የብሩንዲ የፖለቲካ ቀውስ ፥ የአፍሪቃ ዋንጫ አስተናጋጅ | አፍሪቃ | DW | 17.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የብሩንዲ የፖለቲካ ቀውስ ፥ የአፍሪቃ ዋንጫ አስተናጋጅ

ለሳምንታት የዘለቀ ደም አፋሳሽ አመፅ መካከለኛው አፍሪቃ የምትገኘው ሀገር፤ ብሩንዲን አጨናንቋል።የሀገሪቱ ጦር ከአማፂያን ጋር እየተታኮሰ በርካታ ሰዎች መሞታቸውም ተረጋግጧል። ከዚህም በተጨማሪ ማንነታቸው ያልታወቁ እና የወታደር የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች በርካታ የመንግሥት ፓርቲ አባሎችን መግደላቸው ተሰምቷል።

በሚመጣው ግንቦት እና ሰኔ ወር ብሩንዲ ውስጥ ምክር ቤታዊ እና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይካሄዳል። የገዢው ፓርቲ መሪ ፒር ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ ዙር በፕሬዘደንትነት እቀርባለው ማለት ግጭቱን ይበልጥ አፋፍሞታል። የብሩንዲ ህገ መንግሥት ለአንድ መሪ የስልጣን ዘመን ቢበዛ 2 የምርጫ ዙር ነው ያስቀመጠው። ይህም እኢአ በ2000 ዓም በተደረገ የሰላም ስምምነት ፀድቋል። ይሁንና ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ ለመጀመሪያ ጊዜ ማለትም ፤ ከ10 ዓመት በፊት ሲመረጡ፤ «የመረጠኝ ህዝቡ ሳይሆን ምክር ቤቱ ነው» በሚል ምክንያት የስልጣን ዘመናቸውን የሚያራዝሙበትን ምክንያት ሰጥተዋል።

ለምርጫ ታዛቢዎች የአመፁ መጠናከር ከምርጫው መቃረብ ጋር ይያያዛል። የሰብአዊ መብት ተሟጋች ፤ፒር -ካቬ ቦኒምፓም በዚህ ይስማማሉ።« ጥቃቶች ሲፈፀሙ የሚታየው ልክ በገዢው ፓርቲ እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ግጭት ሲነሳ ነው።»

እንደ ቦኒምፓ፤ ተቃዋሚዎች ገዢው መንግሥት የምርጫ ምዝገባውን እያጭበረበረ ነው ብለው ያምናሉ ይላሉ። የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚቴ በበኩሉ ይህንን ወቀሳ ያጣጥላል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቦኒምፓ ሲቪል ማሕበረሰቡም ቢሆን በምርጫው የምዝገባ አሠራር ደስተኛ እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት። « ሆን ተብሎ ተቃዋሚዎችን ለማስፈራራት እና ለማሸማቀቅ ሲባል ፍተሻ ይካሄድ ነበር።ይህም ከፖለቲካዊ ግጭት ጋር ግንኙነት እንዳለው ለመገመት ያስችላል።»

የመብት ተሟጋቹ ቦኒምፓ መንግሥትን የሚቃወም አስተያየት በመስጠታቸው ታስረው እንደነበር ይናገራሉ። ጋዜጠኞችም ቢሆኑ ነፃነት እንደሌላቸው እና ለህይወታቸው እንደሚሰጉ ነው የሚናገሩት። RPA የተባለው የተቃዋሚዎች የሬዲዮ ጣቢያ ባልደረባ የሆነ አንድ ጋዜጠኛ ለዶይቸ ቬለ እንደተናገረው በቅርቡ ከተጣለበት ጥቃት ለጥቂት ነው የተረፈው። የመካከለኛው አፍሪቃ የግንኙነት መረብ ባልደረባ ጌዚነ አሜስ ፤ ለተቃዋሚዎች እና የመብት ተሟጋቾች የመፈናፈኛው እድል እጅግ ውስን ነው።«ይህም ማለት ሀሳብ የመስጠት እና የመሰብሰብ መብታቸው የቀነሰ ነው። መንግሥት ደግሞ በሲቪል ማህበረሰብ እና የመብት ተሟጋቾች ላይ ጭቆናውን ቀጥሏል። »

በዛ ላይ መንግሥት እና ተቃዋሚዎች አንድ ዓይነት ህግ የላቸውም ይላሉ።« ይህም ግልፅ የሚሆነው ለምሳሌ ተቃዋሚዎች ልክ ከምርጫዎቹ ሁለት ሳምንታት አስቀድመው ብቻ ነው የመሰብሰብ እና የምርጫ ዘመቻ የማካሄድ መብት ያላቸው። ከዚያ ቀደም በነበሩት ጊዜያት የመሰብሰብ መብት የላቸውም ። ገዢው ፓርቲ ግን ይህን ዕለት ከዕለት ይችላል። ይህ ደግሞ ጥቅም አለው። ምክንያቱም አንዱ ፓርቲ ብቻ ነው ሁሌ እይታ ያለው።»

መንግሥትን የሚቃወም ወይም የፕረዚዳንቱን ለ3ኛ ጊዜ ለምርጫ መቅረብ የሚቃወሙ ከባድ ፍርድ ይጠብቀዋል ሲሉ አሜስ፤ የመንግሥት ቃል አቀባይ ኦኔሲሜ ንዱዊማና እንደሱ አይደለም ይላሉ። ይልቁንስ ፤ ተቃዋሚዎች የምርጫ ሂደቱን ሊያበላሹ ብሎም መንግሥትን ሊገለብጡ ነው የተነሳሱት። « ሰዎች የገዢውን ፓርቲ ስም ያጠፋሉ፤ ወይም ይተነኩሳሉ። ይህም በዚህ ላይ የሚደረገው አፀፋ፤ አመፅ ማስነሳቱን ለማየት ነው። እኛ የሚመስለን ብሩንዲ ውስጥ አመፅ እስኪነሳ ድረስ የሚራመዱ እና በዚህም ብጥብጥ መካከል የሽግግር መንግሥትነቱን ስልጣን ሊቆናጠጡ የሚሹ ሰዎች ከተቃዋሚዎቹ ውስጥ ይገኛሉ። »

ፕሬዚዳንቱ ለህዝብ ቅርብ ለመሆን ይሞክራሉ። የይምረጡኝ ስጦታዎች ያከፋፍላሉ፣ የምርጫ ድግስ ያደርጋሉ። ይሁንና ተወዳጅነታቸው እየቀነሰ ነው። እንደ ጌዚነ አሜስ ፤ ብሩንዳዊያኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ መንግሥት ቃል የሚገባውን እንደማይወጣው ተገንዝበዋል። አሜስ ህዝቡ ምርጫ አድክሞታል ፤ ይህ ግን የግድ በመንግሥት ምክንያት ብቻ አይደለም ይላሉ። ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ አንድ የጋራ የሚሉት እጩ ያስፈልጋቸዋል።

የእውቀት እና የልማት መድረክ የተሰኘ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ፓሲፊክ ኒኒናሃዝቬ ፤ ሀገሪቱ አለም አቀፋዊ ትብብር ብታገኝ ይመርጣሉ፤« ህዝቡን ከማያከብር መንግሥት ጋር ነው እየሰራን ያለነው። ነገር ግን ለጋሽ ሀገራቱን ይሰማል። እና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ የሀገሪቱን 50 ከመቶ ማስተዳደሪያ እንደሚሸፍን ለማስታወስ እወዳለሁ። ስለሆነም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለሀገሪቱ ኃላፊነት አለበት።»

ይላሉ ኒኒናሃዝቬ። ጌዚነ አሜስ ደግሞ የአውሮፓ ሕብረት አንድ አይነት ርምጃ ያስፈልገዋል ባይ ናቸው።« የብሩንዲን ወቅታዊ ልማት ወጥ ለማድረግ የአውሮፓ ህብረት አንድ አይነት ውሳኔ ያስፈልጋል፤ በግልፅ፤ የፕረስ፣ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ እና የመሰብሰብን ነፃነት የሚጠይቅ። ህገ መንግሥቱ እንዲቀየር እና ነፃ ምርጫ እንዲካሄድ የሚያዝ »

የአፍሪካ ዋንጫን እንደ ጥሩ ገፅታ ማሳያ

የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ሀገር ኤኳቶሪያል ጊኒ ከዚህ ዝግጅት ትርፋማ ለመሆን እየሞከረች ነው በመባል ትተቻለች። በተለይ የሀገሪቱ መንግሥት ዝግጅቱን ከጥሩ ገፅታው ብቻ ለማሳያ እየተጠቀመበት እንደሆነ የመብት ተሟጋቾች ይናገራሉ። ትንሻ የመካከለኛው አፍሪቃ ሀገር - ኤኳቶሪያል ጊኒ ከጥር 9 እስከ የካቲት 1 , 2007 ዓም የሚዘልቀውን የአፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው ሞሮኮን ተክታ እንድታዘጋጅ የተወሰነው። ተረኛ የነበረችው ሞሮኮ ባለፈው ህዳር ወር ነበር በምዕራብ አፍሪቃ የተዛመተውን ገዳዩን የኤቦላ ቫይረስ ፍራቻ ውድድርን እንደማታዘጋጅ ያስታወቀችው። ምንም እንኳን ኢኳቶርያል ጊኒ ከሁለት ዓመት በፊት የተካሄደውን የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ከጋቡን ጋር በጋራ ብታዘጋጅም ፤ 800 000 ገደማ የሚሆን ነዋሪ ያላት ሀገር ዘንድሮ ብቻዋን ነው ዝግጅቱን መወጣት ያለባት።

« የማላቦ መንግስት የሀገሪቱን የውጭ ገፅታ ለማሻሻል ይሞክራል። በአለም አቀፍ ዘንድ ገፅታውን ለመቀየር ሲሞክር ይህ የመጀመሪያው ጊዜ አይደለም »ይላሉ ከሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል ቪክቶር ኖጉሪያ ።እንደ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለዓመታት የኤኳቶሪያል ጊኒን መንግሥት የሰብአዊ መብትን አያከብርም ሲሉ ተችተዋል።

«የሰብአዊ መብት እና የፖለቲካዊ ሁኔታውን በተመለከተ በግልፅ ተቃዋሚዎችን የሚነካ ጨቋን እና አምባ ገነን መንግሥት ነው ያለው ፤ የሀገሪቱ የፍትህ አሰራር ሂስ የሚያሰነዝር ነው። ልዩ ለግድያ የተዘጋጀ ቦታ አለ፤ ከዚህም በተጨማሪ የፕረስም ሆነ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብት የተጨቆነ ነው።»

አምንስቲ ኢንተርናሽናል ባለፉት አመታት የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ክስ ሳይመሰረትባቸው በዘፍቃድ እየታሰሩ እና እየተገረፉ ነው ሲል ዘግቧል።እንደዚሁ ድርጅት ዘገባ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ቢያንስ አራት እስረኞች ተገድለዋል። ኤኳቶሪያል ጊኒ ለሁለት ሳምንታት ያክል ብቻ ነው የሞት ብይኗን ያቋረጠችው። ይህም የፖርቹጋል ቋንቋ ተናጋሪ ሀገራት ማህበረሰን ለመቀላቀል መስፈርቶችን ማሟላት ስለነበረባት እንደሆነ ይነገራል።

የተፈጥሮ ሀብትን በተመለከተ ኤኳቶሪያል ጊኒ በዘይት እና በጋዝ ከአፍሪቃ ሀብታም ከሆኑት ሀገራት ተርታ ትመደባለች። ይሁንና ተራው ሰው ከዚህ ተጠቃሚ ሊሆን አልቻለም። የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከጥሬ ሀብት የውጭ ገበያ የሚገኘውን ገንዘብ ለራሳቸው በግል ባንካቸው እንደሚያስገቡ ይተቻሉ። እኢአ በ2013 ዓም በተደረገው የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ጥናት መዘርዝር ከዓለም በሙስና ከተዘፈቁ ሀገራት ኤኳቶሪያል ጊኒ ከ177 ኛ 163ኛ ቦታውን ነበር የያዘችው፤ ታድያ ከአለም በሙስና የተዘፈቁ 20 ሀገራት አንዷ የሆነችው ሀገር፤ በባለፈው ዓመት መዘርዝር ጀረጃዋ ጨርሶ አልተጠቀሰም።

« ሀገሪቱ የዘይት ሀብት ስላላት የህዝቡ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት ጋር ሲነፃጸር በአማከይ ከፍተኛ ነው። ይሁንና ድህነቱ እና እኩል አለመሆኑ በሀገሪቱ ጨምሯል። ህዝቡ ከሀገሪቱ ሀብት ተጠቃሚ እየሆነ አይደለም።

ይላሉ ከሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ኖጉሪያ፤ እኢአ ከ 1979 ዓም ጀምሮ ፕሬዚዳንት ቴውድሮ ኦቢያንግ ንጉማ ሀገሪቱን ይመራሉ። የመብት ተሟጋቹ እንደሚሉት ፕሬዚዳንቱ ይህንን አጋጣሚ ለጥሩ ስም እየተጠቀሙበት ነው።

« ይህ ክስተት ፤ የፕሮፖጋንዳ ዝግጅት ነው። ነገር ግን በሌላ በኩል ስላለው የሀገሪቱም ገፅታ ትኩረት እንዲሰጥ ይጠቅማል። ተስፋ የምናደርገው ጋዜጠኞች እድሉን ተጠቅመው ይህንንም እንዲያደርጉ ነው። ርግጥ ነው ቁጥጥሩ ጥብቅ ይሆናል። ነገር ግን ጋዜጠኞች በዚህ ጉዳይ ላይ ፍላጎቱ ካላቸው ፤ በሀገሪቱ ትኩረት ስላላገኘው ነገር ሊዘግቡ ይችላሉ። »

ይላሉ ኖጉሪያ። በርግጥ የዘንድሮው የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር አዘጋጅ ሀገር ኤኳቶሪያል ጊኒ ከዚሁ ዝግጅት በምን እንደምትጠቀም በቀጣዩ ሳምንታት የሚታይ ይሆናል።

ዲርከ ኮፕ/ ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic