የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋና የጌዲኦ ረሐብ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 15.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋና የጌዲኦ ረሐብ

ተገቢውን ትኩረት አላገኘም የተባለው የጌዲኦ መፈናቀል እና ረሐብ የብዙዎች መነጋገሪያ ከመኾን አልፎ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻን ቀስቅሷል። በአሜሪካ ሠራሹ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ 157 ሰዎች በአጠቃላይ የመሞታቸው ዜና መላ ዓለምን አስደንግጧል። በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎችንም እጅግ አሳዝኗል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:29

«ሰብአዊነት ይቅደም፤ ፍትሕ ለጌዲዮ»

ንብረትነቱ የኢትዮጵያ የኾነው አሜሪካ ሠራሹ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ባለፈው እሁድ ኢትዮጵያ ውስጥ ተከስክሶ 157 ሰዎች በአጠቃላይ የማለቃቸው ዜና መላ ዓለምን አስደንግጧል። በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎችንም እጅግ አሳዝኗል፤ በስፋትም አነጋግሯል። ተገቢውን ትኩረት አላገኘም የተባለው የጌዲኦ መፈናቀል እና ረሐብ የብዙዎች መነጋገሪያ ከመኾን አልፎ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻን ቀስቅሷል። የጌዲኦ ችግረኞችን ለመታደግ በማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች እንቅስቃሴ ከጀመሩ ወጣቶች መካከል ለማነጋገር ሞክረናል።   

የጌዲኦ መፈናቀልና ረሐብ

ከኦሮሚያ ክልል፤ ምዕራብ ጉጂ ዞን የተፈናቀሉት አደጋ ውስጥ የሚገኙ የጌዲኦ ተወላጆች በጌዲዮ ዞን ገደብ ወረዳ ጎቲቲt ቀበሌ ውስጥ በርካቶች በከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንደሚገኙ እየተነገረ ነው።  

ዘ ጋርዲያን የድረ-ገጽ ጋዜጣ እንደጻፈው እና ድር-ገጽ ላይ እንዳሰፈረው ጽሑፍ ከኾነ፦ «ጎቲ በተባለው መንደር አንድ ሰፈራ ውስጥ የሚገኙ 20-30,000 የጌዲኦ ተወላጆች ካለፈው ነሐሴ ወር አንስቶ የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት ከምንም በላይ ምግብ ተነፍገዋል።»

ሸገር 102.1 በበኩሉ ትዊተር ገጹ ላይ ባወጣው ዘገባ፦ በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን «ዜጎች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት» መጋለጣቸውን ጠቅሷል። «ከእርዳታ ጠባቂዎቹ መካከል ለሞት የሚያሰጋ ረሀብ የጠናባቸው እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል» ብሏል።

ጋዜጠኛ ብስራት መለሰ፦«ከ 6 ወር በፊት ጌዲኦ ዞን» እንደነበር በመግለጥ የፌስቡክ ጽሑፉን ያንደረድራል። «ያው ጋዜጠኛም አይደለሁ» ሲልም ይቀጥላል። «ወቅቱ 600 ሺ ተወላጆች የተፈናቀሉበት እና ለከፋ ችግር የተጋለጡበት ነበር። መሬት ላይ በርካታ ጌዴኦዎች ያለ በቂ እርዳታ ምክንያት በምግብ እጦት ሲጎሳቀሉ የምእራብ ጉጂ፣ የጌዴኦ እና አለም አቀፍ የርዳታ ተቋማት አስተዳደሮች፣ ጽ/ቤት ውስጥ የተጎጂን ቁጥር በመጨመር እና በመደለዝ በቁጥር ጫወታ ተጠምደው ሲራኮቱ ነበር። እጅግ ለም የሆነው ዞኑ ለልጆቹ መሆን አልቻለም። ዛሬም ርሃብ አለ። ዛሬም በራበው ሰው ፖለቲካ ይሰራል። ምግብ፣ ፍትህ በርሃብ ለሚሰቃዩ ጌዴኦዎች!» ብሏል። በፌስቡክ እና ትዊተር በርካቶች ዘንድ የደረሰው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘገባ በምግብ እጦት የተጎዱ የጌዲኦ ተወላጆች ላለፉት 8 ወራት ርዳታ እንዳልተደረገላቸው ይገልጣል።

«ፍትሕ ለጌዲዮ ሕዝብ» ፤ «ሕይወት ለማዳን እንረባረብ» የሚሉ ጥሪዎች በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በስፋት ተሰራጭቷል። መሥፍን በለው በትዊተር ገጹ፦ «ሰብአዊነት ይቅደም፤ ፍትሕ ለጌዲዮ» ሲል በእንግሊዝኛ ጽፏል።

ብሩክታይት በቀለ በፌስቡክ ገጿ ስለጌዲዮ መፈናቀል እና ረሐብ በተደጋጋሚ ሰፋ ያሉ ጽሑፎችን አቅርባለች። ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በአካባቢው እንደነበረች የገለጠችው ብሩክታይት ኹኔታውን እንዲህ ትገልጣለች።

«ዛሬ በ ጎቲ በነበረኝ ቆይታ ካየኋቸው ልቤን ከሰበሩት ነገሮች አንደኛና ዋነኛው ረሀብ ነው። ረሀብ እንደ ቅጠል እያረገፍቸው ነው። በተለይ እናቶች እና ህፃናት በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። በተዘዋወርኩባቸው መጠለያዎች ልክ እንደተመለከቱኝ እጅ እጄን እያዩ በጌዴኦኛ "dayyo Saggale uwi" በአማርኛ "እህት ምግብ ስጭን" የሚሉ ልጅ ያዘሉ እናቶች ድምፅ ከአይምሮዬ ሊወጣ አልቻለም።»

የ#እንደግፍ_እናካፍል የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የድጋፍ አሰባሳቢ ቡድን አባል ሰለሞን መንገሻ በፌስቡክ ገጹ ስለ ጌዲኦ ጽፏል። የክንዳቸው እና የጉንጫቸው ሥጋ ከአጥንታቸው ጋር የተጣበቁ አንዲት ሴትዮ እና የተኛ ጨቅላ አጠገብ የተቀመጠች ሌላ    አንዲት ከሲታ ልጅ የሚታዩበት ፎቶግራፍ አያይዟል። ይህን ፎሮግራፍ በርካቶች ተቀባብለውታል። ሌሎች ይህንኑ ፎቶ ከታፋው ጀምሮ እስከ ቁርጭምጭሚቱ ድረስ  እጅግ የቀጠኑ እግሮቹን ዘርግቶ የተቀመጠ ትንሽ ልጅ ከሚታይበት ሌላ ፎቶ ጋር አያይዘዋል። ፎቶግራፉ ላይ የትንሹ ልጅ ዐይኖች እና ቁንጮው ጎልተው ይታያሉ።  

ከሰለሞን ጋር እንደግፍ እናጋራ በሚል መርኅ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በርካታ የድጋፍ ዘመቻዎችን የምታስተባብረው ጋዜጠኛ ራሄል ገብረ እግዚአብሔርን በስልክ አነጋግረናታል። ለጌዲኦ ተወላጆች የምግብ እና የአልባሳት ድጋፎችን በቦታው ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ገልጣለች።

የ#እንደግፍ_እናካፍል ቡድን አባልት ጌዲኦ ለመሄድ መወሰናቸውን በፌስቡክ ገጹ የገለጠው ሰለሞን መንገሻ፦«እዚያ ህዝብ እርዳታ እንዳያገኝ ታግቶ በረሃብ እየተቀጣ እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ ዜጎች በርሃብ ተጎሳቁለው የሚታዩበትን ምስል ማየት ልብ ይሰብራል፡፡ ቶሎ የሚበስሉ የምግብ እህሎችን፣ ሩዝ ፣ ፓስታና ማካሮኒ፡...ወዘተ የምትችሉ ደግፉን፤ በአይነትም ይሁን በገንዘብ ለመደገፍ የምትፈልጉ በውስጥ መስመር አዋሩን ወይንም ደውሉልን» ሲል የስልክ ቊጥሮችን ፌስቡክ እና ትዊተር ገጹ ላይ አኑሯል።

ፖለቲከኛ ሙሉነህ ኢዩኤል፦«የቀዶ-ጥገና ክፍል ውስጥ አንዱ ያደነዝዛል ሌላኛው ይቆራርጣል። ይሄ ካልገባህ ምን ሊገባህ እንደሚችል አላውቅም! ደንዝዘን ሳለ የተቆረጠ ምን እንደሚመስል ከጌዴኦ በላይ ምስክር ከየት ይመጣል» የሚል ጽሑፍ ትዊተር ገጹ ላይ አስነብቧል።

አሜሪካ ሠራሹ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን

ሌላው በሳምንቱ አሁንም ድረስ በመላው ዓለም መነጋገሪያ ኾኖ የቆየው አሜሪካ ሠራሹ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ደብረዘይት/ቢሾፍቱ አቅራቢያ ተከስክሶ በአጠቃላይ የ157 ተሳፋሪዎችን ሕይወት መቅጠፉ ነው።

በአውሮፕላኑ አደጋ መላው ዓለም ከማዘኑ ባሻገር፦ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች እንዳይበሩ ወይም ወደ አየር ክልላቸው እንዳይገቡ እና እንዳያርፉ የሚከለክሉ ሃገራት ተበራክተዋል። ከ5o በላይ ሃገራት አውሮፕላኑ በአየር ክልላቸው እንዳይገባ የከለከሉ  ሃገራትን ፈለግ በመከተል ዩናይትድ ስቴትስም ረቡዕ እለት ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን እንዳይበር ያገዱትን አገሮች ተቀላቅላለች። የዩናይትድ ስቴትስ የፌደራል አቭየሽን አስተዳደር በእንግሊዘኛው ምህጻር FAA የወሰደውን ርምጃ የአውሮፕላኑ አምራች ቦይንግ ኩባንያ እደግፋለሁ ብሏል። ኾኖም ቦይንግ አውሮፕላኖቹ ችግር የለባቸውም ባይ ነው።

የሺወርቅ መኮንን፦ «አደጋዉ ልብ የሚሰብርና አሳዛኝ ነዉ፣ ለሞቱት እግዚአብሔር ነፍሳቸዉን ይማረዉ» የሚል አስተያየት በፌስቡክ ሰጥታለች። ዛኪር ሙዜማ ደግሞ፦«በጣም አዝነናል ለቤተሰቦቻቸዉ እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸዉ መፅናናትን እንመኛለን» ብሏል። መብረር በጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከተከሰከሰውና በአጠቃላይ ለ157 ተሳፋሪዎች ሞት ሰበብ ስለኾነው የኢትዮጵያ ቦይንግ 737 አውሮፕላን አደጋ በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ሐዘናቸውን በመግለጥ ላይ ናቸው።

«ለአዲስ አበባ ምን ይደረግ?»

ጋዜጠኛ እና የመብት ተሟጋች እስክንድር ነጋ በጠራው፦ «ለአዲስ አበባ ምን ይደረግ?» በሚል ስብሰባ እሁድ መጋቢት 1 ቀን፤ 2011 ዓም በአዲስ አበባ የተካሔደው ውይይትም መነጋገሪያ ነበር። በስብሰባው የተሳተፉ ታዳሚያን የከተማዋን አስተዳደር በብርቱ ወቅሰዋል። የከተማዋ አስተዳደር «በእርግጥ የነዋሪዎቹን ጥቅም እያስከበረ ነው ወይ?» የሚል ጥያቄም አንስተዋል። ከስብሰባው መልስ የታሰሩ ወጣቶች እንዲፈቱ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ዘመቻ ተጀምሮ የነበረ ሲኾን፤ ፖሊስ ያሰራቸውን ወጣቶች ብዙም ሳይቆይ መፍታቱን ይፋ አድርጓል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

 

Audios and videos on the topic