የብራዚል ምርጫና የሁለቱ ወይዛዝርት ፉክክር | ዓለም | DW | 01.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የብራዚል ምርጫና የሁለቱ ወይዛዝርት ፉክክር

ኣንድ ዘመን ሁለቱም የአንድ ፓርቲ አባላትና ጓዶች ነበሩ፣ ፕሬዚዳንት ዲልማ ሩሴፍና ማሪና ሲልቫ! ከ 4 ቀናት በኋላ በሚካሄደው አቀፍ- አቀፍ ምርጫ ፣ የሆነው ሆኖ የመሪነቱን እርፍ ለመጨበጥ ሁለቱ ወይዛዝርት ብርቱ ፉክክር በማድረግ ላይ ናቸው።

የብራዚል ሕዝብ የፊታችን እሁድ ለምርጫ አደባባይ ይወጣል። ከአንድ ወር በፊት ማሪና ሲልቫ 50 ለ 40 በመምራት ላይ እንደነበሩ አንድ የምርጫ ጉዳይ ተከታታይ ተቋም ጠቁሞ ነበር። ይሁንና የምርጫ ው ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ፣ የተለያዩ ምርጫ ነክ ተቋማት እንደሚጠቁሙት ፣ውጤቱ ተቀራራቢ ስለሚሆን፤ ሁለተኛ ዙር ምርጫ አይቀሬ ነው ። በእሁዱ ምርጫ አሸናፊው አብላጫ ድምፅ ካላገኘ ጥቅምት 16 ቀን ዳግመኛ ምርጫ አስፈላጊ ይሆናል። ስለሚጠበቀው የብራዚል ምርጫና የሁለቱ ወይዛዛርት ትንንቅ ፣ ዶቸ ቨለ አጠር ያለ ዘገባ ያቀርባል።

በዓለም ውስጥ በቆዳ ስፋትና በህዝብም ብዛት የ 5ኛነቱን ደረጃ በያዘችው ሀገር በብራዚል የፊታችን እሁድ በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ የሚወዳደሩት የ 66 ዓመቷ የአገሪቱ ፕሬዚዳንትና የሠራተኞች ፓርቲ ተወካይ ዲልማ ሩሴፍና የ 56 ዓመቷ የሶሾያሊስቱ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ ማሪና ሲልቫ ናቸው። ለተፈጥሮ ጥበቃ በመታገል የታወቁ ፤ ግራ ዘመም የፖለቲካ መርሕ ተከታይ መሆናቸውም የሚነገርላቸው ማሪና ሲልቫ በተጨማሪ በብራዚል ከታወቀው መደበኛ የካቶሊክ ክርስትና ሃይማኖት ወደ ጰንጠቆስጤ የዞሩ ናቸው። መራጩ አዲስ መሪ ማየት ይሻ ይሆናል ቢባልም ፣ ለኤኮኖሚ ዕድገትና ለኑሮ መሻሻል ያሁኗ ፕሬዚዳንት ሩሴፍ መርሕ ሳይሻል እንደማይቀር የሚናገሩ ባራዚላውያን ብዙዎች ናቸው። ቫለሪያኖ ኮስታ የተባሉት በሳዖ ፓውሎ ዩንቨርስቲ የማሕበራዊ ሳይንስ ባለሙያ ስለሁለቱ ፖለቲከኞች እንዲህ ይላሉ---

«እንደሚመሰለኝ በምንም ዓይነት የማይጣጣሙ ናቸው። ሁለቱም ፖለቲከኞች፤ የተከበሩና ጠንካራ አቋም ያላቸው ቢሆንም፤ ስለዓለም ያላቸው ምልከታና የርእዮት አቅጣቻቸው ፍጹም የተለያየ ነው።»

ለነገሩ ፤ አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኙት የሠራተኛው ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ ዲልማ ሩሴፍና የሶሺያሊስቱ ፓርቲ ተፎካካሪአቸው ማሪና ሲልቫ፣ በፖለቲካው ሕይወት ካለፈ ተመሳሳይ ተመክሮ በመነሣት ውድድራቸውም ሰላማዊና የሠመረ ሊሆን በቻለ ነበር። ማሪና ፤ በምርጫ ዘመቻቸው 25 ዓመት የሠራተኛውን ፓርቲ ማገልገላቸውን ሳያወሱ ያለፉበት ጊዜ የለም። ወታደራዊ አምባገነነ አገዛዝ በነበረበት ወቅት በ 1980ኛዎቹ ዓመታት ነው የሠራተኛው ፓርቲ ፣ ሕዝብን በማሰባሰብ ጠንከር ያለ የፖለቲካ ተቃውሞ እንዲንጸባረቅ በማድረግ፣ ለሀገሪቱ ዴሞካራሲያዊ ተሐድሶ ወሳኝ ድርሻ አበርክቷል። እናም የሠራተኛው ፓርቲ ፣ በልዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ መሪነት ፣ እ ጎ አ ጥር አንድ ቀን 2003 ዓ ም ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግሥት ሥልጣን መረከብ ቻለ። ከ 8 ዓመታት በኋላ የእርሳቸውን ፈለግ በመከተል ዲልማ ሩሴፍ የብራዚል የመጀመሪያቱ ሴት ፕሬዚዳንት በመሆን የሐገሪቱ የመሪነት ሥልጣን ለመረከብ በቁ። አሁንም ቫለሪያኖ ኮስታ--

«በብራዚል የሠራተኛው ፓርቲ ለዘመናት የፖለቲካ ተጽእኖ ማሳደር የሚችል የፖለቲካ ማሕበር ነው። ከዲልማና ማሪያና ሌላ 2 እጩ ተወዳዳሪዎችም አሉ። ከአረንጓዴው ፓርቲ፣ ኤድዋርዶ ዞርዠ ማርቲንስ እንዲሁም ሶሺያሊዝምና ነጻነት ከተሰኘው ፓርቲ ሉቺያና ጌንሮ የተባሉት ይገኛሉ። የአርሶ አደሩንና የተፈጥሮን ጥቅም የሚያስቀድሙት ማሪና ሲልቫም ከዚሁ ፓርቲ ናቸው። የግራ ዘመም ርእዮት የሚያንጸባርቀው የከተሞችና የኢንዱስትሪ ሠራተኞች ማሕበር ዲልማ ሩሴፍንና የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ሉላን ያፈራ ነው።»

የዲልማና ማሪና መቀናቀን ሀ ብሎ የጀመረው እ ጎ አ በ ግንቦት ወር 2008 ዓ ም ነው። ማሪና ፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሉላና ያኔ የሚንስትሮች ም/ቤት ሰብሳቢ ዲልማ ሩሴፍ ለኤኮኖሚ ዕድገት ይበጃል ያሉትን መርሕ በመቃወም የተፈጥሮ አካባቢ ሚንስትርነት ሥልጣናቸውን ለቀቁ። ሉላ በአግራቸው ይተኩ ዘንድ ማሪናን ሳይሆን ዲልማን በመምረጣቸው፤ ማሪና ከአነአካቴው በ 2009 ከሠራተኛው ፓርቲ ተሰናበቱ። በዓመቱ የባራዚል የአረንጓዴ ፓርቲ በመወከል በፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ተሳትፈው ነበር። አሁን የፕሬዚዳንትነት ፉክክሩ በአዲስ መልክ፤ በ2 ቱ ሴቶች መካከል የተጀመረው፤ የሶሺያሊስቱ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ ኤድዋርዶ ካምፖ፣ በአኤሮፕላን አደጋ በመሞታቸው ነው። ቀድሞ በብራዚል የ ሃይንሪኽ በኧል ድርጅት ኀላፊ የነበሩት ስለብራዚል የውስጥ ጉዳይ የተመራመሩት ቶማስ ፋቶየር እንደሚሉት ማሪና፤ ከሙስና ጋር በተያያዘ፤ ስማቸው በመጥፎ አይነሣም። ዲልማ ፤ ፓርቲያቸው ከገባበት የቅሌት ተግባር በእርምት ሥራውን እንዲያሻሻል በመታገል ላይ ሳሉ፤ማሪና «የአዲሲቱ ብራዚል ተጠሪ» በሚል ተቀጥላ መሞካሸታቸው አልቀረም። ይሁን እንጂ፣ በምርጫው ዘመቻ የድምፅ ሰጪው ሕዝብ አመለካከት በመዋዠቅ ላይ ነው። Datafolha የተባለው የሕዝብ አስተያየት ሰብሳቢ ተቋም እንደገለጸው ከሆነ ማሪና በተከታታይ የድጋፉ መጠን እየተሸረሸረባቸው ነው።

በአንድ ወር ብቻ በነሐሴ 24 እና በመስከረም 17 ,2007 መካከል የድጋፉ መጠን ከ 34 ከመቶ ወደ 27 ከመቶ ነው ያሽቆለቆለው። ዲልማ ሩሴፍ ከዚህ አንጻር ፣ ተጨማሪ 6 ነጥብ በማግኘት አሁን ባጠቃላይ ወደ 40 ከመቶ ከፍ ብሎላቸዋል። እናም ከዚህ ቀደም ባልተገመተ ሁኔታ በመጀመሪያ ዙር ሊያሸንፉ ይችላልም እየተባለ ነው። የማሪና አቅጣጫ ለድምጽ ቅነሳው አስተዋጽዖ አድርጓል እንደ ፖለቲካ ጠበብት ግምገማ! የሶሺያሊስቱ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪ፣ ማሪና በማሕበራዊ ኑሮ ዕድገት በኩል የገዥውን ፓርቲ መርኀ-ግብር እየደገፉ የመንግሥት ወቺ መቀነስ አለበት ይላሉ። የአማዞን ደን የሚጠበቅበት ሁኔታ እንዲቀጥል ሲሉም የግብርና ውጤቶችን ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን ሀገር ጥቅም ያጤኑበት አልመሰለም። ቫሌሪያኖ ኮስታ--

«ማርቲና የነበራቸውን ሰፊ ተቀባይነት በማጣት ላይ ናቸው። አዝማሚያው ወደፊትም የሚያሽቆለቁል እንጂ የሚያሻቅብ አይደለም። ታዲያ ፣ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ባልታሰበ ሁኔታ ፣ ዲልማ ሩሴፍ በመጀመሪያ ዙር የምርጫው አሸናፊ ሊሆኑም ይችላሉ።»

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic