የቦኑ የአየር ንብረት ጉባኤ | ጤና እና አካባቢ | DW | 29.05.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የቦኑ የአየር ንብረት ጉባኤ

36ኛዉ የተመድ ዓለም ዓቀፍ የአየር ንብረት ለዉጥን የሚመለከት ጉባኤ እዚህ ጀርመን ቦን ከተማ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ተካሂዷል። ጉባኤዉ ባለፈዉ ህዳር ወር ደርበን ላይ በተካሄደዉ ድርድር የተደረሱ የመፍትሄ ሃሳቦችን በመያዝ በመጪዉ ዓመት

default

የቦኑ ጉባኤ ተሳታፊዎች በከፊል

በቀጠር ዶሃ ከተማ ለሚካሄደዉ ዓለም ዓቀፍ ስብሰባ ይደረስበታል ተብሎ ለሚታሰበዉ ስምምነት መንገድ ያመቻቻል በሚል ነዉ የተካሄደዉ። ደቡብ አፍሪቃ ደርበን ላይ የተካሄደዉ የተመድ ዓለም ዓቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ በመጪዉ የአዉሮጳዉያን ዓመት 2015ዓ,ም መንግስታትን የሚያግባባ ስምምነት ለማምጣት ዝግጅቱ እንዲጠናከር ተስማምቶ ነዉ የተደመደመዉ። ከስድስት ወራት በኋላ እዚህ ቦን ከተማ ጀርመን አገር ካለፈዉ ግንቦት 6 እስከ ግንቦት 17 ቀን 2004ዓ,ም ድረስ የተካሄደዉ ጉባኤ ደግሞ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመቆጣጠር ብሎም ለመግታት የታለሙ ስልቶች ተግባራዊነትን የሚረዳ፤ እንዲሁም የቴክኒክና የሳይንስ ድጋፍ የሚሰጡ አካላት ሊያደርጉ ይገባል ያላቸዉን ሃሳቦች እያነሳ በስፋት ተወያይቷል። ጤና ይስጥልኝ የዝግጅታችን ተከታታዮች እንደምን ሰነበታችሁ! ስለአየር ንብረት ለዉጥ በየደረጃዉ የተለያዩ ጉባኤዎች እየተካሄዱ በሚገኙበት በዚህ ወቅት የአየር ንብረት ለዉጡ በተለይ በድሃ አገራት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያስከተለ መሆኑ እየተነገረ ነዉ። 

የበለፀጉና በኢንዱስትሪዉ ያደጉ ሐገሮች መጠን ያጣዉ ከባቢ አየርን የሚያሞቁ ጋዞች ልቀት እልባት እንዲያገኝ ሲጠየቁ እነሱ በተራቸዉ፤ ዛሬ በመመንደግ ላይ ያሉት አዳጊ ሐገሮችም ከድርሻዉ ያንሱለት የሚል መከራከሪያ ሲያቀርቡ፤ በዚህ ምክንያትም የአደገኛ ጋዞች ወደከባቢ የአየር ልቀት ይህነዉ የሚባል አንዳች ገደብ ሳይደረግለት ይህን መጠን የሚደነግገዉ የኪዮቶ ዉል ከተቋጠረበት አንስቶ ከሚከስምበት ዓመት ላይ ተደርሷል። የያዝነዉ የአዉሮጳዉያን 2012ዓ,ም ለኪዮቶ ዉል የመጨረሻነቱ ተደጋግሞ በመገለፁም የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ፍሬ ያለዉ ዉጤት ከየጉባኤዉ ሲጠብቁ ቆይተዋል። እዚህ ቦን ከተማ ለሁለት ሳምንታት የተካሄደዉ ስብሰባ  ለመጪዉ ቀጠር ዶሃ ለሚካሄደዉ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ የተለያዩ ሃሳቦችን አቀራርቦ፤ የተካረሩ ወገኖችን አግባብቶ ለ2015ዓ,ም የጋራ ማግባቢያ ያዘጋጃል የሚል ተስፋ ነበር። ምድርን ለከፍተኛ ሙቀት የዳረጉ አደገኛ ጋዞችን ለመቀነስ ይረዳሉ በተባሉ ነጥቦች ላይ ከመስማማት ይልቅ ዩናይትድ ስቴትስና አዉሮጳ ሌሎች የዉይይቱ ተሳታፊዎች ከተባለዉ ለመድረስ እንቅፋት ሆኑብን ሲሉ ክሳቸዉን አሰምተዋል። ከ195 ሐገሮች የተሰባሰቡ ተሳታፊዎችን ከሁለት የከፈለዉ ሁኔታም የቻይና ተደራዳሪ እንደጠቆሙት ከሆነ ደርበን ደቡብ አፍሪቃ ላይ ከስምምነት የተደረሰዉ ለቀጣይ አራት ዓመት የሚያገለግል ሁሉን የሚያግባባ ዉል መቅረፁ ላይ ከማተኮር ይልቅ በኢንዱስትሪ ያደጉት ሐገሮች በተለይ አዳጊ ሐገሮች ብክለት በመቀነሱ ግንባር ቀደም ይሁኑ ሲሉ አይናቸዉን ከእነሱ ላይ አለማንሳታቸዉ ነዉ።

በዚህም ምክንያት ጉባኤዉ ባደጉትና በማደግ ላይ ባሉት ሐገሮች መካከል የሃሳብ ልዩነት ታይቶበታል። ፈጣን እድገት የሚያሳዩት ቻይና እና መሰሎቿ ምዕራቡና ያደገዉ ዓለም ከባቢ አየሩን ለረዥም ጊዜ ሲበክሉ የኖሩ ናቸዉና ብክለቱን ለመከላከል አብዛኛዉን የኃላፊነት ድርሻ ይሸከሙ ባይናቸዉ። ይህም ለቀጣይ ልዩነቶችን በማቀራረብና ተደራዳሪዎች በማግባባት ለስምምነት እንዲያደርስ የታሰበዉ ኮሚቴን ተግባር እንዳከበደዉ የተመድ የአየር ንብረት ጉዳይ የበላይ ክርስቲና ፊጎርስ አመልክተዋል። ሌላዉ ቀርቶ ይህ ኮሚቴ በማን ሊቀመንበርነት ይመራ የሚለዉ ሳይቀር አከራካሪ እንደነበር ታይቷል። ቻይናና ተከታዮቿ ኮሚቴዉ በህንድ ሊቀመንበርነት እንዲመራ ይሻሉ፤ በሌላዉ ወገን ደግሞ ኖርዌይና የካረቢያን አካል የሆነችዉ ትሪኒዳድና ቶቤጎ ተሰልፈዋል። የጠነከረዉ ፍጥጫም በጉባኤዉ አካሄድ ስርዓት ያልተለመደ እና መግባባት የጠፋበት እንደሆነ ነዉ የደቡብ አፍሪቃ የአየር ንብረት ጉዳይ ተወካይ ናዚፖ ጆይስ የገለጹት።

UN-Klimakonferenz in Bonn Christiana Figueres

ክርስቲና ፊጎርስ

በአንድ ወገን ጉባኤዉ እንደታሰበዉ ለዶሃዉ ስብሰባ ሊቀርብ የሚችል የድርድር ዉጤት ለመጨበጥ ሲጥር፤ በሌላ በኩል የአየር ንብረት ለዉጥ መዘዝ በተለይ በደሃ ሐገሮች ላይ የሚያስከትለዉን ተፅዕኖ ቀጥሏል። የድርድሩና ዉይይቱ ዓላማም አንድም ከፍ እያለ የሄለደዉን የዓለምን የሙቀት መጠን መግታት ሲሆን ከተለወጠዉ የአየር ንብረት ጋ ተላምዶ ምግብና ዉሃን የማግኘት አቅምን የማረጋገጡን ስልት መቀየስም ሌላዉ ነዉ።

ናይሮቢ የሚገኘዉ የተመድ የአካባቢ ጥበቃ መርሃግብር ኃላፊ ኬትዝ አልቨርሰን ከአየር ንብረት ለዉጥ ዉይይቶች ሁሉ ከለዉጡ ጋ ተላምዶ የመኖሩ ጉዳይ ዉጤት ሊታይበት የሚችል ነዉ ባይናቸዉ፤

«መላመድ የሚለዉ ሃሳብ በአንዳንድ አካባቢ ትርጉም ያለዉ መሻሻል ያየንበት ጉዳይ ነዉ፤ የበለጠ ተጨባጭ፤ በተጨማሪም በአዳጊ ሐገሮች ከልማት፤ ከኤኮኖሚ እድገት እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋ በጣም የሚተሳሰር ነዉ። የኤኮኖሚ እድገት ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃን ያካትታል ያም አረንጓዴ ኤኮኖሚ ነዉ። ስለዚህ በእኔ እይታ ተላምዶ መኖር እጅግ በቅርብ የተንጠለጠለ ፍሬ ማለት ነዉ፤ ማለትም ከዘርፈ ብዙዉ የአየር ንብረት ለዉጥ መከላከያ ፈተናዎች ይልቅ ፈጥነን ልናሳካዉ የምንችል ዓይነት ነዉ።»

እሳቸዉ እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ ይህ የመላመድ ርምጃ ዓለም ዓቀፍ ግንዛቤና ተቀባይነት ይኑረዉ እንጂ እያንዳንዱ ሐገር በራሱ አካባቢያዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ሊያከናዉነዉ ይገባል። በአንዱ አካባቢ የሚሰራዉ ስልት ለሌላኛዉ ላይሆን ይችላልና፤

«ተላምዶ የመኖሩ ርምጃ የግድ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በሚቀመጠዉ መመሪያ መሠረት ሊሄድ አይችልም፤ ይልቁንም የአካባቢዉ ሁኔታ ይመረኮዛል። ይህም የመላመድ አካሄዱ የአካባቢዉን ችግር እንዲሁም የአየር ንብረት አጠቃላይ ይዞታ፤ እንዲሁም የአካባቢዉ ኅብረተሰብን ለጉዳት የመጋለጥ ሁኔታን ያካትታል። የመላመድን ሂደት ስናከናዉን የምናገናኘዉ በአካባቢዉ ካለ ሁኔታ ጋ በማያያዝ ነዉ፤ ለምሳሌ በአርክቲክ አካባቢ ባህር ላይ የበረዶዉ እየቀለጠ መሸሽ፤ ወይም ዝቅ ባለ አካባቢ የሚገኙ ደሴቶች የከበባቸዉ የባህር ዉሃ መጠን ከፍ ማለት ሊሆን ይችላል። ከዚህ ሌላ ሰዎች ያላስተዋሉት ነገር የባህር ጠለል ከፍ ማለት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚታይ አይደለም። ለምሳሌ ላለፉት 20ዓመታት የዩናይትድ ስቴትስ የባህር ዳርቻ የባህር ዉሃዉ ከፍታ እየቀነሰ ነዉ የሄደዉ።»

በኢንዱስትሪ የበለፀጉት ሐገሮች አዳጊ ሐገሮች ከአየር ንብረት ለዉጡ ጋ ተላምደዉ ለመኖር እንዲችሉ ለዚህ ተግባር የሚዉል በየዓመቱ አንድ መቶ ሺ ቢሊዮን ዶላር ከአዉሮጳዉያኑ 2020ዓ,ም አንስቶ ለመለገስ ቃል ገብተዋል። ገንዘቡ እንዴትና ከየት ይመጣል የሚል ጥያቄ ቢነሳም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ መፍትሄ የሚያስፈልገዉ እንደሆነ ይታመንበታል። ከዚህ የሚበልጠዉና እጅግ ከፍተኛዉ አሳሳቢ ጉዳይ ግን በድርቅ፤ በጎርፍ፤ በሚጨነግፉ ምርቶች፤ እንዲሁም ከፍታዉ እየጨመረ በሚያሰጋዉ የዉቅያኖስ ዉሃ የሚቸገሩ ሐገሮች ገንዘቡን እንዴት በዉጤታማነት ለዚህ ያዉሉታል የሚለዉ ነዉ። 

ፋጡማ ዴንቶን ሴኔጋል የሚገኘዉ የዓለም ዓቀፉ የልማት ምርምር ማዕከል አስተባባሪ ናቸዉ። እሳቸዉ የሚያንቀሳቅሱት መርሃግብር የሚያተኩረዉ አፍሪቃ ዉስጥ አነስተኛ ገበሬዎች ለአየር ንብረት ለዉጥ የሚጋለጡበት ሁኔታ የማጥናት አቅምን ማጠናከር ላይ ነዉ። ዴንቶን እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ በፍጥነት የሚለዋወጠዉን የአየር ንብረት ሁኔታ አጥንቶና ተገንዝቦ ችግሩን የመቋቋሚያ ስልትን መቀየስ ከገበሬዉ ባህላዊ እዉቀት አቅም በላይ በመሆኑ ያንን የሚያካሂዱበትን መረጃ አሰባስቦ ለእነሱ በሚበጅ መልኩ የሚያቀርብላቸዉ አካል የግድ ያስፈልጋል።

«ገበሬዎች መቼ መትከል ወይም መዝራት እንዳለባቸዉ የሚጠቁም እጅግ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መረጃ ነዉ የሚፈልጉት። የአዝመራ ወቅት በምን ያህል ጊዜ ያበቃል፤ በድርቅ ወቅት እንዴት ዓይነት እህል መዝራት ይበጃል፤ የአፈሩን ለምነትስ እንዴት ማሻሻል ይቻላል፤ አፈር ጨዋማ ሲሆንስ ምን መደረግ ይኖርበታል፤ በባህር ዳርቻ ጎርፍ የአፈሩን ለምነት በሚጠራርገዉ ጊዜ አካባቢዉ ጨዋማ ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ መትከልም ሆነ ማምረት አይችሉም። እነሱ የሚፈልጉት ሳይንስ አንዳች ተግባራዊ መፍትሄ እንዲሰጣቸዉ እና ምን ሊመጣ ይችላል ብለዉ እንዲጠብቁ እንዲጠቁማቸዉ ነዉ።»

እርግጥ ነዉ በአየር ንብረት ለዉጥ ክፉኛ የተጋለጡ አርሶ አደሮች ብቻ ሳይሆኑ ባጠቃላይ ህይወታቸዉ በግብርናዉ ላይ የተመሠረቱ ማኅበረሰቦችም ሆኑ ሐገሮች እንዲህ ላለዉ መረጃ መጓጓታቸዉ አይቀርም። ይህ ደግሞ ምርምር ነዉና ጠቀም ያለ ገንዘብ መጠየቁ ግድ ነዉ። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ የአየር ንብረት ጉዳይ ድርድሮች በይበልጥ በለዉጡ ለሚጎዱ ወገኖች ሲባል ትኩረታቸዉን ከአየር ንብረት ለዉጥ ጋ ተላምዶ እንዴት መኖር ይቻላል በሚለዉ ላይ ቢያደርጉ መልካም እንደሆነ የሚያሳስቡት ፋጡማ ዱንቶን፤ ለዚህ የሚሆን ገንዘብ እንመድባለን የሚሉት ለጋሾች ቃላቸዉን ሊያከብሩ ይገባል ይላሉ፤

«ሳይንስ የአየር ንብረት ለዉጥ በተለያዩ መንገዶች ምን ያህል የሰዉ ልጅን ደህንነት እንደሚፈታተን እጅግ ብዙ ጥሩ ጥሩ መረጃዎችን ሰጥቶናል። ስለዚህ ተላምዶ ለመኖር ለሚባለዉ አማራጭ የሚዉሉ በርከት ያሉ የገንዘብ ርዳታዎች ሊዉሉ ይገባል። በዚህ ረገድ ከበለፀጉት ሐገራት ይበልጥ ቁርጠኝነት የተሞላዉ ርምጃ ማየት እንፈልጋለን። በጥቅሉ ሲታይ ይህ የአንድ ሐገር ብቻ ችግር አይደለም፤ ይልቁንም የሰዉን ዘር በሙሉ የሚመለከት ጉዳይ ነዉ። ስለዚህም ነገሮች አሁን ካለዉ በተሻለ ፍጥነት ሁኔታዎች መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸዉ ማስተዋል ይገባል።»

የአየር ንብረት ለዉጥ ከሚያስከትላቸዉ ተፅዕኖዎች ጋ ተላምዶ ለመኖር ገንዘብ ማስፈለጉ ተጎጂዎቹ ሐገሮች ደጋግመዉ በየጉባኤዉ ሲያነሱ ይስተዋላል።

ችግሩ ግን የገንዘቡ ምንጩ ብቻ አይደለም። በጀርመን የልማት ተቋም DIE ዉስጥ የአየር ንብረት ፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት ፔተር ፓዉቭ እንደሚሉት ከሆነ እንኳን አዲስ የእርዳታ በጀት ሊያዝ፤ አንዳንድ ሐገሮች በእጃቸዉ የሚገኘዉን የልገሳ ገንዘብ በአግባቡ እንዴትሥራ ላይ ማዋል እንደሚቻል የሚያዉቁ ሰዎች እና ራሱ ግንዛቤዉም የላቸዉም፤

«አሁን ከሚከሰተዉ ሁኔታ እንኳ ስንፈትሸዉ፤ ፈጥኖ ለሚገኘዉ የገንዘብ ድጎማ፤ አብዛኞቹ አዳጊ ሐገሮች አንድ ፕሮጀክት የመቅረፅ ወይም ይህን ገንዘብ ለማግኘት የሚያስችል አቅም የላቸዉም። ይህ ዋነኛ ችግር ነዉ። ፕሮጀክት የመቅረፅ አቅማቸዉን ማዳበር፤ የገንዘብ ርዳታዉን አግኝተዉ መላመዱን ለመጀመር እንዴት ነዉ እነዚህ ሐገሮች በዚህ ረገድ ሊረዱ የሚችሉት? ባለፉት አስርት ዓመታት በእነዚህ ሐገሮች በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተቋቁመዋል፤ እነዚህ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በዚህ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። የግሉ ዘርፍም ከፍተኛ ሚና ሊኖረዉ ይችላል። የአካባቢና ንዑስ ብሄራዊ መንግስታትም በዚህ ረገድ ድርሻ አላቸዉ። በአሁኑ ወቅት የመጣላቸዉን የአየር ንብረት ለዉጥ መቋቋሚያ የገንዘብ ርዳታ በአግባቡ ለመጠቀም ያዳገታቸዉ በርካታ ሐገሮች መኖራቸዉን አዉቃለሁ።»

ገንዘቡን ለመጠቀም አዳጊ አገሮች አቅሙ የላቸዉም፤ የቀረበላቸዉንም በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋል ያዳግታቸዋል ቢባልም ገንዘቡ በእጃቸዉ የገባ ሐገሮች ደግሞ ለረጂዎቻቸዉ ማቅረብ የሚገባቸዉ ወሳኝ መረጃ ማስፈልጉንም ፓዉቭ ያሳስባሉ፤

«የበለፀጉ ሐገሮችን የቀረጥ ከፋይ ዜጎች ገንዘብ የሚነካ በመሆኑ ለጋሽ ሐገሮች ዉጤቱን ለዜጎቻቸዉ ማሳየት ይፈልጋሉ። ግልፅ ዉጤት የሚያሳዩ ፕሮጀክቶችን የማቅረቡ ነገር ደግሞ እጅግ አዳጋች ነዉ። ስለዚህም የሚሠሩትን ሥራዎች ከነዉጤታቸዉ ግልፅ በሆነ መልኩ ማቅረብ ከሚችሉ አጋሮች ጋ መሥራት አስፈላጊ ነዉ።»

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic