የብሪታንያ ህዝበ ውሳኔ ውጤትና ቀጣዩ እርምጃ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 28.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የብሪታንያ ህዝበ ውሳኔ ውጤትና ቀጣዩ እርምጃ

የብሪታንያ ህዝብ ባለፈው ሐሙስ ባካሄደው ህዝበ ውሳኔ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት ለመውጣት መወሰኑ ብዙ አነጋጋሪ ጉዳዮችን አስከትሏል ። ብዙም ያልተጠበቀው ይህ ውሳኔ የአውሮጳ ህብረትን እና አባል ሃገራቱን ሲያደናግጥ ብሪታንያውያንን ደግሞ ባልተገመተ መንገድ ከፋፍሏል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:07

የብሪታንያ ህዝበ ውሳኔ ውጤትና ቀጣዩ እርምጃ

ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት ትውጣ አትውጣ በሚል ለዓመታት ሲካሄድ የቆየው ክርክር ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ መልስ አግኝቷል ። የብሪታንያ ህዝብ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ላይመለስ ለ43 ዓመታት ከቆየበት የአውሮጳ ህብረት አባልነት ለመውጣት በይፋ ወስኗል ። አስቀድሞ ለመገመት አስቸጋሪ ሆኖ እስከ መጨረሻው የዘለቀው የዚህ ህዝበ ውሳኔ የመጨረሻ ውጤት አርብ ማለዳ ከታወቀ ወዲህ ፣በብሪታንያም ሆነ በመላው አውሮጳ በአብዛኛው ያሳደረው ድንጋጤ እና ስጋት አሁንም እንዳለ ነው ።የአውሮፓ ህብረት እና አባል ሃገራት በዚህ ባልተጠበቀው ከህብረቱ የእንውጣ ውጤት መደናገጣቸውን ቢያሳውቁም የብሪታንያን ህዝብ ውሳኔ ግን እናከብራለን ነው ያሉት ። አብዛኛዎቹ ብሪታንያ ላይ የሚያስከትለው መዘዝ ቀላል እንደማይሆን ከወዲሁ ሲያስጠነቅቁ አንዳንዶቹ ደግሞ ህብረቱ ያሉበትን ችግሮች እንደገና በማጤን ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል ። የህዝበ ውሳኔው ውጤት ብሪታንያ «ከአውሮጳ ህብረት ትልቀቅ» እንደሚሆን ብዙም ያልተጠበቀ ቢሆንም የአውሮፓ ህብረት ግን እንውጣ ለሚለውም ውሳኔ ራሱን አዘጋጅቶ እንደነበር ነው ያሳወቀው ። በዚሁ መሠረትም የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዦን ክሎድ ዩንከር አርብ በሰጡት መግለጫ ብሪታንያ ከህብረቱ አባልነት የምትወጣበት ድርድር ቶሎ እንዲጀመር ጠይቀዋል ።
«ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት በምትለቅባቸው ደንቦች እና ቅድመ ሁኔታዎች ላይ በአስቸኳይ ድርድሮች ለመጀመር ዝግጁ ነው

። ይህ ሂደት እስከሚያበቃ ድረስ ብሪታንያ ከነሙሉ መብቶችና ግዴታዎቿ ጋር የአውሮፓ ህብረት አባል እንደሆነች ትቀጥላለች ።ብሪታንያ ባፀደቀቻቸው ውሎች መሠረት ከህብረቱ እስክትወጣ ድረስ የአውሮፓ ህብረት ህጎች ለብሪታንያ እና በብሪታንያ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆናቸው ይቀጥላል ። በዚህ ዓመት በየካቲት ወር ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር የደረሰችበት አዲስ ስምምነት ተግባራዊ አይሆንም ። ዳግም ድርድር አይካሄድም ።ብሪታንያ ወደፊት የህብረቱ የቅርብ ተጓዳኝ ትሆናለች የሚል ተስፋ አለን ። »
የአውሮጳ ህብረት ድርድሩን ለመጀመር ዝግጁ ነኝ ብሏል ። ታዲያ ከዚህ በኋላ የፍቺው ድርድር እንዴት ነው የሚጀመረው? ዋና ዋና የመደረዳሪያ ነጥቦቹስ ምን ይሆናሉ ? ለንደን ነዋሪ የሆኑት የህግ ባለሞያ እንዲሁም የኤኮኖሚ የኢሚግሬሽን ጉዳዮች አማካሪ አቶ ታዬ አለማየሁ ያስረዱናል ።
ብሬክዚት ወይም የብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት መልቀቅ ህብረቱን ይበልጥ ለመፈረካከስ አደጋ እንዲጋለጥ ያደርጋል የሚል ስጋት አለ ። የብሪታንያ ህዝበ ውሳኔ ውጤት በአውሮፓ ህብረት ላይ እምነት የሌላቸውን እና ሉዓላዊነታችንንም እየተጋፋ ነው የሚሉትን በአባል ሃገራት የሚገኙ ብሄረተኞችን ማስደሰቱ ማስፈንጠዙ ቀጥሏል ። ቀኝ ፅንፈኞች አጋጣሚውን በመጠቀም በየሃገሮቻቸው ህዝቡ ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስድ የሚያካሂዱትን ቅስቀሳ አጠናክረው ቀጥለዋል ። የፅንፈኞች እንደገና ማቆጥቆጥ የሚያሳስባቸው ወገኖች ህዝበ ውሳኔውን የአውሮጳ ህብረት እንዲበታታን በሩን የሚከፍት የመጀመሪያ እርምጃ አድርገው ይቆጥሩታል ። አቶ ታዮ ግን ይህ በሁለት መንገድ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው ይላሉ ።
የህዝበ ውሳኔው ውጤት የብሪታንያን ህዝበ ይበልጥ ከፋፍሏል ። ከአራቱ የብሪታንያ ግዛቶች አንዷ የሆነችው ስኮትላንድ ምርጫዋ ከህብረቱ ጋር መቆየት ነው ። ከህዝቧ አብዛኛው ከህብረቱ ጋር መቆየትን ቢመርጥም በአጠቃላዩ የብሪታንያ

ድምፅ ምክንያት ከህብረቱ እንዲወጣ መደረጉን አልተቀበለም። ይህም ዳግም ከብሪታንያ የመነጠል ጥያቄን አስነስቷል ። በአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት የነፃ ዝውውር መብት ተጠቃሚ የሆኑት ወጣት ብሪታንያውያንም ውጤቱን ተቃውመው ሌላ ህዘበ ውሳኔ እንዲካሄድ እየጠየቁ ነው ። በብሬክዚት ላይ ዳግም ህዝበ ውሳኔ ማካሄድ ይቻል ይሆን ? የስኮትላንድስ ጥያቄ እና ማስጠንቀቂያስ ምን ሊያስከትል ይችላል
ስለ ሐሙስ ህዝበ ውሳኔ ከሚሰጡት አስተያየቶች አብዛኛዎቹ ውጤቱ ከህብረት ይልቅ መከፋፈልን የሚያበረታታ በመሆኑ አይደገፍም የሚሉ ናቸው ። የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገብረ እግዚዘብሔር ከጠየቃቸው አስተያየት ሰጭዎች አንዳንዶቹ ተመሳሳይ ሃሳቦች ነው የሰጡት ።
የብሪታንያ ህዝበ ውሳኔ ውጤት በታወቀ በማግሥቱ ቅዳሜ የአውሮጳ ህብረት መስራች አባል ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት ደግሞ የጀርመን የፈረንሳይ እና የኢጣልያ መሪዎች እንዲሁም የአውሮጳ ህብረትፕሬዝዳንት ዶናልድ ቱስክ በቀጣይ እርምጃዎች ላይ መክረዋል ። ዛሬ ደግሞ የብሪታንያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን የሚገኙበት የህብረቱ አባል ሃገራት የመሪዎች ጉባኤ ማምሻውን ይጀመራል ። ጉባኤው ነገም ይቀጥላል ። ነገ ግን ካሜሩን አይገኙም።
ስለ ብሬክዚትና ተያያዥ ጉዳዮች ጥያቄ አስተያየት ወይም ጥቆማ ካላችሁ በSMS በፌስቡክ በኢሜል እና በዋትስአፕ አድራሻዎቻችን ላኩልን በስልክም መልዕክቶቻችሁን ልትተዉልን ትችላላችሁ ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic