የብር ምንዛሪ ዋጋ ማቆልቆልና ተጽዕኖው | ኤኮኖሚ | DW | 08.09.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የብር ምንዛሪ ዋጋ ማቆልቆልና ተጽዕኖው

የኢትዮጵያ ብር የምንዛሪ ዋጋ ባለፈው ሣምንት ሃያ በመቶ ማቆልቆሉ በአገሪቱ የኑሮ ውድነትን ይበልጥ ከማባባስ ባሻገር በመጪዎቹ ዓመታት የምጣኔ-ሐብት ዕድገት ላይ ከባድ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አንዳንድ የኤኮኖሚ ጠበብት እያስገነዘቡ ነው።

default

ብሄራዊው ምንዛሪ በዶላር በሶሥት ብር ገደማ ወደ 16.35 ከፍ ሲል እርግጥ የውጭ ንግድን እንደሚያሳድግና በአንጻሩም ወደ አገር ምርት ማስገባቱን እንደሚያለዝብ ነው የሚታሰበው። ዕርምጃውን ባለሙያዎች ቢተቹትም ዓለምአቀፍ የምንዛሪ ተቋም በበኩሉ ኢትዮጵያን የፉክክር ብቃት የሚያሳድግ ነው ሲል ደግፎታል። ተቋሙ እንደሚያምነው እርግጥ ዕርምጃው ተስማሚ በሆነ የምንዛሪ ፖሊሲ መታጀቡ ግድ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በያመቱ ከ 14 በመቶ በላይ የኤኮኖሚ ዕድገት የሚጠበቅበት የአምሥት ዓመት የልማት ዕቅድ ማውጣቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ባንክ የአገሪቱን ብሄራዊ ምንዛሪ ዋጋ ዝቅ በማድረግ የወሰደው ዕርምጃ ባለፈው ዓመት ተኩል ጊዜ አራተኛው ሲሆን ውሣኔው የምርቶችን ዋጋ በማናር የኑሮ ውድነትን እያሳደገ መሄዱ እንደማይቀር ነው የሚነገረው። እርግጥ የወቅቱን ሁኔታ አስመልክቶ ገና ጭብጥ መረጃ ማቅረብ ባይቻልም አጠቃላዩ ሂደት የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ግሽበትን መጨመር የሚያመለክት ነው። ለብዙው ዜጋ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑም አልቀረም።

የኑሮ መወደድ በመሠረቱ የገበያተኛውን ሕዝብ ደሞዝ ከሁኔታው መስተካከልን ይጠይቃል። ማለት የመግዛት አቅሙ እያነሰ እንዳይሄድ። በዚህ በኩል ተሥፋ ከመሰጠቱ በስተቀር እስካሁን በተጨባጭ የተወሰደ ዕርምጃ የለም።

የብር ዋጋ መውደቅ የውጭ ንግድን እንደሚያጠናክርና በሌላ በኩል ደግሞ ወደ አገር የሚገቡ ምርቶችን እንዲያስወድድ የማያጠራጥር ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ቡናንና ሌሎች የአርሻ ምርቶችን ወደ ውጭ የምትልክ ቢሆንም እንደበለጸጉ አገሮች የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለውጭ የምትሸጥ አይደለችም። በአንጻሩ ወደ አገር እንዲገቡ የሚፈለጉት ምርቶች ከነዳጅ አንስቶ እስከ ቴክኒክ ዕቃዎች ብዙዎች ናቸው። እዚህ ላይ ብሄራዊው ነጋዴ ይበልጡን መጎዳቱ አይቀርም።

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ዕርምጃው የኢትዮጵያን ቶፎካካሪነት ብቃት ለማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጿል። ሆኖም ዕርምጃው ስኬት እንዲያሳይ በጥሩ የምንዛሪ ፖሊሲ መታጀብ አለበት ባይ ነው።

የምንዛሪው ቅነሣ የተደረገው በቅርቡ የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ በያመቱ በከፍተኛ መጠን ለማሳደግ የአምሥት ዓመት ዕቅድ ወጥቶ ከተዋወቀ በኋላ ነው። አሁን ከተፈጠረው ጠንካራ የኑሮ ውድነት አንጻር ይህን ዕቅድ ማሳካት መቻሉ ለብዙዎች አጠራጣሪ ነው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ