የቦኮ ሃራም ግሥጋሴ | አፍሪቃ | DW | 04.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የቦኮ ሃራም ግሥጋሴ

ናይጀሪያ ዉስጥ የሚንቀሳቀሰዉ እስላማዊ ፅንፈኛ ታጣቂ ቡድን የሚፈጽማቸዉን የኃይል ርምጃዎች እያጠናከረ በመሄድ ላይ ነዉ። በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል በያዝነዉ ሳምንት መጀመሪያ አንዳንድ ከተሞችን መቆጣጠሩ የሚነገርለት ይኸዉ ቡድን ቀጥሎ የቦርኖ ግዛት ዋና ከተማ ማይዱጉሪን ሊይዝ ይችላል የሚል ስጋትም ይሰማል።

ይህን ታጣቂ ቡድን የሀገሪቱ ጦር ኃይል መቆጣጠር እንዴት ተሳነዉ የሚለዉ ይብዙዎች ጥያቄ ነዉ። ሁኔታዉን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች በዉስጡ ያለዉ ያሠራር ብልሹነትና የበላይ ባለስልጣናቱ ለግል ጥቅምና ለገንዘብ መራኮት ያመጣዉ ጣጣ መሆኑን ይናገራሉ።

እንደናይጀሪያ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ከሆነ በወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አጀብ ወደሁለት መቶ የሚገመቱ በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ የፅንፈኛዉ ቦኮ ሀራም ተዋጊዎች ባለፈዉ ሰኞ ወደባማ ከተማ መጡ። ከናይጀሪያ መንግሥት ወታደሮች ጋ ተታኮሱና ወታደሮቹ 59ኙን ታጣቂዎች ሲገድሉ ከእነሱ ወገን ደግሞ 30 የሚሆኑት ቆሰሉ። በዘገባዎቹ መሠረትም አንድ የናይጀሪያ ተዋጊ ጀት የወገን ጦርን በስህተት በቦምብ በመደብደቡ በአካባቢዉ የሚገኘዉ የመንግሥት ሠራዊት ክፉኛ ተዳክሟል። በሺዎች የሚገመቱ ሲቪሎችና ወታደሮችም ከአካባቢዉ ለመሸሽ ተገደዋል። የአይን እማኞች እንደሚሉትም ከዚያን ቀን አንስቶም በሰሜን ናይጀሪያ ቦርኖ ግዛት የምትገኘዉ ባማ ከተማ በፅንፈኛ ታጣቂዎቹ ቁጥጥር ሥር ትገኛለት። በአንፃሩ የናይጀሪያ ጦር ኃይል ባማ ዉስጥ ደረሰ የተባለዉን ሽንፈት ያስተባብላል። እንደዉም ታጣቂዉን ቡድን እድል እንዳደረገና ቦርኖ ግዛትም ሆነ አካባቢዉ ከእጁ እንዳልወጣ ነዉ የሚገልጸዉ።

Flüchtlingslager in Bama, Nigeria

ኗሪዎች ከተማዋን ለቀዉ ሲሸሹ

ባማ ቦኮ ሀራም ከተቆጣጠራትና ከጥቂት ቀናት በፊት የኻሊፋ አስተዳደር ካወጀባት ከጎዉዛ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ናት። ከባማ ደግሞ ወደግዛቱ ዋና ከተማ ማይዱጉሪ ያለዉ ርቀት 70 ኪሎ ሜትር ብቻ ነዉ። የናይጀሪያ መንግሥት ጦር እየተዳከ ለመምጣቱ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ነዉ በብሪታንያዉ የቻተም ሀዉስ ተቋም የናይጀሪያ ጉዳይ አዋቂ ማርክ አንቶኒ ፔሩስ ደ ሞንተክሎስ የሚያስረዱት፤ ዋነኛዉም በከፍተኛ ባለስጣናትና የጦር አዛዦች የሚፈፀመዉ የገንዘብ ማጋበስ ነዉ።

«ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካታ ወንጀሎች ነበሩ። ወታደሮች በከፍተኛ ደረጃ በሚገኙ ባለስልጣናት በሚፈፀሙ የሙስና ተግባራት ተሰላችተዋል፤ ገንዘቡን ቦኮ ሃራምን በአግባቡ ለመዋጋት ከማዋል ይልቅ ራሳቸዉ የሚሰበስቡ በመሆናቸዉ።»

የናይጀሪያን የፀጥታ ክፍል ለማጠናከር በይፋ የሚመደበዉ በጀት ከሁለት ቢሊዮን ዩሮ በላይ ነዉ። ሆኖም በአሁኑ ወቅት የተቀረዉ ግን ከመቶ ሚሊዮን የሚያንስ መሆኑ ነዉ የተገለጸዉ። ከጥቂት ወራት በፊት የቦርኖ ግዛት አገረ ገዢ በሰሜን ናይጀሪያ የሚገኘዉ ሠራዊት ተገቢዉ ትጥቅ እንደሌለዉ በመግለጽ የማዕከላዊ መንግሥትን ድጋፍ ጠይቀዉ ነበር። የቀድሞዉ የሠራዊቱ አባል ሙሐመድ አብዱል በጦሩ ዉስጥ ስላለዉ ችግር የሚነገረዉ እዉነት መሆኑን ያረጋግጣል።»

«የመዋጊያ መሣሪያ የለም። የቦርኖ ግዛት አገረ ገዢ የናይጀሪያ ጦር በቂ ትጥቅ እንደሌለዉ ግልፅ አድርገዋል። የምንጠይቀዉ እንዴት መዋጋት እንችላለን ብለን ነዉ። መሣሪያ እንዲገዛ ገንዘብ የሚሰጥ ከሆነ፤ ለስንቅና ትጥቅ ገንዘብ የሚሰጥ ከሆነ ለምንደነዉ ታዲያ ለመዋጋት ብቃት የጠፋዉ? ምክንያቱም ከወንበዴዎች ጋ በዱላ ልትዋጋ አትችልም።»

የተየያዩ የመብት ተሟጋቾች የናይጀሪያ ጦር የሲቪሉን ደህንነት አላስጠበቀም ጥፋቶችን ይፈጽማል ሲሉ ይከሳሉ። የጦር ኃይሉ ከታጣቂዉ ቡድን ጋ በሚያደርገዉ ዓመታት የዘለቀ ዉጊያ እስካሁን ድል ያልቀናዉ የሲቪሉን ሕዝብ ትብብር ስለተነፈገ መሆኑን የሚገልፁም አሉ። ደ ሞንትክሎስም ከምንም በላይ የናይጀሪ ጦር የተለያዩ የኃይል ርምጃዎች በመዉሰዱ ምክንያትም ከኅብረተሰቡ ትብብር አያገኝም ባይ ናቸዉ።

ሂልከ ፊሸር /ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic