የብራስልስ የኢራን ማዕቀብና ትርጉሙ | ኤኮኖሚ | DW | 01.02.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የብራስልስ የኢራን ማዕቀብና ትርጉሙ

የአውሮፓ ሕብረት ኢራንን ከአቶም መሣሪያ ባለቤትነት ለመግታት በሣምንቱ መጀመሪያ ጠንካራ የማዕቀብ ዕርምጃዎችን ወስዷል። ሕብረቱ ከኢራን ነዳጅ ዘይት ማስገባቱን ለማቆም ሲወስን በቴህራን መንግሥት ላይ ግፊቱን ይበልጥ ለማጠናከር ሌሎች ማዕቀቦችንም ጭምር ነው ያጠበቀው።

በብራስልስ እገዳ መሠረት ሕብረቱ ከፊታችን የጎርጎሮሣውያኑ ሐምሌ አንድ ቀን አንስቶ ከኢራን ማንኛውንም ነዳጅ ንጥረ-ነገር አያስገባም። ከዚሁ ሌላ አውሮፓውያን በኢራን የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪ ውስጥ አዲስ መዋዕለ-ነዋይ ማድረጋቸው የተከለከለ ነው።                                                                                    

የቴህራን ማዕከላዊ ባንክ ሂሣብም ከጥቂት በጥብቅ ቁጥጥር ከሚካሄድ ተግባር በስተቀር የሚታገድ ይሆናል። ሕብረቱ እንደሚለው ማዕከላዊው የገንዘብ ተቋምና የአገሪቱ ሶሥተኛ ቀደምት ባንክ “ቴጃራት” የኢራንን የአቶም ፕሮግራም በቀጥታ ሲያራምዱ ነው የቆዩት። ማዕቀቡ የወርቅና ሌሎች ክቡር ድንጋዮችን ንግድም የሚያግድ ነው። ሕብረቱ ከወዲሁ የ 433 ኩባንያዎችንና የ 113 ግለሰቦችን ሂሣብ ማገዱም ይታወቃል። የአውሮፓ ሕብረት ለዚህ ሁሉ ከባድና ጥብቅ ዕርምጃ የተነሣው ደግሞ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተርቬለ እንዳስረዱት ኢራን አቶም ቦምብ እንዳትሰራ ባደረበት ጥልቅ ስጋት ነው።

“የኢራን በአቶም መሣሪያ መታጠቅ በአካባቢዋ ሁኔታ ላይ ብቻ ሣይሆን በመላው ዓለም ላይ የሚያስከትለው አደጋ አለው። ስለዚህም የአውሮፓ ሕብረት አሁን የኢራንን የአቶም ዕቅድ ማራመጃ የገንዘብ ምንጭ ለመዝጋት ውሣኔ ማድረጉ ትክክለኛ ነገር ነው”

ማዕቀቡ በመካከለኛው ምሥራቅ ባስከተለው ውጥረት የተነሣ የጥሬ ዘይት ዋጋ ዛሬ በኢሢያ ገበዮች ላይ ከፍ ማለቱ ነው የተነገረው። ኢራን በየቀኑ ለውጭ የምትሸጠው  ነዳጅ ዘይት 2,5 ሚሊዮን በርሚል ገደማ ይጠጋል። አገሪቱ ከሲሶ የሚበልጥ የውጭ ምንዛሪ ገቢዋን የምታገኘውም ከዚሁ ከዘይትና ከጋዝ ንግድ ነው። ስለዚህም ማዕቀቡ ፍቱን ቢሆን በአገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ የሚኖረውን ከባድ ተጽዕኖ መገመቱ አያዳግትም። ኢራን ባለፈው ዓመት ብቻ በነዳጅ ዘይትና በጋዝ ሽያጭ 75 ሚሊያርድ ዶላር አስገብታለች። አንድ-አምስተኛው ወይም ሃያ በመቶው ነዳጅ ዘይት የተሸጠውም ለአውሮፓ ሕብረት ዓባል ሃገራት ነበር። የጀርመን የምጣኔ-ሐብት ምርምር ኢንስቲቲዩት  የኤነርጂ ጉዳይ ባለሙያ ክላውዲያ ኬምፈርት እንደሚሉት ማዕቀቡ ኢራንን እጅጉን ሊጎዳ እንደሚችል አይጠራጠሩም።

“አዎን፤ በጣሙን ሊጎዳት ,ይችላል። ኢራን 50 በመቶ መንግሥታዊ ገቢዋን የምታገኘው ከነዳጅ ዘይት የውጭ ንግድ ነው። እናም አገሪቱ በዚሁ ላይ በጣሙን ጥገኛ ናት” ከዚህ በተጨማሪ አሁን እንደታቀደው የፊናንስ አቅርቦቱም የሚገደብ ከሆነ ደግሞ ኢራን ክፉኛ ነው የምትመታው”

ቴህራን በበኩሏ በፋርስ ባሕረ-ሰላጤ እጅግ ጠቃሚ የሆነውን የነዳጅ ዘይት መስመር የሆርሙስን መተላለፊያ በመዝጋት ማዕቀቡን ለመጋተር ማሰቧ አልቀረም። ይህ ደግሞ ቢሣካ የነዳጅ ዘይት እጥረትንና እንዲያም ሲል የዋጋ መናርን የሚያስከትል ሲሆን በሌላ በኩል ግን ዋሺንግተን አይሞከርም ያለችው ነገር ነው። ታዲያ ሁኔታው ጦርነትን እንዳይጋብዝ ያሰጋል። ይህም ያለ ምክንያት አይደለም።

“ሆርሙስ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነ የንግድ መተላለፊያ መንገድ ነው። አርባ በመቶ ገደማ የሚጠጋው የነዳጅ ዘይት አቅርቦት ይህን መንገድ የሚያቋርጥ ሲሆን መስመሩ ትልቅ ተፈላጊነት አለው። ባለፉት ጊዜያት እንዳየነው ይህን መሰሉ መንገድ ሊታገድ የመቻሉ ወሬ መነሣቱ እንኳ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ወዲያው እንዲንር ነው ያደረገው። እንደ ዕውነቱ መንደዱ እጅግ ጠቃሚ ነው። በሌላ በኩል ይህ ሊሆን ይችላል ወይ? ብሎ መጠየቁ ግድ ነው። አሜሪካ ወዲያው ጣልቃ እንደምትገባ ስታስታውቅ ይህ ቢሆን ለኢራንም የራሷን የነዳጅ ዘይት አቅርቦት የሚቋረጥ በመሆኑ እንደሚጎዳት አንድና ሁለት የለውም። እንግዲህ ነገሩ በዕውነት ያን ያህል ገፍቶ መሄድ መቻሉ ገና የሚታይ ነው”

ለማንኛውም የከፋው ሊመጣ መቻሉንም አብሮ ማጤኑ ሳይበጅ የሚቀር አይመስልም። እንበል ቴህራን የነዳጅ መተላለፊያውን ብትዘጋና የአውሮፓ ሕብረት በኢራን ላይ የጣለው ማዕቀብም ፍቱን ቢሆን ማነው ይበልጥ ተጎጂው? የጀርመን የምጣኔ-ሐብት ምርምር ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ክላውዲያ ኬምፈርት እንደሚሉት”

“አውሮፓ ሌሎች ነዳጅ ዘይት አቅራቢዎችን ልትገለገልም ትችላለች። እርግጥ መጠኑ ዝቅ ያለ እንደሚሆን መታወቅ አለበት። በወቅቱ በዓለም ገበያ ላይ ለነገሩ የነዳጅ ዘይት አቅርቦት ከመጠን በላይ በመሆኑ እጥረት የሚፈጠር መሆኑ አይጠበቅም። ለማንኛውም እገዳው ዕውን ከሆነና የፊናንስ እጥረትም ከተከተለ ኢራን በመጀመሪያ ደረጃ ራሷን ነው የምትጎዳው”

ግን ተጎጂዋ ኢራን ብቻ አትሆንም። ማዕቀቡን ባጠናከረው በአውሮፓ ሕብረት ውስጥም አንዳንድ ሃገራት መቸገራቸው የሚቀር አይመስልም። በሕብረቱ ውስጥ ዋነኞቹ የኢራን ዘይት ገዢዎች ለምሳሌ ስፓኝ፣ ኢጣሊያና ግሪክ ሲሆኑ በተለይም በከባድ የበጀት ቀውስ ለተወጠረችው ለግሪክ የኢራንን ዘይት መተው በጣሙን ከባድ ነው የሚሆነው። አቴን ከኢራን ለምታስገባው ዘይት በወቅቱ ገንዘብ አትከፍልም። ቴህራን የዘይት ዕዳዋን መክፈሉን አሸጋሽጋላታለች። እናም ማዕቀቡ ከፊታችን ሐምሌ በፊት በቅጽበት እንዳይጸና መደረጉም ይህን የዓባል ሃገራቱን ሁኔታ ጭምር በማጤንም ነው። የሕብረቱ የውጭ ፖሊሲ ተጠሪ ካትሪን ኤሽተን የነዚህ ሃገራት ችግር በሚገባ እንደሚታይ በበኩላቸው ቃል ገብተዋል።

“ማዕቀቡ በእያንዳንዱ አገር ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ ለይተን ማወቃችን ጠቃሚ ነገር ነው። ሊታወቅ የሚገባው ማዕቀቡ በሚጣልበት አገር ላይ የሚከተለው ተጽዕኖ ብቻ አይደለም። ማዕቀቡን በሚጭኑት ሃገራት ላይም የሚኖረው ግፊት ጭምር እንጂ! ሁሉንም ነገር በጥሞና የምንመረምር ሲሆን እርግጥ የነዳጅ ዘይት አቅርቦቱ መቀጠሉን ለማረጋገጥ ከሌሎች አምራች ሃገራትም እንነጋገራለን”                                                        

በሌላ በኩል ኢራንን በተመለከተ እርግጥ ለቴህራን ማዕቀቡ በታላላቆቹ የእሢያ ደምበኞቿ ቢወሰድ ይበልጥ አስደንጋጭ በሆነ ነበር። ምክንያቱም ኢራን ወደ ውጭ ከምትልከው ነዳጅ ዘይት ከ 60 በመቶ የሚበልጠውን የሚገዙት ቻይና፣ ጃፓን፣ ሕንድና ደቡብ ኮሪያ ናቸው። እነዚህ በውጭ ነዳጅ ላይ በጣሙን ጥገኛ የሆኑ ሃገራት ደግሞ በማዕቀቡ ደስተኛ እንደማይሆኑ ግልጽ ነው። ያም ሆነ ይህ የሕብረቱ ማዕቀብና ይሄው ያስከተለው ውጥረት ቢቀር በአጭር ጊዜ ስሌት ለነዳጅ ዘይት ዋጋ ይበልጥ መናር ምክንያት መሆኑ የሚቀር አይመስልም።

“እርግጥ ነው፤ አሁን ከተፈጠረው ውጥረት አንጻር ዋጋው አቆልቋይ አይሆንም። በመሠረቱ ግን ማቆልቆል ነበረበት። ምክንያቱም የገበያ መረጃዎች የሚጠቁሙት በቂ አቅርቦት መኖሩን ነው። ግን የኤኮኖሚው ሁኔታ ያን ያህል አርኪ አይደለም። የሆነው ሆኖ ኢራን ጠቃሚ የነዳጅ ዘይት አገር በመሆኗ ተጨማሪ ወደ ላይ ያዘነበለ የዋጋ እንቅስቃሴ እንደምናይ አምናለሁ”

ለማንኛውም 18  በመቶ የሚሆን ዘይቷን ለአውሮፓ የምትሸጠው ሁለተኛዋ ታላቅ የኦፔክ አምራች አገር ኢራን በብራስልስ ማዕቀብ ጨርሶ እንደማትጎዳ በወቅቱ እየገለጸች ነው። በዕውነትም ለምሳሌ ቻይናን የመሰለች ዋነኛ ገዢዋ ማዕቀቡን ካልተከተለች ይሄው የሚኖረው ፍቱንነት ሲበዛ የሚያጠያይቅ ነው። በነገራችን ላይ ቤይጂንግ በኢራን ላይ ተቀባይ ቧምቧዋን እድትዘጋ፤ ማለትም ማዕቀቡን እንድትከተል ከዋሺግተን በኩል ሲደረግ ለቆየው ግፊት እስካሁን የምትበገር አልሆነችም።

መሥፍን መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ

 

Audios and videos on the topic

 • ቀን 01.02.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/13pr5
 • ቀን 01.02.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/13pr5