የቦምብ ጥቃት በሶማሊያ | አፍሪቃ | DW | 28.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የቦምብ ጥቃት በሶማሊያ

ሶማሊያ ዋና ከተማ መቅዲሾ ውስጥ ዛሬ በደረሰ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ከ10 የሚበልጡ ሰዎች ህይወት ጠፋ ። ሰባት ሰዎች ደግሞ ቆሰሉ ። በሶማሊያ ብሔራዊ የፀጥታ ዋና መስሪያ ቤት አቅራቢያ በደረሰው በዚሁ ጥቃት ከተገደሉት መካከል ሰላማዊ ሰዎችና የደህንነት ኃይሎችም ይገኙበታል ። ለጥቃቱ አሸባብ ሃላፊነቱን ወስዷል ።

ጥቃቱ የደረሰው የሶማሊያ የደህንነት ኃይሎች በሚያዘወሩት ቡና ቤት ላይ ነው ። የዶቼቬለ የመቅዲሾ ዘጋቢ መሀመድ ኦማር ሁሴን እንደተናገረው ዛሬ ጠዋት አጥፍቶ ጠፊ ያሽከረክር የነበረው መኪና ቡና ቤቱን ጥሶ ሲገባ ነበር አደጋው የደረሰው ። በወቅቱም የደህንነት ሰራተኞች ቡና ቤቱ ውስጥ በመስተናገድ ላይ ነበሩ ።

« ዛሬ ከጠዋቱ 5 ሰዓት ከሩብ ገደማ ነው የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት የደረሰው ። የሶማሊያ ብሔራዊ ደህንነት ዋና ፅህፈት ቤት ፊት ለፊት ከሚገኝ ቡና ቤት ጋር ፈንጂዎች የታጨቁበት መኪና ሲላተም በቤቱ ውስጥ ቡና የሚጠጡ ፖሊሶች ነበሩ ። »

እስከ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ድረስ በአደጋው የሞቱት ሰዎች ቁጥር 10 መድረሱ ነው የተዘገበው ። ከመካከላቸውም ፖሊሲችና ሰላማዊ ሰዎች እንደሚገኙበትና ቡና ቤቱም ሙሉ በሙሉ መውደሙን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል ። ከአደጋው በኋላ ወደ ስፍራው በመሄድ የደረሰውን ጥፋት በዓይኑ መመልከቱን የሚናገረው መሃመድ ግን የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከዚህ ይበልጣል ነው የሚለው ።

« እኔ እስካሁን 12 ሰዎች መገደላቸውን 7 ደግሞ መቁሰላቸውን ተመልክቻለሁ ። ከሟቾቹ መካከል አንዱ የፖሊስ መኮንን አንድ ደግሞ ተራ ወታደር ነው ። »

ባለፈው ሳምንት አርብም ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት መቅዲሾ ፣ ከመቅዲሾም በፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ውስጥ ደርሷል ። መሀመድ እንደሚለው መንግሥት ከተማይቱን የሚያሸብሩትን ኃይሎች እያዳከመ መሆኑን ቢገልፅም ተጨባጩ ሁኔታ ግን ተቃራኒው ነው ።

« እውነቱን ለመናገር የሶማሊያ መንግሥት ባለፉት ጥቂት ቀናት የአሸባብን ርዝራዦች እያጠፋሁ ነው ሲል እየተናገረ ነው ። መንግሥት ይህን ቢልም እስካሁን የከተማይቱን ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችል እርምጃ አልወሰደም ። ባለፈው ሳምንት አርብ በመቅዲሾው ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግስት ላይ ባነጣጠረ ጥቃት 11 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል ። »

የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት መቅዲሾ እየተደጋገመ ነው ። የዚህ ምክንያቱ እንደ መሃመድ ወታደሮቹ በአግባቡ አለመያዛቸው ነው ።

« በመቅዲሾ ጎዳናዎች ላይ ለጥበቃ የተሰማሩ ወታደሮች አሉ ። ሆኖም እነዚህ ወታደሮች በየወሩ በቂ ደሞዝ በወቅቱ ስለማይከፈላቸው መኪናዎች ፈንጂ ይጫኑ አይጫኑ ሳይፈትሹ ሊያሳልፉ ይችላሉ ።»

በመሀመድ አስተያየት ባለሥልጣናትንና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ዒላማ ካደረጉትአጥፍቶ ጠፊዎች ከሚያደርሷቸው የዛሬውን መሰል ጥቃቶች በተጨማሪ መቅዲሾ ሰዎች በየለሊቱ የሚገደሉባት ከተማም ናት ። የመንግሥት ባለሥልጣናት ብቻ ሳይሆኑ የተመድ ወይም ደግሞ ከመንግሥት ጋር የሚሰሩ የጥቃት ዒላማ ናቸው ። ለዚህም መሀመድ በዋቢነት የገለፀው ትናንት በከተማይቱ የተፈፀመውን ግድያ ነው ።

« ለምሳሌ ትናንት ለሊት የልጅነት ልምሻ የፖሊዮ ክትባት ቅስቀሳ ያደርጉ ከነበሩ ሰዎች መካከል ሁለቱ ተገድለዋል ፤ አንድ ሴትና አንድ ወንድ ። »

ለዛሬው የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ሃላፊነቱን የወሰደው አሸባብ መሰል ጥቃቶችን ማድረስ እንደሚቀጥልም ዝቷል ።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች