የቦምብ ፍንዳታዎች በግብጽ ቤተክርስቲያናት ላይ | አፍሪቃ | DW | 09.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የቦምብ ፍንዳታዎች በግብጽ ቤተክርስቲያናት ላይ

በግብጽ ሁለት ከተሞች ባሉ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያኖች ላይ በደረሱ ተከታታይ የቦምብ ፍንዳታዎች ቢያንስ 44 ሰዎች ሲሞቱ ከ 100 በላይ ደግሞ ቆሰሉ፡፡ በፍንዳታው የሞቱት እና የቆሰሉት በአሌክሳንድሪያ እና ታታ ከተሞች የሆሳዕናን በዓል በማክበር ላይ የነበሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡

የመጀመሪያው ፍንዳታ የደረሰው ከካይሮ በስተሰሜን 100 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው ታታ በተሰኘችው ከተማ ዛሬ ረፋዱ ላይ ነበር፡፡ በፍንዳታው ቢያንስ 26 ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ 70 ቆስለዋል፡፡ ፍንዳታው የደረሰበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የሆሳዕናን በአል በሚያከብሩ ምዕመናን ተጨናንቆ እንደነበር አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ በወደብ ከተማይቱ አሌክሳንድሪያ በሰዓታት ልዩነት በደረሰው ሁለተኛው ፍንዳታ ደግሞ ቢያንስ 11 ሰዎች ሲሞቱ 35 ቆስለዋል፡፡ በግብጽ ክርስቲያኖች ላይ ጥቃት እንደሚያደርስ ሲዝት የቆየው ራሱን “እስላማዊ መንግስት” ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን ለሁለቱ ፍንዳታዎች ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡ግብጽን በሚቀጥለው ሳምንት ይጎበኛሉ ተብለው የሚጠበቁት የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ጥቃቱን አውግዘውታል፡፡

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ