የብሪታኒያ ሕዝብ ውሳኔ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 21.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የብሪታኒያ ሕዝብ ውሳኔ

ብሪታንያ ከአዉሮጳ ኅብረት አባልነት ትውጣ ወይስ በአባልነት ትቀጥል የሚል ምርጫ የተሰጠው የብሪታንያ ሕዝብ ከነገ ወዲያ ድምፁን ይሰጣል። ከወዲሁ ለመገመት አስቸጋሪ የሆነው የዚህ ሕዝብ ውሳኔ ውጤት በጉጉት እየተጠበቀ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:23

የብሪታኒያ ሕዝብ ውሳኔ

ውጤቱ ከአውሮጳ ኅብረት እንውጣ ወይም በእንግሊዘኛ ምህፃር «BREXIT» ከሆነ ለብሪታንያም ሆነ ለአውሮጳ ኅብረት ምን ተፅኖዎች ይኖሩታል? ብሪታንያ ከአዉሮጳ ኅብረት ትወጣ ወይስ ከኅብረት ጋር ትቆይ የሚለው ጥያቄ ከነገ ወዲያ በሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ መልስ ያገኛል ። ህዝቡን ለሁለት በከፈለው እና ብዙ ሲያጨቃጭ እና ሲያከራክር በቆየው በዚህ ጥያቄ ሰበብ አንዲት እንደራሴ ሃገሪቱ ከኅብረት ጋር መቆየቷን እቃወማለሁ በሚል ሰው እስከ መገደል ደርሰዋል። ባለፈው ሰሞን የተካሄዱ የዳሰሳ ጥናቶች እንዳመለከቱት ብሪታንያ ከኅብረቱ ጋር ትቆይ የሚሉት እና እድትወጣ የሚፈልጉት ዜጎች ቁጥር ተቀራራቢ ነበር። ምርጫው ሲቃረብ ግን ሃገሪቱ ከአውሮጳ ህብርት ጋር እንድትቆይ የሚፈልገው ብሪታንያዊ ቁጥር እንድትወጣ ከቋመጠው እንደሚበልጥ እያሳዩ ነው። ይሁንና ከአውሮጳ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን አንስቶ በኋላም በአውሮጳ ኅብረት ላለፉት 43 ዓመታት በአባልነት የቆየችው ብሪታንያ በዚህ ሕዝብ ውሳኔ አባልነትዋ ይቋረጥ ይቀጥል ከነገ በስተያ ነው የሚታወቀው። ያም ሆኖ ብትወጣ ምን ሊከተል ይችላል ማነው ተጊጂው ተጠቃሚውስ ምን ዓይነት ተጽእኖስ ይኖረዋል የሚሉት ሲነሱ ሲጣሉ የከረሙ የመነጋገሪያ ነጥቦች ናቸው። በአውሮጳ ኅብረት ውል አንቀጽ 50 መሠረት ማንኛውም የአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገር ከአባልነት ሊወጣ የሚችል ቢሆንም የአዉሮጳ ኅብረት ብሪታንያ ከኅብረት ጋር እንድትቆይ ነው የሚፈልገው። የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ማርቲን ሹልዝ ብሪታንያ ከኅብረቱ ጋር ለምን ትቆይ እንደሚሉ ያስረዱት ሦስት ዓብይ ጉዳዮችን በማንሳት ነበር።

« ከአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት በኤኮኖሚ እድገት ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ፣ የቡድን ሰባት አባል ሃገር፣ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላት፣ የተመ የፀጥታ ምክር ቤት አባል፣ እነዚህ ሦስት መስፈርቶች ብቻ የሚያሳዩት የአውሮጳ ኅብረት ኤኮኖሚ እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ ፖለቲካ ያለ ጥርጥር ደካማ ይሆናል።»
ብሪታንያ ከአዉሮጳ ኅብረት ትውጣ አትውጣ የሚለው ክርክር የተጀመረው ሃገሪቱ የአዉሮጳ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን አባል ከሆነችበት ከጎርጎሮሳዊው 1973 ዓ,ም አንስቶ ነው። ብሪታንያ ኋላ የአዉሮጳ ኅብረት የተባለው የአውሮጳ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን እንዲመሠረት ያበቃው የጎርጎሮሳዊው 1957 ቱ የሮሙ ውል ፈራሚ አይደለችም። የሮሙን ውል የፈረሙት ቤልጂግ ፣ፈረንሳይ፣ ኢጣልያ፣ ላግዘምበርግ፣ ኔዘርላንድስና ምዕራብ ጀርመን ናቸው። ብሪታንያ ውሉ ውስጥ ያልገባችው የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ የተሰባሰቡበት የጋራ ብልፅግና ማህበር ይበቃኛል ብላ ነበር ከዚያ በኋላ ግን በ1963 በኋላም በ1967 የኮሚሽኑ አባል ለመሆን ብታመለክትም ያያኔው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ሻርል ደጎል ከብሪታንያ ኤኮኖሚ የተወሰኑት ዘርፎች ከአውሮጳ ኤኮኖሚ ጋር አይመጣጠንም ሲሉ በመቃወማቸው ሳይሳካ ቀርቷል። ይሁንና ደጎል ከፕሬዝዳንትነት ከተነሱ በኋላ ብሪታንያ ለሦስተኛ ጊዜ አመልክታ በጎርጎሮሳዊው ጥር አንድ 1973 የኮሚሽኑ አባል ለመሆን በቃች። ብሪታንያ የአውሮጳ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን አባል የሆነችው በወግ አጥባቂው በኤድዋርድ ሂዝ ዘመነ መንግሥት ነበር። ያኔ በሃሮልድ ዊልሰን የሚመራው ተቃዋሚው የሌበር ወይም የሠራተኛ ፓርቲ በ1974 የምርጫ ዘመቻ በብሪታንያን የአዉሮጳ ኤኮኖሚ ኮሚሽን አባልነት ላይ እንደገና ለመደራደር እና ብሪታንያ ከኮሚሽኑ ጋር ትቆይ ወይም ትውጣ በሚለው ምርጫ ላይ ሕዝብ ውሳኔ እንዲካሄድ

እንደሚያደርግ በገባው ቃል መሠረት ሥልጣን ከያዘ በኋላ በ1975 ሕዝብ ውሳኔ ተካሄደ። በወቅቱም ዋና ዋና የሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሃገሪቱ በአባልነት መቀጠልዋን ሲደግፉ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ግን ጎልቶ የሚታይ ክፍፍል ነበር። ይሁንና ብሪታንያ በአዉሮጳ ኅብረት አባልነት ትቀጥል የሚለው ድምፅ አመዝኖ ከኅብረት ጋር ቆይታለች። ሆኖም የ«BREXIT» ጥያቄ ከዚያም በኋላ ቀጥሎ በ2012 የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ሕዝብ ውሳኔ መካሄዱን ቢቃወሙም ወደፊት ሊካሄድ እንደሚችል ሃሳብ በማቅረብ አልፈውት ነበር። የቀድሞው የ «BREXIT» ጥያቄ ሲቀጥልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወግ አጥባቂው ፓርቲያቸው በ2015 የሚመረጥ ከሆነ በአዉሮጳ ኅብረት አባልነት መቀጠል አለመቀጠል ላይ ሕዝብ ውሳኔው እንዲካሄድ ቃል ገቡ። በዚሁ መሠረት ከነገ ወዲያ ሰኔ 16፣ 2008 ዓ,ም ወይም በጎርጎሮሳዊው ሰኔ 23፣ 2016 ዓ,ም የብሪታንያ ሕዝብ ከአውሮጳ ኅብረት መውጣትን ደግፎ ወይም ተቃውሞ ድምፁን ይሰጣል። ውጤቱ ምን እንደሚሆን ከሕዝብ ውሳኔው በኋላ ነው የሚታወቀው ። ምናልባት ውሳኔው ከአውሮጳ ኅብረት መውጣት ቢሆን ማን ይጠቀማል ለሚለው ከሚሰጡ አስተያየቶች አመዛኙ ብሪታንያ ከኅብረት መልቀቅዋ ይጎዳታል እንጂ ይጠቅማታል የሚሉ አይደሉም። ለ26 ዓመታት ያህል ብሪታንያ የኖሩት የህግ ባለሞያው አቶ ታዬ አለማየሁ በብሪታንያ የአውሮጳ የስደተኞች ሕግ አማካሪ ናቸው። የኢትዮጵያ የውጭ ኤኮኖሚ አማካሪም ነበሩ። ርሳቸውም ብሪታንያ ከኅብረት መውጣትዋ ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም ይላሉ።
ከሃገሪቱ የውጭ ንግድ ግማሽ ያህሉ ከኅብረት አባል ሃገራት የሚካሄድ መሆኑ እንዲሁም ወደ ሃገርዋ ከምታስገባቸው ምርቶች ከግማሽ የሚበልጡት ከነዚሁ ሃገራት መምጣታቸው ብሪታንያ ከኅብረት ብትወጣ ይበልጥ ተጎጂ መሆንዋን ጥናቶች ያሳያሉ። «ቤርትልስማን» የተባለው የጀርመኑ የምርምር ተቋም ባካሄደው ጥናት ብሪታንያ ከአዉሮጳ ኅብረት ከወጣች ኤኮኖሚዋ በ14 በመቶ እንደሚቀንስ ይህም ኪሳራውን ወደ 300 ቢሊዮን ዩሮ እንደሚያደርሰው አስታውቋል። ይሁንና ብሪታንያ ከኅብረት ትውጣ የሚሉት ወገኖች ሃገሪቱ ለኅብረት የምትዋጣው ገንዘብ በዝቷል፣ ከኅብረት የምታገኘው ጥቅም አናሳ ነው፣ኅብረት

ሉዓላዊነታችንን ይጋፋል፣ ከኅብረት ብትወጣ የስራ እድልም ይሰፋል ወደ ብሪታንያ የሚመጡት ስደተኞች ቁጥርም ይገደባል፣ ኤኮኖሚውም ያድጋል ሲሉ ይከራከራሉ። የነርሱስ መከራከሪያ ምን ያህል ተቀባይነት ይኖረው ይሆን ?
የዛሬ 41 ዓመት ብሪታንያ በአውሮጳ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን አባልነት ትቀጥል ወይስ አትቀጥል የሚል ምርጫ የቀረበለት የብሪታንያ ሕዝብ ከማህበሩ ጋር መቆየቱን መርጦ ነበር። ከነገ ወዲያ ለሁለተኛ ጊዜ ከአውሮጳ ኅብረት ጋር እንቆይ ወይስ እንውጣ የሚል ጥያቄ ሲቀርብለት መልሱ ምን ይሆን ? የሕዝብ ውሳኔውን ውጤት ለማወቅ እስከ ከነገ ወዲያ መጠበቅ ያስፈልጋል። የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቬድ ካሜሩን ግን ከወዲሁ ህዝቡ በተለይም በርሳቸው የእድሜ ክልል እና ከዚያም በላይ እድሜ ያለው ዜጋ ለወጣቱ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ሲል ከኅብረት መውጣትን ተቃውሞ ድምጹን እንዲሰጥ ተማጽነዋል። ተማጽኗቸው ውጤት ማምጣት አለማምጣቱ ከአንድ ቀን በኋል ይታወቃል። አድማጮች በብሪታንያ ሕዝብ ውሳኔ እና አንድምታዎቹ ላይ ያተኮረው የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን በዚሁ ያበቃል። በዝግጅቱ ማብራሪያ በመስጠት የተባበሩንን አቶ ታዬ አለማየሁን አመሰግናለሁ። አድማጮች በተላለፈው ዝግጅት ላይ አስተያየት ጥያቄ እንዲሁም ጥቆማ ካላችሁ በ«SMS» በኢሜል በስልክ በፌስቡክ እንዲሁም በደብዳቤ ላኩልን እናስተናግዳለን ።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic