የቦምብ ፍንዳታ በሶማሊያ | አፍሪቃ | DW | 19.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የቦምብ ፍንዳታ በሶማሊያ

ዛሬ በማዕከላዊ ሶማሊያ በለድዌይን ከተማ ውስጥ በኣንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ ከ10 ሰዎች በላይ ተገድለው በርካቶች መቄሰላቸው ተሰማ። በመኪና ላሊ የተጠመደ ቦምብ መፈንዳቱን ተከትሎ ታጣቂዎችም ተኩስ ከፍተው ለማምለጥ የሞከሩ ፖሊሶችን ሲገድሉ ማየታቸውን የዓይን እማኞች ተናግሯል።

ለጥቃቱም ከኣልቃኢዳ ጋር ቁርኝት እንዳለው የሚነገርለት ጽንፈኛ ቡድን ኣልሸባብ ሀላፊነት ወስዷል።

ጃፈር ዓሊ

የከተማይቱ በለድዌይን የፖሊስ ዋና ኣዛዥ ኮ/ል አብዱልቃዲር አሊን የጠቀሱ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የዛሬው ፍንዳታ ድንገተኛ እና ከባድም ነው የነበረው። ድንገተኛ ሲባል ኮ/ሉ እንደሚሉት የውጪ ጥበቃ መላላት ብቻም ሳይሆን ኣዛዦች እንደዋዛ በማይረባ ግርግዳ ውስጥ በተሰባሰቡበት ኣጋጣሚ ነበር ፍንዳታው የደረሰው። ነገር ግን ከባድ ከማለት ያለፈ ኮ/ል አብዱልቃዲር የሟቾችን ቁጥርም ሆነ የደረሰውን ኪሳራ ከመግለጽ ተቆጥቧል። ሁኔታው ብዙም ሳይቆይ ግን በቁጥጥር ስር መዋሉም ተገልጿል።

የዓይን እማኞች እንደሚሉት ኣንድ በከፍተኛ ፍጥነት የሚከንፍ ኣሮጌ መኪና መቶ ከበለድዌይን ፖሊስ ጣቢያ የጊቢ በር ጋር ተጋጨና በርግዶ ገባ። ወዲያውኑ ፊት ለፊት ካለው የጣቢያው ግርግዳ ጋር ከመላተሙ ከፍተኛ ፍንዳታ ደረሰ። ፍንዳታውን ተከትሎም በመተረየስ ጠመንጃ የታጠቁ ተዋጊዎች ከየአቅጣጫው ወደ ጣቢያው መተኮስ ጀመሩ። በፍንዳታው ተደናግጠው ለማምለጥ የሚርበተበቱ ፖሊሶችንም ይገድሉ ነበር ብሏል እማኞች።

ከፍንዳታው በኃላም በርካታ ኣስክሬኖች እየተጎተቱ ወደ ኣንድ ስፍራ ሲከማቹ ኣይተናል የሚሉት የዓይን እማኞች በርካታ ቁስለኞችም ደም እየዘሩ ሲወጡ ማየታቸውን ለዜና ሰዎች ነግሯል። ለጥቃቱም ኣልሸባብ ኃላፊነቱን ወስዷል። ቁስለኞችን ሳይጨምር የሟቾቹ ቁጥርም የጸጥታ ጥናት ተቐም ባልደረባ የሆኑት ሚ/ር ኣንድሩስ አሶማዋ እንደሚሉት ከ 10 እስከ 14 ይገመታል።

«በትክክል ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ እርግጠኛ ኣይደለንም። የሆነ ሆኖ ግን አ 10 እስከ 14 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ እገምታለሁ። እንደምታውቁት ጥቃቱ የደረሰው በፖሊስ ጣቢያ ላይ ነው። ጣቢያው ደግሞ የኣፍሪካ ህብረት ጦርም ማዕከል ነው። የጂቡቲ ጦር የሚገኝበት። እናም አደጋው ያንን የኣፍሪካ ህብረት ማዕከል ዒላማ ያደረገ ነው። ኣፈጻጸሙንም ብንመለከት መጀመሪያ በመኪና የተጠመደ ቦምብ እንዲፈነዳ ተደረገ። ቀጥሎም የጠመንጃ ተኩስ እንዲከተል ተደረገ። ይሔ ኣሁን ኣልሸባብ የሚጠቀምበት የጥቃት ዘዴ ነው።»

በኢትዮጵያ ድንበር ኣቅራቢያ የምትገኘው የበለድዌይን ከተማ ከዋና ከተማይቱ ሞቃዲሾ በስተ ሰሜን 300 ኪ ሜ ላይ ስትገኝ በአካባቢው ዋና ስልታዊ ከተማ እንደሆነች ይነገርላታል። ባለፈው ወር በኣንድ የኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኝ ከተማ በኣንድ ምግብ ቤት ውስጥ ኣንድ ኣጥፍቶ ጠፊ ባፈነዳው ቦምብ 15 ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን በወቅቱም ለጥቃቱ ኣልሸባብ ኃላፊነት መውሰዱ ኣይዘነጋም።

ምግብ ቤቱ የሶማሊያው መንግስት ደጋፊዎችን ጨምሮ የኣፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮ ጦር አሚሶም እና የኢትዮጵያ ወታደሮች የሚያዘወትሩበት ነው ያለው አልሸባብ ኢላማውም በከተማይቱ የመሸጉ የኢትዮጵያ ወታደሮች መሆናቸውን መግለጹ ይታወቃል።

በሶማሊያ ያለው የኢትዮጵያ ጦር በዚያች ኣገር ካለው የኣፍሪካ ህብረት በምህጻሩ AMISOM ጋር ሊቀላቀል መወሰኑም ታውቐል። ኣፈጻጸሙ ግን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደሚሉት በሂደት ነው ተብሏል።

ሞቃዶሾን ጨምሮ ከደቡባዊቷ የወደብ ከተማ ኪስማዮ ጭምር ተገፍቶ የወጣው ኣልሸባብ ኣሁንም ቢሆን ግን በደቡብ ሶማሊያ ሁሪያውን ሁሉ እንደሚቆጣጠrw ይታወቃል።

ጃፈር ዓሊ

ሸዋዬ ለገሠ