የቦስኮ ንታጋንዳ የፍርድ ሒደት | አፍሪቃ | DW | 05.09.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የቦስኮ ንታጋንዳ የፍርድ ሒደት

በጦር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው ቦስኮ ንታጋንዳ ለፍርድ ቤቱ ዳኛ በሀገራቸው ሠላም ለማስፈን የታገሉ ወታደር መኾናቸውን ገልጠዋል። አቃቤሕግ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጦር አበጋዝን በ18 የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ከሷል። ቦስኮ ንታጋንዳ በአስገድዶ መድፈር፣ ግድያ እና ሕፃናትን ለውትድርና መልምሎ በጦርነት በማሳተፍ ወንጀሎች ነው የተከሰሱት።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 06:06
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
06:06 ደቂቃ

የቦስኮ ንታጋንዳ የፍርድ ሒደት

«ጨፍጫፊው» የሚል ቅፅል የተሰጣቸው የኮንጎው የጦር አበጋዝ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 እጃቸውን ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ከሠጡበኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ፊት ክሳቸውን አስተባብለዋል። በአስተርጓሚያቸው በኩል ሐሳባቸውን የገለጡት የ41 ዓመቱ ጎልማሳ ቦስኮ ንታጋንዳ ስማቸው ላይ የተለጠፈው ቅጽል እንደማይወክላቸው አስታውቀዋል።

«መጥፎ ስም እንዳለው ነፍሰ-ገዳይ ጨፍጫፊው እየተባልኩ ነው፤ ግን እኔ እንደእዛ አይደለሁም። ትናንት በአቃቢት ሕጓ የተገለጠው ዓይነት ቦስኮ ንታጋንዳ አይደለሁም።»

በእርግጥም አቃቤያነ-ሕግ «እጅግ ኃይለኛ እና አስፈሪ» የሚባሉት ቦስኮ ንታጋንዳን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎችን ኢቱሪ በተባለው አካባቢ ፈጅተዋል ሲሉ ረቡዕ ዕለት ከሰዋቸዋል። ግድያውንም ኮንጎ ውስጥ የዛሬ 12 እና 13 ዓመት ግድም ፈጽመዋል ብለዋል። የጦር አበጋዙ ሐብት ለማጋበስ እና ኃይላቸውን ለማጠናከር ሲሉ በተቆጣጠሩት አካባቢ የጎሣ ግጭት እንዲቀሰቀስ አድርገዋል ብለዋል።

በቦስኮ ንታጋንዳ ወታደሮች ጥቃት እና በደል ለደረሰባቸው ሰለባዎች ቆመው የሚከራከሩት አቃቢት-ሕግ ሣራህ ፔሌት ደምበኞቻቸው በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ በርካታ በደሎች እንደደረሰባቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድዋል።

«ደምበኞቻችን በአጠቃላይ ማለት ይቻላል በአሁኑ ወቅት እጅግ ለአደጋ እንደተጋለጡ ናቸው። መፃዔ ዕድላቸውን አለያም ኢቱሪ ውስጥ የጎሣ ግጭት ሰለባ የኾኑ ልጆቻቸውን በተመለከተ ጭላንጭል ተስፋ ነው ያላቸው»

አቃቢት-ሕግ ሣራህ ፔሌት ወደ 300 የሚጠጉ ሕፃናት ወታደሮችን ወክለው ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት። ወታደሮቹ እጅግ በፍርኃት የተዋጡ በመኾናቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ መፈለጋቸውን ተናግረዋል። እናም ቆመው የሚከራከሩላቸውን ወታደሮች በስም ሳይኾን በቁጥር መጥቀስ እንደመረጡ አስረድተዋል። የቦስኮ ንታጋንዳ ጠበቆች በበኩላቸው የምስክሮቹ ፍፁም ምሥጢራዊነት በፍርድ ሒደቱ ደምበኛቸው ፍትኅ እንዳይጎናጸፉ ያደርጋል ሲሉ ተከራክረዋል።

በፍርድ ሒደቱ ስማቸው ባይጠቀስም የቦስኮ ንታጋንዳ ወጣት ምልምል ወታደሮች ናቸው የተባሉ ምስክሮችን አቤቱታ ጭምር አቃቤያነ-ሕግ አቅርቧል። በጦር አበጋዙ ትዕዛዝ ስር ልጆቹ የወሲብ ጥቃትተፈፀሞባቸዋል ተብሏል። ቦስኮ ንታጋንዳ በገዛ ወታደሮቻቸውላይ የጦር ወንጀል የፈፀሙ በሚል በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የተከሰሱ የመጀመሪያው ሰው ኾነዋል።

ሶፕሮን የተባሉት ሌላ አቃቤ-ሕግ ደግሞ ደምበኞቻቸው ላይ የደረሰው መከራ ዕድሜ እና ፆታ ሳይለይ በኹሉም ላይ መኾኑን አስረድተዋል።

«እኔ የምወክላቸው ሠለባዎች አረመኔያዊ የኾነ ጥቃት ነው የደረሰባቸው። ተደብድበዋል፣ ቁም ስቅል ተፈጽሞባቸዋል፣ ተደፍረዋል። ይኽ ድርጊት የተፈፀመው ምንም ልዩነት ሳይኖር በኹሉም፦ በሴቶች፣ ዕድሜ በገፉ ወንዶች፣ በሕፃናት እና አካል ጉዳተኞች ላይ ነው።»

ኾኖም ቦስኮ ንታጋንዳ ለዐሥር ደቂቃ በዘለቀው ንግግራቸው የጎሣ ግጭት የፈጠሩ ወንጀለኛ አለመኾናቸውን አስረግጠው ተናግረዋል። ይልቁንስ በኢቱሪ አካባቢ ሠፍኖ የነበረውን ውጥንቅጥ እና አለመረጋጋት ሥርዓት ለማስያዝ የዘመቱ ወታደር መኾናቸውን በአጽንዖት ገልጠዋል። ተከሳሹ ለስለስ ባለው አንደበታቸው በአስተርጓሚያቸው በኩል ለማስረዳት ሞክረዋል።

«እንደወታደር ምንጊዜም እዋጋ የነበረው ወታደሮችን ነው እንጂ ሲቪሎችን አልነበረም። እንደውም ሲቪሎችን ከለላ እሰጣቸው ነበር። ወንጀለኛ አይደለሁም።»

Kindersoldat in Demokratische Republik Kongo

የእኚህ ጦር አበጋዝ ጠበቃዎች ደምበኛቸው ፍትኃዊ የፍርድ ሒደት ያገኛሉ ብለው እንደማያስቡ ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ ገልጠዋል። ሰውዬው የወጣላቸው «ጨፍጫፊው» የሚለው ቅጽል እንደማይገባቸው ይልቁንስ የተዋጣላቸው የጦር መሪ መኾናቸውን ለማስረዳት ሞክረዋል። ደምበኛቸው እንደቀረበባቸው ክስ ኢቱሪ በተባለው አካባቢ ፍላጎታቸው ሐብት እና ኃይልን የማጠናከር ሳይሆን ወታደራዊ ብቻ እንደነበረም አብራርተዋል።

አቃቢት-ሕግ ሣራ ፔሌት ግን ከ300 ሕፃናት ወታደሮች መካከል አብዛኞቹ ሴቶች እንደኾኑ እና ከፍተኛ በደል እንደደረሰባቸው ተናግረዋል። ብዙዎቹ ሴት ሕፃናት ወታደሮችየአስገድዶ መደፈር ወንጀል ተፈጽሞባቸው ያረገዙ መኾናቸውን፤ በቤተሰቦቻቸው ዘንድም መገለል የደረሰባቸው እንደሆኑ ጠቅሰዋል። ከነዚህ ሕፃናት ወታደሮች የተወለዱ ሕፃናት ወላጅ አልባ ብቻ ሳይኾኑ አባታቸውን የማያውቁ መኾናቸው በደሉን መሪር ያደርገዋል ሲሉም ለፍርድ ቤቱ አክለዋል።

ቦስኮ ንታጋንዳ ግን በአቃቤያነ-ሕግ የቀረበባቸውን የወንጀል ክስ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አድርገዋል። በቦስኮ ንታግንዳ ላይ የመጀመሪያውን ምስክር ለመስማት ለማክሰኞ፤ መስከረም 4 ቀን፣ 2007 ዓም ቀጠሮ ተይዟል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic