የብሪክስ ሀገራት ጉባኤ | ዓለም | DW | 29.03.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የብሪክስ ሀገራት ጉባኤ

አምስቱ በማደግ ላይ የሚገኝ ኤኮኖሚ ባለቤት የሆኑት ሀገሮች አራተኛዉን ጉባኤያቸዉን እያካሄዱ ነዉ። ጉባኤን ህንድ ዉስጥ የጀመረዉ ብራዚል፤ ሩሲያ፤ ህንድ፤ ቻይናና ደቡብ አፍሪቃን ያካተተዉ ይህ ስብስብ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮችን ሊደግፍ የሚችል

ራሳቸዉ የሚያስተዳድሩት ባንክ ለማቋቋም መክረዋል። በጉባኤዉ የተገኙት የተጠቀሱት ሀገራት መሪዎችም በሀገሮቻቸዉ መካከል ያለዉን የንግድ ትስስር ለማጠናከርና ለማስፋፋት ስምምነት ተፈራርመዋል። በአህፅሮተቃል BRICS በመባል በሚታወቁት ሀገራት ወደሶስት ቢሊዮን ህዝብ እንደሚኖር ይገመታል። ብራዚል፤ ሩሲያ፤ ህንድ፤ ቻይናና ደቡብ አፍሪቃ የመጠሪያ ስማቸዉ መነሻ ፊደላት በጋራ ተደርድረዉ ነዉ ይህን ስያሜ ያስገኙት። እነዚህ ሀገሮች በዓለም ከሚታየዉ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት ጋ ራሳቸዉን ለማጣጣም ሲሉ ነዉ ይህን BRICS የተሰኘ የጋራ መድረክ ከጥቂት ዓመት አስቀድመዉ የመሠረቱት።

እንደሀገሮቹ እምነትም የበለፀገዉ ዓለም በማደግ ላይ ያሉትን ሀገሮች የኤኮኖሚ ልማትን መደገፍ አልሆነላቸዉም። ለዚህም ህንድ ኒዉዴሊህ የተሰባሰቡት አምስቱ ሀገሮች ራሳቸዉ የሚያንቀሳቅሱትና የሚያዙበት የገንዘብ ተቋም ለመመስረት ተስማምተዋል። የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንሞሃን ሲንግ ሀገራቱ የተስማሙበትን ይህን እቅድ እንዲያጠኑና የደረሱበትን ዉጤትም በመጪዉ የBRICS ጉባኤ እንዲያቀርቡ ለየመንግስታቱ የገንዘብ ሚኒስትሮች ሃላፊነት መሰጠቱን አመልክተዋል። እንዲህ ያለዉ የልማት ባንክ መቋቋም ተቋማዊ አካል የማዋቀር ፍላጎት መንስኤ እንደሆነ ነዉ በሳኦ ፖሎ የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር ኦሊቨር ስቱንክል የሚስረዱት፤

«የBRICS የልማት ባንክ ማቋቋም ተቋማዊ መዋቅር የማስያዝ ስልት ዉጤት ነዉ። አንድ ድርጅት ተቋማዊ መዋቅር ከሌለዉ ድርጅቱን በመጠኑ ቢሆን አስተማማኝ እንዳይሆን ያደርገዋል። ምክንያቱም ከዓመት ዓመት ቢሰባሰቡም የአባል መንግስታት ግዴታ የሚለዉን ግብ ያጣል። አንድ መዋቅር መኖሩ ለወደፊት የሚኖረዉን ትብብር ቀላል ያደርገዋል። ኤኮኖሚያዉ ትብብር በድጋሚ ዋናዉ ጉዳይ ሆኗል፤ ትንሽ እንኳ አለመግባባት ቢኖር ለBRICS መሠረታዊ ጉዳይ ነዉ። በብራዚልና ህንድ መካከል ያለዉ ንግድ እጅግም የማይወሳ ትንሽ ጉዳይ ነዉ፤ በብራዚል እና ሩሲያ ወይም በሩሲያና በደቡብ አፍሪቃ መካከልም ያለዉም እንዲሁ ነዉ።»

እንዲያም ሆኖ የBRICS አባል መንግስታት በመካከላቸዉ የሚካሄደዉን የንግድ ልዉዉጥ ይበልጥ ለማጠናከር ተዋዉለዋል። ዉሉም ባለፈዉ ዓመት 230 ቢሊዮን ዶላር የነበረዉን እስከ መጪዉ የአዉሮጳዉያን 2015ዓ,ምድ ድረስ ወደ500 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረስ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

እቅዱ የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ እንደሚሉት የአምስቱን ሀገሮች መድረክ ወደጠንካራና አቅም ወዳለዉ ድርጅትነት ሊያሸጋግረዉ ይችላል። የBRICS ሀገራት የመሠረቱት ትስስር በቀላሉ የማይታይ እምቅ አቅም እንዳለዉ ጉዳዩን በቅርብ የሚያጠኑ ተንታኞች ያምናሉ። የመጀመሪያዉ የBRICS ጉባኤ በሩሲያዋ የካተሪንቡርግ ከተማ በተካሄደ ወቅት እደርስበታለሁ በሚል ካለመዉ ግብ ግን እስካሁን አልደረሰም ይላሉ በበርሊን ከጀርመን የዉጭ ጉዳይ ፖለቲካ ተቋም አሌክሳንደር ራሀር፤

«በፋይናንስ ቀዉሱ ምዕራቡ ዓለም መዳከሙን ተመልክተዋል። ከምዕራቡ ዓለም በተቃራኒ የሚገዳደር ኃይል መገንባት እንደማይቻልም ያዉቃሉ፤ በዚህ ምክንያትም አሜሪካና የአዉሮጳ ኅብረት ጠንክረዉ መዉጣታቸዉን አይተዋል። እንዲያም ሆኖ የBRICS ሀገራት በሙሉ የዓለምን ሥርዓት ለማረቅ፤ ተሰሚነት ለማግኘት እና ተፅዕኖም ለማሳረፍ ኃይላችን በጋራ አሰባስበን በተጓዳኝ በአንድ እንደራጅ ይላሉ። ሆኖም በጣም ብዙ ጥያቄ ያለበት ጉዳይ ነዉ።»

ሩሲያና ቻይና ሲቀሩ፤ ብራዚል፤ ደቡብ አፍሪቃና ህንድ በዴሞክራሲያዉ ስርዓታቸዉ ይታወቃሉ። በሀገራቱ መካከል ያለዉ የአስተዳደር ልዩነትም ለልዩነታቸዉ እንደምክንያት ይጠቀሳል። ይህንኑ ልዩነት ይዘዉ ህንድ ላይ የተሰባሰቡት የBRICS አባል ሀገሮች፤ ድህነትን እንዴት መቀነስ እንደሚቻል፤ የምግብ እህል ቀዉስ እንዴት ሊገታ ይችላል፤ መሠረተ ልማትን እንዴት ማሻሻል ይቻላል፤ የቴክኒዎሎጂና እዉቀት ሽግግሩ ምን ያህል ስኬታማ ነዉ፤ ምናልባትም የአየር ንብረት ለዉጥን ለመግታት የሚያደርጉት ጥረት ያስገኘዉን ዉጤት በጋራ ሊቃኙ ይችላሉ።

ፕሪያ ኤሰልቦርን

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic