የብዙ ስደተኞች አስከሬን በሊቢያ ባህር ጠረፍ መገኘቱ | አፍሪቃ | DW | 05.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የብዙ ስደተኞች አስከሬን በሊቢያ ባህር ጠረፍ መገኘቱ

በሊቢያ ምዕራባዊ የባህር ጠረፍ በምትገኘው የዙዋራ ከተማ ባህር የተፋቸው ወደ 133 የሚጠጉ ስደተኞች አስከሬን ባለፉት ጥቂት ቀናት መገኘቱን የግብረ ሰናዩ የ«ቀይ ጨረቃ» ድርጅት ዛሬ ገለጸ።

የድርጅቱ ቃል አቀባይ አል ኻሚስ አል ቦሳይፊ እንዳስታወቁት፣ አስከሬናቸው ከተገኙት በመስመጥ አደጋ ሕይወታቸውን ካጡት ስደተኞች መካከል ሶስት አራተኛው ሴቶች ሲሆኑ፣ ቢያንስ አምስት ሕፃናትም ይገኙባቸዋል፣ በከፊል መፈራረስ በጀመሩት አስከሬኖች ላይ አንድም የመታወቂያ ሰነድ አለመገኘቱን እና ብዙዎቹም ከሰሀራ በስተደቡብ ካሉ አፍሪቃውያት ሀገራት ተወላጆች እንደነበሩ አል ቦሳይፊ አክለው አስረድተዋል። አንድ ያካባቢ ባለስልጣን እንደገመቱት፣ ማቾቹ ስደተኞች ባለፈው ሳምንት ወደ አውሮጳ ለመግባት ጉዞዋቸውን በዙዋራ ከተማ አቅራቢያ ከምትገኘው የሳብራታ ከተማ ሳይጀምሩ አልቀሩም። እንደሚታወሰው፣ ባለፈው ሳምንት እስከ አንድ ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች ነበሩ ጀልባዎች በሰመጡበት አደጋ ሕይወታቸውን ያጡት።

ይህ በዚህ እንዳለ፣ ሊቢያ ቱርክ ወደ አውሮጳ የሚመጡ ስደተኞችን መልሳ ለመውሰድ ከአውሮጳ ህብረት ጋር ከጥቂት ጊዜ በፊት የተፈራረመችውን ዓይነት ውል በመድረስ ስደተኞችን መልሳ እንደማትቀበል አስታወቀች። የሊቢያ ብሔራዊ አንድነት መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር ፋየስ አል ሳራሽ ለጀርመናውያኑ ሳምንታዊ ጋዜጣ «ቬልት አም ዞንታግ» በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ የአውሮጳ ህብረት ስደተኞችን ወደ ሊቢያ መልሶ የሚልክበትን ድርጊት ሀገራቸው በፍፁም እንደማትቀበል ግልጽ አድርገዋል። ስደተኞቹ ሊቢያ ውስጥ ሊቀመጡ እንደማይችሉ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚንስትር አል ሳራሽ፣ አውሮጳ ስደተኞቹን ወደ ትውልድ ሀገራቸው መልሳ የምታደርስበበትን መንገድ ራሷ መፈለግ እንደሚኖርባት አሳስበዋል። የአውሮጳ ህብረት የሚመልሳቸውን ስደተኞችን ቱርክ እንድትቀበል ህብረቱ ከዚችው ሀገር ጋር ስምምነት ከተፈራረመ ወዲህ፣ ስደተኞች በሊቢያ በኩል እያደረጉ ወደ አውሮጳ ለመግባት ሙከራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ