የብሪታኒያ ሕዝበ-ውሳኔ እና ኢትዮጵያ | ኤኮኖሚ | DW | 22.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የብሪታኒያ ሕዝበ-ውሳኔ እና ኢትዮጵያ

ብሪታኒያውያን በነገው ዕለት በአገራቸው በአውሮጳ ኅብረት እጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን ህዝበ-ውሳኔ ይሰጣሉ። ሕዝበ ውሳኔው ከአውሮጳ ባሻገር ሊኖረው የሚችለው ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ እያከራከረ ነው። ሕዝበ-ውሳኔው ከአውሮጳ እና ብሪታኒያ ከፍተኛ የልማት እርዳታ ለምታገኘው ኢትዮጵያ ግን ያን ያክል ለውጥ የሚያመጣ አይመስልም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:35

የብሪታኒያ ሕዝበ-ውሳኔ እና ኢትዮጵያ

የአውሮጳ ኅብረት ከጎርጎሮሳዊው 2014-2020 ባሉት ዓመታት ለኢትዮጵያ 745ሚሊዮን ዩሮ የልማት እርዳታ ለማቅረብ ሥምምነት ፈጽሟል። ብሪታኒያ በጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም ለተለያዩ የዓለም አገራት ከምትሰጠው የተመዘገበ የልማት እርዳታ ውስጥ 334 ሚሊዮን ፓውንድ ለኢትዮጵያ ደርሷታል። ነገ ሁለቱ የኢትዮጵያ የልማት እርዳታ አቅራቢዎች ከጎርጎሮሳዊው 1975ዓ.ም ጀምሮ የመሰረቱት ትዳር እጣ ፈንታ ይወሰናል።

ብሪታኒያ አባል የሆነችበት የአውሮጳ ኅብረት ለኢትዮጵያ የሚያቀርበው የልማት እርዳታ በዘላቂ ግብርና፤ የምግብ ዋስትና እና ጤና፤ የመንገዶች እና የኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ላይ ያተኩራል።

ዶ/ር ጌትነት ኃይሌ በኖቲንግሐም ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ ትምህርት ቤት የኤኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው። ዶ/ር ጌትነት ብሪታኒያውያን ነገ በሚያደርጉት ህዝበ ውሳኔ ከአውሮጳ አባልነት ለመውጣት ወሰኑም አልወሰኑም አገሪቱ ለኢትዮጵያ በምትሰጠው እርዳታ ላይ ለውጥ እንደማያመጣ ይናገራሉ።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እርስ በርስ የሚገበያዩ አገራት ወደ ጦርነት የመግባት እድላቸው አናሳ ነው በሚል እምነት ኤኮኖሚያዊ ትብብርን ለማጠናከር የተቋቋመው ህብረት በሂደት እየተጠናከረ መምጣቱ ይነገርለታል። ኅብረቱ ዜጎች እና ሸቀጦች ከአንዱ ወደ ሌላው በቀላሉ እንዲዘዋወሩ የሚፈቅድ የወጥ ገበያ (single market) ሥርዓት ዘርግቷል። ከ28ቱ አባል አገራት መካከል 19ኙ በዩሮ የሚገበያዩ ሲሆን አንድ ምክር ቤትም አለው። በአካባቢ ጥበቃ፤ ትራንስፖርትና የሸማቾች መብት ጥበቃ በመሰሉ ጉዳዮች ላይም ህብረቱ የጋራ ህግጋት አለው።

ኅብረቱ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሐ አገሮች ከጦር መሳሪያ እና ጥይት ውጪ ምርቶቻቸውን በአውሮጳ ገበያ እንዲገበያዩ የፈቀደበት ሥርዓት አለው። በሥርዓቱ በአሁኑ ወቅት ከ49 በላይ አገራት ተጠቃሚዎች ናቸው። ዶ/ር ጌትነት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሐ አገሮች በአውሮጳ ገበያ ከቀረጥ ነጻ እንዲገበያዩ የሚፈቅደው ሥርዓት የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት እና ንግድ ማበረታታቱን ይናገራሉ።

እሸቴ በቀለ
አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic