የቦሪስ ጆንሰን ድልና ቀሪ የብሬግዚት ተግዳሮቶች | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 17.12.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የቦሪስ ጆንሰን ድልና ቀሪ የብሬግዚት ተግዳሮቶች

የብሪታንያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ከ650ው የብሪታንያ ምክር ቤት መቀመጫዎች 365ቱን በማሸነፍ ከፍተኛ ድል መቀዳጀቱ ሊቀመንበሩ ቦሪስ ጆንሰን ብሬግዚትን ያለ ተቀናቃኝ እንዲያሳኩ መንገዱን ጠርጎላቸዋል።ፓርቲው ከ3ት አሥርት ዓመታት በኋላ በአብላጫ ድምጽ ያሸነፈበት ይህ ምርጫ የብሪታንያን ህዝብ ለሁለት የከፈለውን የብሬግዚትን ፍጻሜ ያቃረበ መስሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:06

የቦሪስ ጆንሰን ድልና ቀሪ የብሬግዚት ተግዳሮቶች

ባለፈው ሐሙስ በተካሄደው የብሪታንያ አጠቃላይ ምርጫ ያሸነፉት የብሪታንያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ቦሪስ ጆንሰን በቃላቸው መሠረት ከአንድ ወር በኋላ ብሪታንያን ከአውሮጳ ህብረት አባልነት ለማውጣት ተዘጋጅተዋል።የምርጫ ውጤት ይህን ማድረግ የሚያስችላቸው ቢሆንም ከዚያ በፊት ግን በአዲሱ የብሬግዚት ውል ላይ የሃገሪቱን ምክር ቤት ይሁንታ ማግኘት ይኖርባቸዋል።እስከ ጎርጎሮሳዊው 2020 ጊዜ የተያዘለት የሽግግር ወቅትም በቂ ላይሆን ይችላል እየተባለ ነው። የቦሪስ ጆንሰን ድል እና ቀሪ የብሬግዚት ተግዳሮቶቻቸው የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው።

ባለፈው ሳምንት በብሪታንያ የተካሄደው ወቅቱን ያልጠበቀ አጠቃላይ ምርጫ ያልተጠበቀ ውጤት አስገኝቷል።የብሪታንያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ከ650ው የብሪታንያ ምክር ቤት መቀመጫዎች 365ቱን በማሸነፍ ከፍተኛ ድል መቀዳጀቱ ሊቀመንበሩ ቦሪስ ጆንሰን ያለሙትን ብሬግዚትን ያለ ተቀናቃኝ እንዲያሳኩ መንገዱን ጠርጎላቸዋል።ፓርቲው ከሦስት አሥርት ዓመታት በኋላ በአብላጫ ድምጽ ያሸነፈበት ይህ ምርጫ የብሪታንያን ህዝብ ለሁለት የከፈለውን የብሬግዚትን ፍጻሜ ያቃረበ መስሏል።

አሸናፊው ቦሪስ ጆንሰን ከምርጫው በፊት በገቡት ቃል መሠረት ከአውሮጳ ህብረት ጋር በተስማሙበት  በጎርጎሮሳዊው ጥር 31፣2020 ብሪታንያን ከአውሮጳ ህብረት አባልነት እንደሚያስወጡ በእርግጠኝነት ተናግረዋል። ጆንሰን ከድሉ በኋላ ባሰሙት ንግግር እንዳሉት ከምርጫው ውጤት ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን መገንዘብ ይቻላል።

«በዚህ ሥልጣን እና በዚህ አብላጫ ድምጽ በስተመጨረሻ ምን ማድረግ እንችላለን «ብሬግዚትን ገቢራዊ ማድረግ «ትኩረት ሰጥታችሁታል።ምክንያቱም ይህ ምርጫ ብሬግዚትን ገቢራዊ

ማድረግ ፣አሁን ለድርድር የማይቀርብ፣የማይቋቋሙት እና የማይከራከሩበት የብሪታንያ ሕዝብ ውሳኔ ነው።በዚህ ምርጫም የዳግም ሕዝበ ውሳኔ አሳዛኝ ዛቻ ሁሉ ያበቃል።»

ከድሉ በኋላ ጆንሰን ብሪታንያን የጎዳው ክፍፍል እንዲቆም ጠይቀዋል።በአሁኑ ምርጫ ዋነኛው ተቃዋሚ ሌበር በአንጻሩ ክፉኛ ተሸንፏል።በዚህ ምርጫ ፓርቲው ከጎርጎሮሳዊው 1935 ወዲህ ደርሶበት የማያውቅ ሽንፈት ነው የገጠመው።203 የምክር ቤት መቀመጫዎችን ብቻ ያሸነፈው የሌበር ፓርቲ ሊ/መንበር ጀርሚ ኮርቢን ውጤቱ በጣም አሳዝኖኛል ብለዋል። ኮርቢን የሚሳዝናቸው ፓርቲያቸው ያጋጠመው ከባድ ሽንፈት ብቻ አይደለም። ድሀው ህብረተሰብ  በተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር በቦሪስ ጆንሰን መንግሥት መርህ ምክንያት ሊደርስበት ይችላል ባሉት በደልም ጭምር እንጂ

«ግልጽ ነው ባገኘነው ውጤት በጣም አዝኛለሁ።የምክር ቤት መቀመጫዎቻቸውንም ላጡት ባልደረቦቼ አዝኛለሁ።በቁጠባ መርሁ በሚገፋ መንግሥት የሚያስተዳድራቸው ዝቅተኛ ኑሮ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አዝኛለሁ።እንደሚመስለኝ እነዚህ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያራምዱት የምጣኔ ሃብት ስልት ክፉኛ ይበደላሉ።»

የኮርቢን ፓርቲ አልተሳካለትም እንጂ ቢያሸንፍ በብሬግዚት ላይ ዳግም ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ቃል ገብቶ ነበር።ኮርቢን በሽንፈቱ ሰበብ ከሃላፊነታቸው እንደሚነሱ ይጠበቃል።ሆኖም እርሳቸው እንዳሉት ፓርቲው በተሸነፈበት በዚህ ወቅት ላይ ጥለው መሄድ አይፈልጉም።ርሳቸውን የሚተካ ሲመረጥ ከሃላፊነታቸው እንደሚወርዱ አሳውቀዋል።የኮርቢን ሙከራ በሽንፈት ሲደመደም ቦሪስ ጆንሰን አብላጫ ድምጽ አግኝተው ምኞታቸውን ማሳካት የቻሉበት ሚስጥር ምን ይሆን? በለንደኑ ስኩል ኦፍ ኤኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጆናታን ሆፕኪን ምክንያት የሚሉትን ተናግረዋል።

«ብሬግዚት ተግባራዊ ሳይሆን ከሦስት ዓመት በላይ አልፏል። መራጮች በተለይም ብሪታንያ ከህብረቱ እንድትወጣ ድምጻቸውን የሰጡት ጉዳዩ በመጓተቱ ተረብሸዋል።የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከአየርላንድ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ደርሰዋል።ከአውሮጳ ህብረት ጋርም ቢያንስ በመጀመሪያው ምዕራፍ አወጣጥ ላይ ተስማምተዋል።ድምፃችሁን ለኔ ስጡ በፓርላማው አብላጫ ድምጽ ካገኘሁ ብሬግዚት እውን ይሆናል አሉ።ይህ ደግሞ አሳማኝ ጥሪ ነበር።ይህም አብላጫ ድምጽ ለማግኘት አበቃቸው።»

የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ የቦሪስ ጆንሰን ስኬት ምክንያቱ ሕዝቡ በብሬግዚት ውጣ ውረድ መሰላቸቱ ብቻ አይደለም ይላል።ተቃዋሚው የተሻለ እና ግልጽ አማራጭ ይዞ አለመምጣቱም ለጆንሰን ማሸነፍ አስተዋጽኦ አድርጓል ይላል

ብሪታንያ በጎርጎሮሳዊው ጥር 31፣2020 ከአውሮጳ ህብረት አባልነት ከወጣች በኋላ የአንድ ዓመት የሽግግር ጊዜ ተይዟል።ገበያው እንደሚለው ከአሁን በኋላ ያለው ሂደት በሁለት ምዕራፍ የሚከፈል ነው።

በአውሮጳ ህብረት እና በብሪታንያ ቀጣይ ግንኙነቶች ለሚካሄዱ ድርድሮች እስከ 2020  የተሰጠው ጊዜ በቂ አይደለም የሚሉ ክርክሮች ይሰማሉ። ፋብያን ዙሌግ ብራሰልስ ቤልጅየም የሚገኘው «የአውሮጳ ፖሊስ ማዕከል» የተባለው የጥናት ማዕከል ዋና ስራ አስፈጻሚ ናቸው። በርሳቸው ትነተና በተያዘው ጊዜ የብሬግዚት ጣጣ ካላለቀ ብሪታንያን ሊጎዳ ይችላል። እናም የጊዜው ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ።

«ወደፊት እየተጓዙ ያሉት ጉዳዮች ከጊዜ ጋር የተያያዙ ናቸው። የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የሚመኙትን ውል እንዲያገኙ ተጨማሪ የሽግግር ጊዜ መጠየቅ አለባቸው ።ያም በመጪው የበጋ ወቅት ማለት ለአውሮፓ ነው።ሌሎች የተለዩ ጉዳዮችም አሉ።የአሳ ማጥመድ ጉዳይ አንዱ ነው።ብሪታንያ ከ2020 በኃላ ከህብረቱ ካልወጣች ለአውሮጳ ህብረት በጀት ማዋጣት ይኖርባታል።በነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች ድርድሩ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል።»

ገበያውም ጊዜው በቂ ይሆናል የሚል  ግምት የለውም።

ቦሪስ ጆንሰንን ከአውሮጳ ህብረት መነጠላቸው ብቻ አይደለም የሚያሳስበው፣የብሪታንያ ግዛቶች የኢንግላንድ የስኮትላንድ የዌልስ እና የሰሜን አየርላንድ እጣ ፈንታም ጭምር እንጂ።ስኮትላንድ

እና ሰሜን አየርላንድ ብሬግዚትን አልደገፉም ያለፈው ሳምንቱን የወግ አጥባቂ ፓርቲን ድልም አላሞገሱም።ምንም እንኳን ጆንሰን የብሬግዚት ጉዳይ ዳግም የማያከራክር የብሪታንያ ሕዝብ ውሳኔ ነው ቢሉም እውነታው ግን ከዚህ ይለያል።ለምሳሌ ከስኮትላንድ 59 መቀመጫዎች 48ቱን ያሸነፈው ብሬግዚትን የሚቃወመው የስኮትላንድ ብሔራዊ ፓርቲ በምህጻሩ SNP ነው።ፓርቲው ስኮትላንድ ከብሪታንያ ነጻ እንድትወጣ ይፈልጋል።በዚህ ጉዳይ ላይ ዳግም ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድም እየጠየቀ ነው።የፓርቲው መሪ ኒኮላ ስተርጀን የአብዛኛው የስኮትላንድ ሕዝብ  ፍላጎት በተቀረው የብሪታንያ ክፍል ከሚገኘው ሕዝብ ፍላጎት የተለየ ነው፤ይህንንም የምርጫው ውጤት አሳይቷል ብለዋል።

«ስለ ዓለም ያለህን አመለካከት አንድ ህዝብ ላይ በግዳጅ መጫን አትችልም። ስኮትላንድ የቦሪስ ጆንሰንን መንግሥት እንደማትፈልግ ከዚህ ምርጫ በላይ ግልጽ ሊያደርገው የሚችል ነገር የለም።የአውሮጳ ህብረትን ለቆ መውጣት አይፈልግም የወደፊቱ እጣ ፈንታ ምን ይሁን ምን የራሱን እድል በራሱ መወሰን ነው የሚፈልገው።»

በገበያው አስተያየት የስኮትላንድ ጉዳይ  ከቦሪስ ጆንሰን ተግዳሮች ውስጥ የሚደመር ነው።

ከቦሪስ ጆንሰን ድል በኋላ ጉባኤ ያካሄዱት የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት መሪዎች፣ በብሬግዚት እንዲሁም በአውሮጳ ህብረት እና በብሪታንያ የወደፊት ግንኙነት ላይ መክረዋል።ተንታኞች እንደሚሉት የብሪታንያ ምርጫ ውጤት ለአውሮጳ ህብረት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በጎ ውጤት ነው፤ቢያንስ የብሬግዚት የመጀመሪያው ምዕራፍ የማብቃቱ ምልክት ነውና።ከአሁን ወዲያ ዳግም ድርድር አይኖርም። ቀኑም አይገፋም በተንታኞች አስተያየት አሁን በብዙው ህዝብ ዘንድ ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት ጋር ትቆያለች የሚለው ተስፋ ተሟጧል።እናም አሁን ሁሉ ነገር ግልጽ መሆኑ ጠቃሚ ነው እንደ ተንታኞች።

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች