የቦምብ ጥቃቶች በሶማሊያ | አፍሪቃ | DW | 02.01.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የቦምብ ጥቃቶች በሶማሊያ

ሶማሊያ መዲና መቅዲሾ በሚገኝ አንድ ሆቴል አጠገብ ትናንት ምሽት በተከታታይ በደረሱ የቦምብ ፍንዳታዎች የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 13 ከፍ ማለቱ ተዘግቧል ። ከሟቾቹ መካከል ፖሊሶችም ይገኙበታል ። የሶማሊያው ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ ለጥቃቱ ሃላፊነቱን ወስዷል ።

ሁለቱ ፍንዳታዎች ትናንት ምሽት በተከታታይ የደረሱት መቅዲሾ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ አቅራቢያ በሚገኘው ጀዚሪያ ከተባለው ትልቅ ሆቴል አጠገብ ነበር ። የዶቬለ የመቅዲሾ ዘጋቢ ሞሐመድ ኦማር ሁሴን እንደሚለው የመጀመሪያው ና ሁለተኛው የቦምብ ፍንዳታዎች የደረሱት በአንድ ሰዓት ልዩነት ውስጥ ነው ።

« የመጀመሪያው ጥቃት ከምሽቱ በሃገሩ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ነው የደረሰው ። በጥቃቱ የ6 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል ። 2ተኛው ደግሞ ከ አንድ ሰዓት በኋላ የፈነዳው ። በዚህ አደጋም 6 ሰዎች ተገድለዋል ። ከመካከላቸው 2 የፖሊስ መኮንኖች ይገኙበታል ። »

የዶቼቬለው ዘጋቢ እንደሚለው ዛሬ ከሆስፒታል ባገገኘው መረጃ መሠረት በፍንዳታው የሞቱት ሰዎች ቁጥር 13 ሲደርስ የቆሰሉት ደግሞ 60 ነው ። አደጋው በደረሰበት ወቅትም በሆቴሉ ውስጥ የሶማሊያ ምክር ቤት አባላት ነበሩ ። አነርሱ ግን ከአደጋው ተርፈዋል ። ጀዚራ የተባለው ፍንዳታው የደረሰበት ቦታ አጠገብ የሚገኘው ሆቴል ሞሐመድ ኦማር ሁሴን እንደሚለው የመንግሥት ሹማምንት ና የዲያስፖራዎች መነኻሪያ ነው ።

« ጀዚራ በቅርቡ የተገነባ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ነው ። የሆቴሌ እንግዶች በሙሉ ማለት ይቻላል በውጭ ሃገራት የሚኖሩ ሶማሌዎች ና የመንግስት ባለሥልጣናት ናቸው ።»

በዚሁ ስፍራ ከጥቂት ወራት በፊት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት እዚያ ያረፉ የኬንያ መንግሥት ልዑካንን ሲያነጋግሩ በአቅራቢያ ተመሳሳይ ጥቃት ደርሶ ነበር ። ከትናንት ምሽቱ የመጀመሪያ ፍንዳታ በኋላ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው ነበር ሆኖም በጠባቂዎች የአፀፋ ተኩስ ከአካባቢው መፈግፈጋቸውን ነው ሞሀመድ የገለፀው ።

«የሆቴሉን ሥራ አስኪያጅ ሚር ሃሰንን አነጋግሬ ነበር ። እርሳቸው እንዳሉት የመጀመሪያው የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ሲደርስ በአካባቢው የአሸባብ ታጣቂዎች ነበሩ ። ከፍንዳታው በኋላም ሆቴሉ ውስጥ ለመግባት ፈልገው ነበር ። ሆኖም የሆቴሉ ጠባቂዎች ና በአካባቢው የነበሩት ኃይሎች ተኩስ ከፍተውባቸው እንዲሸሹ አድርገዋል ። ወደ ሆቴሉ ዘልቀው ለመግባት አልቻሉም ። »

አሸባብ ለቦምብ ጥቃቶቹ ሃላፊነቱን ወስዷል ። በትዊተር ባሰራጨው መልዕክቱ መሰል ጥቃቶችን ማድረሱን እንደሚቀጥልም አስታውቋል። መሐመድ እንደሚለው አሸባብ ቢዳከምም ቦምብ ማፈንዳት ግን አያቅተውም ።

« በርግጥ አሸባቦች እንደ በፊቱ ጠንካራ አይደሉም ። ከዚህ ቀደም ይቆጣጠሯቸው ከነበሩት ከዋና ከተማይቱ ከመቅዲሾም ሆነ ከሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች ሁሉ እየተባረሩ ነው ። ሆኖም አሁን የትግል ስልታቸው ወደ ሽምቅ ውጊያ ተቀይሯል ። እውነቱን ለመናገር አሸባቦች አሁንም አሉ ። በየትኛውም የሶማሊያ አካባቢ በማንኛውም ጊዜ ጥቃት ማድረስ ይችላሉ ። »

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic