የተለያየ ከሳይንስ ጋር ግንኙነት ያለው ዜና፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 28.07.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የተለያየ ከሳይንስ ጋር ግንኙነት ያለው ዜና፣

ፍጥረተ ዓለም ከ 13,7 ቢሊዮን ዓመት ገደማ በፊት በፍንዳታ ሳቢያ እንዴት እንደተዘረጋ ለማወቅ ምርምራቸውን ያጠናከሩ የአውሮፓና የአሜሪካ ጠበብት፤

default

በድረ-ገጽ አገልግሎት ደረጃ፤ከመላዋ ጀርመን በአንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው፣ የበርሊን ዩኒቨርስቲ፣ (Freie Universität Berlin)

የቁስ አካል ሁሉ ምንጭ የሆነውን Higgs Boson(‘God Particle’)ለማወቅ እየተቃረቡ መምጣታቸውንን ገለጡ። ጀኔቭ አጠገብ በከርሠ-ምድር የሚገኘው የአውሮፓውያን ማዕከላዊ የኑክልየር የምርምር ጣቢያ (CERN) ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ጀርመናዊው ሮልፍ ሆየር ፓሪስ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የከፍተኛ ኃይል ምንጭ ነክ የፊዚክስ ሰብሰባ ላይ እንዳስታወቁት፤ በቤተ-ሙከራ የሚካሄዱ የምርምር እርምጃዎች ከታሰበው በላይ ዕድገትም ሆነ ምጥቀት እንደታየባቸው ተናግረዋል። በዩኒቨርስ ፣ ሩቡ፣ የማይታይ ቁስ አካል ነው ተብሎ የሚታሰብ ሲሆን እስካሁን ሊደረስበት የቻለው 5 % ብቻ ሲሆን 70% የማይታየውን የኃይል ምንጭ ማወቅ አልታቻለም። የአውሮፓውያኑ የኑክልየር ምርምር ጣቢያ Large Hadron Collider በተሰኘው መሣሪያው አማካኝነት የጨለማውን ፍጥረተ ዓለም (ዩኒቨርስ )ምንነት ምሥጢር ይፈነጥቃል ብለው እንደሚያምኑና ሆኖም ጊዜ መውሰዱ እንደማይቀር ሆዬር አስረድተዋል።

የጀኔቩ LHC በከርሠ-ምድር በ 27 ኪሎሜትር ዙሪያ፣ የአቶም ቅንጣቶችን በማጋጨት በንዑሱ፣ የፍጥረተ-ዓለሙን መሰል ፍንዳታ በማከናወን ላይ እንደቆየና ይህንም ካለው ከፍተኛ ኃይል በገሚሱ ብቻ ማለትም በ 7 ሚልዮን ሚሊዮን ኤሌክትሮን ቮልት (7eV) መጠቀሙንና እ ጎ አ ከ 2013 ጀምሮ ግን በ 14 TeV ኅይል የሚሠራ መሆኑ ተገልጿል።

ለንደን፤ መጃጀትን በሥልጠናም ሆነ መቋቋም ይቻላል ተባለ።

በብሪታንያና በፊንላንድ ምርምር ያካሄዱ ጠበብት፤ የተማሩ ሰዎች፤ መጃጀትን በተሻለ ሁኔታ መቋቋም ይችላሉ፤ እንዲያውም የአንድ ሥልጠናም ሆነ ትምህርት በመማርየአእምሮን የማሰብና የማስተዋልችሎታ የሚጎዳውን በሽታ በእጅጉ ያስወግደዋል አሉ። የዚህ ምርምር ውጤት በሰፊው ብሩኅ ተስፋ አስጨባጭ መሆኑም ተነግሯል። በብዙ አገሮች፣ የዕድሜ ባለጸጎች የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር እጅግ እየጨመረ በመጣበት ወቅት ፤ መጃጀትን ለመታገል የተመራማሪዎቹ ውጤት ጠቀሜታ እንደሚኖረው ሳይታመንበት አልቀረም። በመጃጀት፤ የማስታወስ፤ የማስተዋል፤ የቋንቋና የሂሳብ ስሌት ችግሮች ሊከሠቱ ይችላሉ።

በሌላ በኩል፤ ጀርመን ውስጥ በላይፕትሲግ የአእምሮ ምርምር ማእከል ጥናት ያደረጉ ጠበብት፣ መጃጀት፣ በተፈጥሮ በአንጎል ውስጥ በሚያውክ ነገር የሚፈጠር ችግር ነው ብለዋል። በዚያ የሚገኘው የምርምር ተቋም ኀላፊ Thomas Arendt እንዳሉት በአንጎል ውስጥ የልዩ ክፍል ነርቦች በብዛት መታወክ ለሴሎች መሞት ሰበብ ይሆናል፤ ይህን ምን እንደሚያስከትለው ግን እስካሁን አይታወቅም ነበረ ። መጃጀት፤ በአመዛኙ ከ 65 ዓመት በላይ ዕድሜ ባላቸው ይበልጥ የሚከሠት ሲሆን፤ ይኸው ከነርብ ጋር የተያያዘው በሽታ በዓለም ዙሪያ በ 24 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የአእምሮ ሳንክ ያስከተለ ነው።

በርሊን፤ በዓለም ዙሪያ የዱር እንስሳትና እጽዋት መመናመን ፣

በተባበሩት መንግሥታት፤ አጠቃላይ ጉባዔ ውሳኔ መሠረት ዘንድሮ ማለትም 2010 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት፣ የብዝኀ-ህይወት መታሰቢያ ዘመን መባሉ አይዘነጋም። በመሆኑም፤ እያንዳንዱ ሀገር በግዛቱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የዱር እንስሳትና ዐራዊት እንዲሁም እጽዋት ኅልውና መንከባከብ ይጠበቅበታል።

በዓለም ዙሪያ በየዕለቱ 150 ያህል የዱር እንስሳትና የእጽዋት ዓይነቶች ከገጸ-ምድር በመጥፋት ላይ መሆናቸው ይነገራል። በምድር ሰቅ ዙሪያና በረዶ በብዛት በሚገኝባቸው በምድራችን ሰሜንና ደቡብ ዋልታዎች አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሎችም የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ ብርቅ ድንቅ የዱር እንስሳትና እጽዋት ለጥፋት የሚዳርግ አደጋ እንደተደቀነባቸው ታውቋል።

አንድ ጤናማና አማካይ ክብደት ያለው ሰው ያለምግብ ምን ያህል ጊዜ መኖር ይችላል?

የሮልድ ኦሌፍስኪ የተባሉት የ«ሆርሞን» ተመራማሪ እንዳሉት ከሆነ ከ 60 ቀን አይበልጥም። ለዚያውም ከውሃ ጋር ለኅልውና አስፈላጊ የሆኑ ቪታሚኖችን ማግኘት ከተቻለ ብቻ ነው። አንድ ሰው፤ ለረሃብ በሚደረግበት ወይም ራሱን በሚያስርብበት ጊዜ፣ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በየቀኑ አንድ ኪሎ ያህል ክብደት ይቀንሳል። በጨረሻም በየቀኑ ግማሽ ኪሎ(500 ግራም)ይቀንሳል ። በረሃብ ላይ የሚገኝ አንድ ሰው አንድ ሳምንት ምግብ ሳያገኝ ከቆዬ በኋላ፤ በቀጥታ በሰውነቱ ውስጥ የተጠራቀመው ቅባት የምግብ አገልግሎትነቱን ይሰጣል። ይሁንና ፤ የደም ግፊትና የልብ ትርታ ይቀንሳል። በሁለት ሳምንት ውስጥ ጡንቻዎች የልብ ጭምር ይኮማተራሉ፤ ይሟሽሻሉ። ያም ሆነ ይህ፤ በረሃብ እስከመሞት የሚያደርሰው የፕሮቲን እጦት ነው። ከመጠን በላይ ክብደት ያላቸው ሰዎች፣ ያለምግብ 200 ቀን ያህል በህይወት መቆየት ይቻላሉ። በሰውነት የተጠራቀመ ቅባት እያንዳንዱ ኪሎ 10 ሺ ያህል ኪሎ ካሎሪ ኃይል አለው።

ሞስኮ፤ የኅዋ ሥነ ቴክኒክ ለምድር ፈጣን ልማት፣

በኅዋ ምርምር ቀደሚዋ ሀገር ሩሲያ፣ ለኅዋ ምርምር ትኩረት የሰጠችበትን ሥነ ቴክኒክ በምድራዊ ግዛቷ ልማትን ለማፋጠን፤ የኅይል ምንጭ አቅርቦትን ለማዘመን እንደምትጠቀምበት አስታወቀች። የኅይል ምንጭ ጉዳይ ሚንስቴር ከአገሪቱ የኅዋ ምርምር መሥሪያ ቤት፤ «ሮስኮስሞስ» ጋር የረጅም ጊዜ ውል የተፈራረመ ሲሆን በውሉ መሠረት፤ ዘመናዊ የኅዋ ሥነ ቴክኒክን፤ መሣሪያውንና አገልግሎቱን በመጠቀም ፣የኅይል ምንጭ በሚገባ ተጠንቶና ፣ ተመርቶ ፣ ለመጓጓዣና ለሌላም ሌላ ዘመናዊ አግልግሎት እንዲውል ይደረጋል።

ይህ በአንዲህ እንዳለ፤ እ ጎ አ ከ 2002 ዓ ም ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሞስኮ፤ በኃይለኛ ጢስ መታፈኗና፣ የአየር ብክለቱን መጠን በ 10 እጥፍ ከፍ እንዳደረገው፤ አሌክሴይ ፖፒኮቭ የተባሉት የአየር ንጽህና ተቆጣጣሪው መሥሪያ ቤት ባለሙያ አስታወቀዋል። ። የአሳት አደጋ ተከላከዮች ከከተማይቱ ውጭ፣ ከበሰበሰ ቅጠልና ጭራሮ የተነሳውን ሰደድ እሳት በዛሬው ዕለት፤ በተሣካ ሁኔታ ለማጥፋት መቻላቸውን ቢያስታውቁም፤ሞስኮ ውስጥ በተከፈቱ መስኮቶች በኩል የሚገባ የከሰል ሽታ ፤ መኖሪያ ቤቶችን ፣ መሥሪያ ቤቶችንና ሬስቶራንቶችን ማወኩ ተገልጿል። ከትናንት በስቲያ፣ ሞስኮ ውስጥ የነበው ሙቀት 37,4 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እንደነበረና ይህም አዲስ ክብረ-ክብረወሰን የያዘ መሆኑ ተመልክቷል። የዛሬውም ሙቀት እጅግ ኀይለኛ መሆኑ ተነግሯል።

በርሊን፤ የዩኒቨርስቲዎች የድረ-ገጽ ደረጃ፤

ዩኒቨርስቲዎች ባላቸው ድር-ገጻዊ መረጃና ግንኙነት መጠን Webometrics ወይም Cybermetrics ከጀርመን ዩኒቨርስቲዎች መካከል Freie Universität Berlin የተሰኘው የበርሊን ከፍተኛ የትምህርት ተቋም(ዩኒቨርስቲ)፣ የአንደኛነቱን ቦታ መያዙ ተነገረ። ጀርመንኛ ከሚነገርባቸው አገሮች፤ ከ Zürich እና ቪየና ዩኒቨርስቲዎች ቀጥሎ፤ 3ኛ፤ በአጠቃላይ ከአውሮፓ 16ኛ ሲሆን፤ ከዓለም ውስጥ ደግሞ፣ የሳይንስ ተቋማት ካሏቸው 20,000 ገደማ ያህል ዩኒቨርስቲዎች 100ኛ መሆኑ ታውቋል።

ቦልዛኖ፤ በበረዶ ተቀብሮ የኖረው «ዖዚ»ና የዘር መለያው ምርምር፣

አውሮፓ ውስጥ በአልፕስ ተራሮች እ ጎ አ በ 1991 ዓ ም የተገኘው የ 5000 ዓመት ገደማ ዕድሜ ሳይኖረው እንዳልቀረ፤ የተነገረለት፤ ሥጋው ጅማቱና አጽሙ በተሟላ ሁኔታ የተገኘው «ዖዚ» የሚል ስያሜ የተሰጠው አጽም ከየትኞቹ የዘመኑ ሰዎች ጋር እንደሚዛመድ ፤ የዘር መለያው አሻራ በመመርመር ላይ መሆኑ ተገለጠ። ከ 5,000 ዓመት በፊት የነበረውንና በአሁኑ ዘመን ያለውን በሽታ በምርምር ለማነጻጸርም ይረዳል ተብሎ ይታመናል። የዖዚን የዘር መለያ አሻራና ዝምድናውን ከመጪው ዓመት ታኅሳስ ወር ማለቂያ በፊት መግለጽ እንደሚቻል ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ