የተመድ ተልዕኮ በመካከለኛዉ አፍሪቃ ሬፐብሊክ | አፍሪቃ | DW | 15.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የተመድ ተልዕኮ በመካከለኛዉ አፍሪቃ ሬፐብሊክ

የተመድ በመካከለኛዉ አፍሪቃ ሬፐብሊክ ዛሬ መስከረም 5 ቀን ይፋዊ ተልዕኮን ይጀምራል። በመካከለኛዉ አፍሪቃ ሬፐብሊክ ሰላም ለማምጣትና ሀገሪቱን የሚያስተዳድር መንግሥት ለመመስረት እንዲያስችል፤ የመንግሥታቱ ድርጅት ተልእኮ ለስድስት ወር ይዘልቃል መባሉ አያጠያያቂ ሆንዋል።

በዚህም ከወዲሁ የድርጅቱ ተልዕኮ ስኬታማ ላይሆን ይችላል የሚል መላምትን አሳድሮአል። የተመድ ዋና ፀሃፊ ባንኪሙን ባለፈዉ ሚያዝያ ወር መካከለኛዉ አፍሪቃ ሬፐብሊክን ሲጎበኙ ሶስት መልክቶችን አስተላልፈዉ ነበር። የመጀመርያዉ መልክታቸዉ «በጦርነት የምትኖሩ የሚትኖሩ ኅብረተሰቦች ብቻችሁን አይደላችሁም የተመድ ከጎናችሁ በመቆሙ ይኮራል» የሚል ነበር። ሁለተኛዉ መልዕክት ለዓለም ያስተላለፉት ጥሪ ነዉ « ወደሌላ አትመልከቱ» ይላል። ሶስተኛዉ መልክት ደሞ « ተስፋ አለ» የሚል ነበር። ታድያ ዛሬ ቃል ወደ ተግባር የተቀየረበት ዕለት ነዉ። ዛሬ መስከረም አምስት ፤ የተመድ ሰማያዊ ቆብ ያደረጉ ሰላም አስከባሪ ጓዶች በመካከለኛዉ አፍሪቃ ሬፐብሊክ ተልዕኮአቸዉን ይጀምራሉ። በዚህ ተልእኮ ወታደሮችና ፖሊሶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 12000 ኃይላት ይዘምታሉ። እስካሁን ወደ ገሚስ የሚሆኑት እቦታዉ ላይ ይገኛሉ። ሰማያዊ ቆብን አድርገዉ በመንግሥታቱ ድርጅት ስር ያሉት ወታደሮች ወደ 5000 ያህሉ በአፍሪቃ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ስር እዛዉ የነበሩና መለዮአቸዉን ቀይረዉ የመንግሥታቱ ድርጅትን መለዮን ያጠለቁ መሆናቸዉ ነዉ የተመለከተዉ። ከነዚህ መካከል ከብሩንዲ፤ ከሩዋንዳ፤ ከጊኒ እና ከካሜሩን የመጡት ሰላም አስከባሪ ጓዶች ስልጠናንም ተሰቶአቸዋል። በተልዕኮዉ ከመንግሥታቱ ድርጅት አቋሞች መካከል ሲቪል ነዋሪዎችን ከጾታ ጥቃት መጠበቅ፤ መከላከል የሚለዉ ይገኝበታል። በመካከለኛዉ አፍሪቃ በመንግሥታቱ መለዮን ለብሰዉ የሚዘምቱት ሰላም አስከባሪዎች፤ ወደ 1800 በሚጠጉ ከፓኪስታን፤ ከኢንዶኔዥያ፤ ባንግላዴሽ እና ሞሮኮ በተዉጣጡ የድርጅቱ የሰላም አስከባሪ ጓዶች ይደገፋሉ።
በመካከለኛዉ አፍሪቃ የ«ኦኮፒ» ዓለማቀፍ ምክር ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ስሚዝ እንደሚሉት፤ የተባለዉ ቁጥር ሰላም አስከባሪ ኃይል እስኪመጣ ድረስ ገና ብዙ ጊዝያትን ይፈጃል፤

« በተልዕኮዉ የተመደቡት ሰላም አስከባሪ ጓዶች ቦታዉ ላይ እስኪደርሱ ገና ብዙ ግዜን ይወስዳል። በአፍሪቃ ዉስጥ ይዘምታል የተባለዉ የሰላም አስከባሪ ጦር ኃይል ቦታዉ ላይ ተጠናቆ የሚገኝበት አንድም ተልኮ እስካሁን አልታየም»
ምክንያቱ ፤ በሌሎች የአፍሪቃ ሀገራትም ይህን አይነት ተልዕኮ በተመሳሳይ ግዜ ስለሚያስፈልግ፤ እንዲዘምት ስለሚወሰን ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪቃ ሕብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል በቂ ወታደሮች ስለሌሉ፤ የመንግሥታቱ ድርጅት ሕብረቱንም ይደግፋል። በሌላ በኩል ይላሉ፤ በመካከለኛዉ አፍሪቃ የኦኮፒ ዓለማቀፍ ምክር ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ስሚዝ በሌላ በኩል ይላሉ፤ ምዕራባዉያኑ ሀገራት ወታደሮቻቸዉን አደገኛ ባሉት የአፍሪቃ ሀገራት ላይ ለተልዕኮ መላክ አይፈልጉም ።
« ወታደሮች በተልዕኮ ላይ አልፈዉ፤ አስክሪናቸዉ ወደ ሀገር ሲመለስ ፖለቲከኞች በሚያደርጉት ምርጫ መራጭን ያጣሉ በፖለቲካዉ ዓለም ተወዳጅ አይሆኑም።
እንደ ዴቪድ ስሚዝ እምነት በመካከለኛዉ አፍሪቃ ሬፐብሊክ 12.000 የተመድ ወታደሮች ለሰላሙ ተልዕኮ ይዘምታሉ ቢባል እንኳ በቂ አይደለም። « ይህች ሀገር የፈረንሳይን አንድ ከግማሽ እጥፍ ትሆናለች፤ ያላት መሰረተ ልማት እጅግ የወደቀ ነዉ። ይህ ደግሞ የመመላለሻዉንና የስልክ መገናኛዉን መንገድ እጅግ ከባድ ያደርገዋል። ታድያ በዚህ ሁኔታ 50 ሺ የተመድ ሰላም አስከባሪ ወታደሮችም ቢዘምቱ በቂ አይሆንም»
የመካከለኛዉ አፍሪቃ ሬፐብሊክ ከተመድ ተልዕኮ ተስፋ የሚያደርገዉ ነገር ቢኖር፤ በአካባቢዉ ላይ የሚገኙትን ታጣቂ ኃይሎች ትጥቅ ማስፈታት መሆኑን ዴቪድ ስሚዝ ይገልፃሉ። በጎርጎረሳዊ 2013 ዓ,ም በሀገሪቱ የመንግሥት ግልበጣ ከተካሄደ በኋላ መካከለኛዉ አፍሪቃ ሬፐብሊክ በማይጣጣሙት በሴሌካ ሚሊሽያዎችና ፀረ-ባላካ ሚሊሽያዎች መካከል ደም አፋሳሽ ጦርነት ወድቃለች። በጦርነቱ ከ 6000 በላይ ሲቪሎች ተገድለዋል፤ የሀገሪቱ ከፊል ነዋሪ ህዝብ ለስደት ተዳርጎአል። እንደ ብዙዎች እምነት ሁለቱ አማፂ ቡድኖች እጅ የሚገኘዉ የጦር መሳርያ እና ስልጣን ቢነጠቅ ምናልባትም ሰላም ይመጣል።


እንድያም ሆኖ መካከለኛዉ አፍሪቃ ሬፐብሊክ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣችበት ከ ጎርጎረሳዊ 1958 ዓ,ም ጀምሮ ደም አፋሳሽ የርስ በርስ ጦርነት፤ ማስተዳደር የማይችል መንግሥትና፤ ከዉጭ ሀገራት የተሰባሰበ የሰላም አስከባሪ ጓድ አልተለያትም።
የተመድ በመካከለኛዉ አፍሪቃ ሬፐብሊክ ዋና ተልዕኮ፤ ሀገሪቱ በጎርጎረሳዊ 2015 ዓ,ም የካቲት ወር ላይ ልታደርግ ላቀደችዉ ምርጫ መዘጋጀት ነዉ። የመንግሥታቱ ድርጅት ሰላም አስከባሪ ጓድ በመካከለኛዉ አፍሪቃ ሬፐብሊክ ፤ የምርጫ ጣብያዎችን ማቆም፤ የምርጫ ታዛቢ መላክ፤ የምርቻ ኮሮጆን መጠበቅና፤ ወደ መዲናዋ ሰብስቦ ማምጣት የመሳሰሉ ልምዶች አሉት። የድርጅቱ ሰላም አስከባሪ ጓዶች በጎርጎረሳዉያኑ 1999 ዓ,ም በሀገሪቱ በተደረገዉ ምርጫ ይህን ተግባር ፈፅመዋል። የዝያን ጊዜ የመንግዝታቱ ድርጅት ተልዕኮ በምህፃሩ /MINURCA / በሚል የሚታወቅ ሲሆን ምርጫዉ ከተጠናቀቀ ከአምስት ወራት በኋላ ተልዕኮዉ መጠናቀቁ ይታወሳል። የመንግስታቱ ድርጅት ወታደራዊ ተልኮ በተጠናቀቀ በዓመቱ ደግሞ ዳግም በዝያች ሀገር የመንግሥት ግልበጣ ተካሂዶ ሀገሪቱ ዳግም በቀዉስ መዘፈቅዋ የሚታወቅ ነዉ።
ሃይከ ፊሸር / አዜብ ታደሰ
ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic