የቦስተኑ የቦምብ አደጋና የፀጥታ ስጋት | ዓለም | DW | 16.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የቦስተኑ የቦምብ አደጋና የፀጥታ ስጋት

ትናንት 27 ሺህ ሯጮች በተሳተፉበት ማራቶን በወንዶች ሌሊሳ ዴሲሳ በአንደኛነት በሴቶች ደግሞ መሠረት ኃይሉ በሁለተኛነት አጠናቀዋል ። ኢትዮጵያዊው ጀግና በድል የክብር ሪቫኑን በጥሶ ካለፈ ከ ሁለት ሰዓትት በኋላ ከሰአት በኋላ ከቀኑ 8 ሰአት ከ 45 ላይ ከመጨረሻው የማሸነፊያ መሥመር በግራ በኩል ታላቅ ፍንዳታ ተሰማ ።

ኢትዮጵያዊው አትሌት ባሸነፈበት አመታዊው የቦስተን ማራቶን በፈነዱ 2 ቦምቦች 3 ሰዎች ከተገደሉና ወደ 141 ቀላልና ከባድ የመቁሰል አደጋ ከደረሰባቸው በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ ዋና ዋና ከተሞች የፀጥታ ጥበቃ ተጠናክሯል  ። ለፍንዳታው ሃላፊነቱን የወሰደ ወገን የለም ።  ፖሊስ የማዕከላዊ ቦስተንን ሰፊ አካባቢ አጥሮ  ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ላይ ነው ። ከተጀመረ ትናንት 116 አመታትን ያስቆጠረው የቦስተን ማራቶን የአሜሪካኖች በተለይም በምሥራቅ ማሳቹሴትስ ግዛት ውስጥ የምትገኘው የቦስተን ከተማ ክብርና ኩራት ነው ። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የዚህ ማራቶን የዘወትር ተሳታፊዎችን ፋጡማ ሮባና አበበ መኮንንን ጨምሮ በርካቶች የድል ባለቤቶች ጭምር የሆኑባት ከተማ ናት ።

ትናንት 27 ሺህ ሯጮች በተሳተፉበት ማራቶን በወንዶች ሌሊሳ ዴሲሳ በአንደኛነት በሴቶች ደግሞ መሠረት ኃይሉ በሁለተኛነት አጠናቀዋል ። ኢትዮጵያዊው ጀግና በድል የክብር ሪቫኑን በጥሶ ካለፈ ከ ሁለት ሰዓታት በኋላ ከቀኑ 8 ሰአት ከ 45 ላይ ከመጨረሻው የማሸነፊያ መሥመር በግራ በኩል ታላቅ ፍንዳታ ተሰማ ። ከ 15 ሰኮንዶች በኋላ ደግሞ ከመንገድ በስተቀኝ ሌላ ፍንዳታ አካባቢውን አናወጠው ከዚያ በኋላ የነበረው እንዳልነበር ሆኖ አትሌቶቹም ታዳሚ ተመልካቹም ራሳቸውን ለማዳን ሩጫ ሆነ ። ይሄ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የ8 ዓመት ህፃንን ጨምሮ በዚህ አደጋ የ3 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል ። 141 ሰዎች ደግሞ በሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን ከመካከላቸው 17 በአስጊ 27 ቱ ደግሞ በአደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ። ከጥቃቱ በኋላ ኒውዮርክና ዋሽንግተንን ጨምሮ ታላላቅ የአሜሪካ ከተሞች ውስጥ ጥበቃው ተጠናክሯል ። ለወትሮው በጎብኝዎች በሚጨናነቀው በዋይት ሃውስ በር ላይ የሚያልፈው መንገድም ተዘግቷል ። ትናንት ማምሻውን ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ለአሜሪካን ህዝብ በሰጡት አጭር መግለጫ  ፊደራል መንግሥት ለቦስተንና ለአካባቢው ህዝብ አስፈላጊውን ድጋፍ

USA Anschlag Boston Marathon Explosion Obama

ባራክ ኦባማ

እንደሚያደርግ ገልፀዋል ። መንግሥት በጥቃቱ ጠንሳሾች ላይም ተገቢውን ፍትህ እንደሚሰጥም ቃል ገብተዋል ። «አትሳሳቱ የጥቃቱን ምንጭ እንደርስበታለን ። ይህን ማንና ለምን እንዳደረገ እንደርስበታለን ። የትኛውም ተጠያቂ ግለሰብ ወይም ቡድን የፍትህን ሙሉ ክብደት ይሸከማል »

ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የቦምብ ጥቃቱን በመግለጫቸው ሽብር ብለው አይጥሩት እንጂ ሌሎች ከፍተኛ የአሜሪካን  ባለሥልጣናትና የደህንነት ሰዎች እንዲሁም መገናኛ ብዙሃን ጭምር ሌላ የሽብር ጥቃት አሜሪካንን ማናወጡ ሲገልጽ ነው የዋሉት ።  ጥቃቱ በሃገር ውስጥ አለያም በውጭ ኃይል መታቀድ አለመታቀዱ ግን ገና አለየለትም የቦስተን ፖሊስ ሌሎች 3 ቦምቦችን አግኝቶ ማክሸፉን ተናግሯል ። ከሽብር ጥቃት በኋላ ቦስተን በብሔራዊ በፌደራልና በከተማዋ ልዩ ኃይሎች ወታደሮችና ፖሊሶች እየተጠበቀች መሆኑን የቦስተን ከተማ ነዋሪና በየአመቱ የኢትዮጵያውያን አትሌቶችን መስተንግዶ የሚያስተባብሩት አቶ መሰለ ክፍሌ ለዶቼቬለ አስታውቀዋል « የከተማይቱ ዋና ዋና መንገዶች ተዘግተዋል ።

USA Anschlag Boston Marathon Explosion

2ተኛው ቦምብ ከፈነዳ በኋላ

ከተማው በሙሉ ፣ ከፍተኛ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ቦስተን አካባቢ በጠቅላላው ቁልፍ የሆኑት ቦታዎች በወታደር ተከበዋል  ። ትምህርት ቤቶች በሙሉ እየተጠበቁ ነው ። ማዘጋጃ ቤቱ አካባቢ መኪና ማቆም አትችልም ። ከባድ መሣሪያ የታጠቁ በተጠንቀቅ ናቸው ።»

እስካሁን ድረስ ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው የለም ። ሆኖም በፍንዳታው በእግሩ ላይ ጉዳት የደረሰበት አንድ የሳውዲ አረቢያ ዜጋ በሚታከምበት ሆስፒታል ውስጥ በጥበቃ ሥር መሆኑ ተዘግቧል ። አንዳንድ የሃገር ውስጥ ዘገባዎች ፖሊስ ከአደጋው ጋር በተያያዘ ከቦስተን ሰሜን ምሥራቅ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ አንድ የመኖሪያ ህንፃ መፈተሹን ቢዘግቡም የአሜሪካን የፌደራል ምርመራ ቢሮ ቃል አቀባይ ግን ለዘገባው ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልሰጡም ። ከቦስተኑ አደጋ በኋላ በአለም ዙሪያ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ጥበቃዎች መጠናከራቸውና እንደሚጠናከሩም ነው የተገለፀው ። ምንም እንኳን በቦስተን ማራቶን አደጋ ቢደርስም ለፊታችን እሁድ የታቀደው የለንደን ማራቶን እንደታሰበው እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል ። ባለሥልጣናት የፀጥታ ጥበቃውን እንደገና እንደሚፈተሹ ተናግረዋል ። የእሁዱ የማድሪድ ማራቶንም በተያዘው እቅድ እንደሚቀጥል ተነግሯል ።

USA Anschlag Boston Marathon Explosion Verletzte

በአደጋው የተጎዱ ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ

የፊታችን ነሐሴ የሚካሄደው የአለም አትሌትክስ ሻምፕዮና እንዲሁም እጎአ የ2014 የክረምት ኦሎምፒክ አዘጋጅ ሩስያ በበኩሏ የፀጥታ እርምጃዎችን እንደምታጠናክር አስታውቃለች ። የትናንቱን ጥቃት ጭካኔ የተሞላበት ሲሉ ያወገዙት  የሩስያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን  ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት  ባራክ ኦባማ  የሃዘን መግለጫ አስተላልፈዋል ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ሠላማዊውን የስፖርት ውድድር ያወኩትን ሰዎች አውግዘው ጥፋተኞቹ ለፍርድ ይቀርባሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል ።  ኢጣልያም ጥቃቱን አውግዛለች ። የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ለቦስተኑ ካርዲናል የሃዘን መግለጫ አስተላልፈዋል ።

አበበ ፈለቀ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic