የብሬግዚት ውዝግብ እና ተጽእኖው | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 12.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የብሬግዚት ውዝግብ እና ተጽእኖው

የብሪታንያ ፓርላማ አባላት በብሬግዚት ውል እጣ ፈንታ ላይ ዛሬ ይወስናሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ፣ ከአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ጋር ትናንት የተስማሙባቸው ለውጦቹ የህዝብ እንደራሲዎቹ ውሉን እንዲቀበሉ ያስችላሉ የሚል እምነት አላቸው። ይሁንና ለውጦች አባላቱ ውሉን እንዲደግፉ ማድረጋቸው ማጠራጠሩ አልቀረም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:15

የብሬግዚት እጣ ፈንታ


ብሪታንያና የአውሮጳ ህብረት በተስማሙበት የብሬግዚት ውል መሠረት ብሪታንያ ከ17 ቀናት በኋላ ከህብረቱ አባልነት ትወጣለች ተብሎ ቢጠበቅም ውሉ ከብሪታንያ ምክር ቤት በኩል በተነሳበት ተቃውሞ ሰበብ ብሪታንያ ከህብረቱ እንዴት እንደምትወጣ እስካሁን ግልጽ ሳይሆን ቆይቷል። የብሪታንያ ምክር ቤት አባላት በተለይ የአየርላንድን እና የሰሜን አየርላንድን ድንበር ጉዳይ የሚመለከተው የውሉ ክፍል ካልተሻሻለ እንደማይቀበሉት ደጋግመው አሳውቀዋል፤ በጥር ወር በሰጡት ድምጽ ውሉን ያልደገፉበት ምክንያትም ይኽው ነበር። በፓርላማ አባላት ጥያቄ መሠረት  ውሉ በሚሻሻልበት መንገድ ላይ ከአውሮጳ ህብረት ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ብራስልስ እና ሌሎች ከተሞች ሲመላለሱ የቆዩት የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ይህንኑ

ጥያቄ ይዘው ትናንት ማታ ሳይቀር ከአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዦን ክሎድ ዩንከር ጋር ሽትርስቡርግ ፈረንሳይ መክረው ነበር። ከምክክሩ በኋላም የፓርላማ አባላቱ ለሚቃወሙት የአየርላንድ ድንበር ጉዳይ የህግ ማዕቀፍ አባሪ የሚያደርግ ለውጥ ላይ መስማማታቸው ተገልጿል። ስምምነቱን ሜይ እና ዩንከር ለብሪታንያ ዋስትና የሚሰጥ ብለውታል። ሁለቱ ወገኖች ትናንት ከተነጋገሩ በኋላ የተስማሙባቸውን ጉዳዮች የብራሰልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ  በሦስት ይከፈላቸዋል።  ተደረገ የተባለው ማሻሻያ ግን የብሪታንያ ፓርላማ አባላትን ጥያቄ የሚያሟላ አይደሉም የሚል ትችት ቀርቦበታል። የሜይ የህግ አማካሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጀፍሪ ኮክስ ዛሬ እንዳሉት አሁንም የተለወጠ ነገር የለም። በርሳቸው እባባል ተደረገ የተባለው ማሻሻያ በተለይ ከህብረቱ ጋር የሚካሄደው የንግድ ድርድር እንዳይሳካ የሚያደርጉ ህጋዊ ስጋቶችን አላስወገደም። ያም ሆኖ ግን የአውሮጳ ህብረት አሁን የሰጠው ዋስትና ብሪታንያ «ላልተወሰነ ጊዜ እና

ካለፈቃድዋ የአየርላንድ እና የሰሜን አየርላንድ ድንበር ክፍት ሆኖ እንዲቆይ በሚያደርገው በዚህ ውል ምክንያት ልትታሰር የምትችልበትን ስጋት ግን ቀንሷል ብለዋል። የአውሮጳ ህብረት ከዚህ ቀደም የብሬግዚት ውል እንደማይሻሻል በተደጋጋሚ ሲያሳውቅ ነበር። ታዲያ ትናንት ከሜይ ጋር የተስማማባቸው ነጥቦች ውሉ ተሻሻለ ሊያስብሉ የሚያስችሉ ይሆን? 
የብሪታንያ ፓርላማ በብሬግዚት ውል ላይ በጥር ወር በሰጠው ድምጽ ሳይቀበለው

Infografik May's Brexit-Plan EN

ቀርቷል። ያኔ ሜይ የተሻሻለ ውል ይዘው ለመምጣት ቃል ገብተው ነበር። ሜይ ለፓርላማቸው ቃል በገቡት መሠረት ከአውሮጳ ህብረት ጋር ተነጋግረው በተስማሙበት፣ ለብሪታንያ ዋስትና ይሰጣል በተባለው አዲስ ሃሳብ ላይ ዛሬ ማምሻውን የብሪታንያ ምክር ቤት አባላት ድምጽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ፓርላማው ዛሬ በሚቀርብለት አዲስ ሃሳብ ይስማማ አይስማማ ከወዲሁ ለመገመት ያዳግታል። ሆኖም ውሉን ከተቀበለ በስምምነቱ መሠረት የብሬግዚት ሂደት ይቀጥላል። ካልተስማሙስ? 
የለንደኑ ወኪላችን ድልነሳ ጌታነህ እንዳለው እነዚህ አስቀደመው የተያዙ እቅዶች መተግበራቸውን የሚወስነው የዛሬ ማታው የድምጽ አሰጣጥ ውጤት ነው። ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት እንድትወጣ ህዝቡ ከወሰነ ሥስት ዓመት ሊሞላ ጥቂት ወራት ብቻ ናቸው የቀሩት። እነዚህ ጊዜያት በሀገሪቱ የክፍፍል የክርክር እና የውዝግብ ጊዜያት ሆነው ነው የዘለቁት። ድልነሳው

እንደሚለው  ሂደቱ በፖለቲከኞችም ዘንድ ይሁን በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ መሰላቸትን እና አለመረጋጋትን ያስከተለ ስጋትም ያሳደረ ነበር። 
የብሬግዚት ውል ያስነሳው ውዝግብ እና ሂደቱ በብሪታንያ ብቻ ሳይሆን በአውሮጳ ህብረትም ላይ ልዩ ልዩ ተጽእኖዎችን መሳደሩ አልቀረም። እነዚህ ተጽእኖዎች ግን እንደ ገበያው አሉታዊ ብቻ አልነበሩም። ለህብረቱ መጠናከር አስተዋጽኦ ያበረከቱም ናቸው።
የብሪታንያ ፓርላማ  በብሪግዚት ውል ላይ ዛሬ የሚያሳልፈው ውሳኔ የብሬግዚትን ጉዳይ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ያደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ቴሬሳ ሜይም ዛሬ የብሪታንያ ምክር ቤትን ድጋፍ እንደሚያገኙ ሙሉ እምነት አላቸው። ይሳካላቸው ይሆን? 

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች