌለዉ ያልሰጠዉን የመጠይቅ መፍንሰዊ ነጻነት ሳይኖራቸዉ ያጸደቁት ዕቅድ ገቢር እንደማይሆን ይታወቅ ነበር።አልሆነም።የዕቅዱ ዘመን ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት ሲቀረዉ አሁን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሌላ ረቂቅ ዕቅድ ይዞ ብቅ ብሏል።

ዘላቂ የልማት ዕቅድ (Ssustainable Development Goal`s) SDG-በምሕፃሩ።የአርቃቂዎቹ አዘጋጆች ፓዉል ላድ እንደሚሉት ረቂቁ MDG ያላካተታቸዉን ጉዳዮች የያዘ፤ ብዙ ወገኖችን ያሳተፈና የሚያሳትፍ ነዉ።እስከ አሁን ድረስ በአንድ መቶ ሐገራት ብሕራዊ ዉይይት ተደርጎበታል።

«ከብሔራዊዉ ዉይይት በተጨማሪ በእኩልነት፤በትምሕርት፤ በጤና፤ በአስተዳደር፤ በሠላምና በፀጥታ በዉሐ፤ እና በመጸዳጃ፤ በእርሻ እና የአካባቢ ጥበቃን በሚመለከቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስብሰባና ዉይይቶችን አድርገናል።ስብሰባዎቹ ባለሚያዎች፤ ሳይንቲስቶችን፤ ነጋዴዎችን፤ የወደፊት መሪዎቻችን የሆኑትን ወጣቶችንና ተማሪዎችን ለማሳታፍ ጠቅመዋል። ከዚሕ በተጨማሪ በጣም «የምንፈልጋት ዓለም» በሚል ርዕስ በጣም አሳታፊ የሆነ የአምደ መረብ መድረክም አዘጋጅተናል።»

ረቂቁ እስከ መጪዉ ዓመት መስከረም ድረስ ሲብላላ ቆይቶ በመስከረሙ ጉባኤ በመሪዎቹ ይጽድቃል ተብሎ ይጠበቃል።በጀርመን ኦክስፋም የተሰኘዉ የብሪታንያ ግብረ-ሠናይ ድርጅት ተጠሪ ቶቢያስ ሐዉስሽልድ እንደሚሉት የ85 ሰዎች ገቢ ከግማሽ ከሚበልጠዉ የዓለም ሕዝብ ይበልጣል።

«85ቱ የዓለም ሐብታሞች፤ ከ3,5 ቢሊዮን ከሚበልጠዉ ማለት ከግማሹ የዓለም ሕዝብ የበለጠ ገቢ አላቸዉ።ሥለዚሕ ሐብት የማካፈል ጥያቄም መነሳት አለበት።»

የዓመዓቱ ግብ ያልተሳካዉ በፖለቲካዊ ዳተኝነት፤ በዕዉቀት እጦት ብቻ አይደለም።በጥቅም ሽኩቻ እና ዕቅዱ የሐብት ክፍፍል የሚያነሳ በመሆኑም ጭምር እንጂ።ያሁንም SDG ባንድ ወይም በሌላ መልኩ ለሐብት ክፍፍሉ ጥያቄ ሁነኛ ምልሽ ካልሰጠ ካለፈዉ የሚሻልበት ምክንያት አይኖርም።ብቻ ደግሞ ለመጪዉ ዘመን ባለሙያዎች አበል የሚያገኙበት፤ ፖለቲከኞች ያለፈ ቃላቸዉን የሚደብቁበት፤ ጋዜጠኞች የሚዘግቡበት አዲስ ርዕስ አገኙ።እንለማማደዉ፤ SDG።ነጋሽ መሐመድ ነኝ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic