የ«ብሪክስ» አባል ሃገራት እና ወቅታዊ ይዞታቸው | ኤኮኖሚ | DW | 17.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የ«ብሪክስ» አባል ሃገራት እና ወቅታዊ ይዞታቸው

የብራዚል፣ ሩስያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪቃ ርዕሳነ ብሔር እና መራሕያነ መንግሥታት ከሁለት ቀናት በፊት የተጠናቀቀውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ባስተናገደችው ብራዚል ዛሬ የሁለት ቀናት ጉባዔ ይጀምራሉ።

በፎርታሌዛ ከተማ የሚወያዩት በምሕፃሩ «ብሪክስ» በመባል የሚታወቁት አምስቱ ሃገራት መሪዎች የቡድናቸውን አንድነት እና ጥንካሬ ለማሳየት ቢሞክሩም፣ ቡድኑ ልል ስብስብ ብቻ ነው።

የምጣኔ ሀብቱ ምሁር ጂም ኦኒል ከብራዚል፣ ሩስያ፣ ህንድ እና ቻይና የመጀመሪያውን ፊደል በመውሰድ «ብሪክ» የሚለውን የአህፅሮት ስም እአአ በ2001 ዓም ሲያወጣ አራቱም ሃገራት በፈጣን የዕድገት ጎዳና ላይ ይገኙ ነበር። ይሁንና፣ በዓለም የተከሰተው የፊናንስ እና የኤኮኖሚ ቀውስ የዕድገታቸውን ጉዞ አሰናከለው። ደቡብ አፍሪቃ ይህኑ ቡድን በ 2009 ስትቀላቀል የአህፅሮት ስሙም ወደ «ብሪክስ » ተቀየረ። ይሁንና፤ የአምስቱን ሃገራት የኤኮኖሚ ጥቅም ማስተባበሩ ቀላል ሆኖ አልተገኘም።

« ሕንድ በርግጥ አዳጊ ሀገር ናት፣ ሩስያ አይደለችም፣ ቻይና ደግሞ የኢንዱስትሪ ኃያል መንግሥት በመሆኑ ጎዳና ላይ ትገኛለች። እና እነዚህ በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሃገራትን እንዴት በአንድ ቡድን ሥር ማሰባሰብ እንደሚቻል አላውቅም። »

ይላሉ በኪል የሚገኘው የዓለም ኤኮኖሚ ጥናት ተቋም ተንታኝ ሮልፍ ላንግሀመር። በቡድኑ ውስጥ ራሱ ትናንሽ ቡድኖች አሉ። ለምሳሌ በ2008 ዓም በዶሀ የልማት አጀንዳ ጉባዔ ላይ ብራዚል እና ሕንድ ከአዳጊ ሃገራት በላቀ ምጥቀት ላይ የሚገኙትን እና በመልማት ላይ ያሉትን ሃገራት ወክለው ነበር የቀረቡት። ከአንድ ዓመትም በኋላ ቻይና እና ሕንድ በተመድ የአየር ንብረት ጉባዔ ላይ የእነሱን ጥቅም የማያስጠብቀውን ረቂቅ ስምምነት ማከላቸው ይታወሳል። ከጥቂት ጊዜ በፊት ባለፈው ግንቦትም ቻይና እና ሩስያ የጋዝ ሽያጭ ውል ተፈራርመዋል፣ ይኸው የ400 ቢልዮን ዩኤስ ዶላሩ ውል ሩስያ ጋዟን ለሌሎች ሃገራትም መሸጥ እንደምትችል ለምዕራቡ ያሳየ ነው።

ይህም ቢሆን ግን፤ በመካከላቸው ውጥረት መኖሩ ይታያል። በፔኪንግ እና በሞስኮ መካከል ከትብብሩ በስተጀርባ ለምሳሌ ቻይና በማዕከላይ እስያ የሚታየውን የሩስያን ተፅዕኖ ለማዳከም የምታደርገው እና ብዙ ህዝብ በማይኖርበት የሳይቤሪያ በርካታ ቻይናዉያን መሥፈር የጀመሩበት ድርጊት ሩስያን ቅር አሰኝቶዋል። በቻይና እና ሕንድ ድንበር የሚካሄደው ውዝግብም የሁለቱን ግዜፍ እስያውያት ሃገራት ግንኙነት አሻክሮታል። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳም፣ ሮልፍ ላንግሀመር የ«ብሪክስ» አባል ሃገራት የጠበቀ ግንኙነት አላቸው ብለው አያስቡም።

«እንደሚመስለኝ፣ እነዚህ ሃገራት ራሳቸውን እንደ ጥሬ አላባ እና የተፈጥሮ ሀብት ተፎካካሪዎች እንጂ እንደ ተጓዳኞች አይተያዩም። »

ሁሉም መፍትሔ ሊያገኙለት የሚገባ የየራሳቸው ችግር ያለባቸው መሆናቸውን ለኤኮኖሚ ትብብር እና ልማት ድርጅት፣ «ኦ ኢ ሲ ዲ» የምርምር ክፍል ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት የ«ሺፍቲንግ ዌልትስ አማካሪ ኩባንያ " ባልደረባ ሄልሙት ራይዘን አስታውሰዋል።

« ደቡብ አፍሪቃ «ብሪክስ» አባል ሃገራት መካከል ንዑሱ ዕድገት መጠን ያስመዘገበች ሀገር ስትሆን ግዙፍ የወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር አለባት። »

Symbolbild BRIC Staaten

እርግጥ፣ ሕንድ ለሶፍትዌር እና ለመድሀኒት ኢንዱስትሪዎችዋ ድጎማ ብትሰጥም፣ ብዙ አዳዲስ የስራ ቦታዎች መፍጠር አላስቻላትም።

የበጀት ሚዛን መጓደል ንዑስ የኤኮኖሚ ዕድገት ብቻ በሚታይባት ብራዚልም ላይ ትልቅ ችግር ደቅኖዋል። የሩስያ ኤኮኖሚ ዕድገት ባለበት እንደቆመ ነው በተባለበት ባሁኑ ጊዜ፣ ቻይና ከሰባት ከመቶ የበለጠ ዕድገት ያስመዘገበችበት ሁኔታ በሌሎቹ የ«ብሪክስ» አባላት ዘንድ እንደ ጥሩ አልታየም። አምሥቱ ሃገራት በጋራ ሊያቋቁሙት ባቀዱት የጋራ የልማት ባንክ ውስጥ የቻይናን ተፀዕኖ ለማሳነስ በማሰብ፣ ለመጀመሪያ የሚያስፈልገውን የ50 ቢልዮን ካፒታልን አምሥቱም ሃገራት እኩል ለመከፋፈል ወስነዋል፤ ምንም እንኳን፣ ለሁሉም እኩል ቀላል ባይሆንም።

ይሁንና፣ ሮልፍ ላንግ እንደሚሉት፣ ሁሉም በያካባቢያቸው ወሳኝ ሚና መያዛቸውን እና «ብሪክስ» ወደፊት ሌሎች በዕድገት ጎዳና ላይ በማኮብኮብ የሚገኙ ለምሳሌ ኢንዶኔሽያ፣ ቱርክ እና ናይጀሪያን የመሳሰሉ ሃገራት የሚጠቃለሉበት ንቅናቄ የመሆን ዕድል አለው።

ዣንግ ዳንሆንግ

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic