የብሩንዲ ስደተኞች በኮንጎ | አፍሪቃ | DW | 28.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የብሩንዲ ስደተኞች በኮንጎ

በርካታ የብሩንዲ ዜጎች በሃገራቸው የሚካሄደውን ግጭት ሸሽተው ጎረቤት ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተሰደዋል ። በተጠለሉበት በዚህ ሃገር ከባድ ችግር ላይ የሚገኙት እነዚህ ስደተኞች ተስፋ የቆረጡም ናቸው ። አናድንዶቹ ደግሞ እድላቸውን ራሳቸው እየወሰኑ ነው ።

ሉዜንዳ ምሥራቅ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ውስጥ ደቡብ ኪቩ በተባለው ግዛት ስር የምትገኝ ከተማ ናት ።ከተማይቱ ከታንጋኒካ ሐይቅ በጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው ያለችው ።ባሻገር በሚገኘው የብሩንዲ ደቡባዊ ክፍል ስደተኞች ድንገት ጥለዉት የመጡት አካባቢ አለ ። በሉዜንዳ የስደተኞች መጠለያ ይገኛል ። መጠለያው ውስጥ ካሉት አንዱ ድየዶኔ ነው ። ለደህንነቱ ስለሚፈራ ትክክለኛ መጠሪያ ስሙን አልተናገረም ።ታሪኩን ግን በፈቃደኝነት ተናግሯል ።

«ከብሩንዲ ስሰደድ ፖሊሶች አግኝተውኝ፣ እየተከተሉኝ እንገድልሃለን ይሉኝ ነበር ። እኔን እግዚአብሄር አትርፎኛል ። ሌሎች ዘመዶቼ ግን አልታደሉም ባለቤቴ ተተኩሶባት ተገደለች እናቴን አባቴንም እንዲሁ አጥቻለሁ ።ሌላ ዘመዴ ደግሞ ሐይቁን ሲያቋርጥ ሰጥሞ ቀርቷል ።»

ሉዜናዳ ውስጥ ድየዶኔን ጨምሮ 15 ሺህየሚሆኑ ስደተኞች አሉ ።የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR እንደሚለው ከ230 ሺህ በላይ የብሩንዲ ዜጎች ጎረቤት ኮንጎ ታንዛንያ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ተሰደዋል ። ስደተኞቹ ከሃገራቸው የወጡት ሥልጣን ላይ የሚገኙትን የፕሬዝዳንት ፕየር ንኩሩንዚዛ የፀጥታ ኃይሎችና የደጋፊዎቻቸውን ጭቆናን ክትትልን ሽሽት ነው ።ንኩሩንዚዛ የሃገራቸው ህገ መንግሥት ከሚፈቅደው ውጭ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን እወዳደራለሁ በማለታቸው በብሩንዲ በተነሳው ብጥብጥ ሰበብ ከ400 የሚበልጥ ህዝብ ህይወት ጠፍቷል ። ከሃገራቸው የተሰደዱት የብሩንዲ ዜጎች ባሉበት የሰላም አየር መተንፈስ ቢችሉም አሁንም ለደህንነታቸው መስጋታቸው አልቀረም ።ከስጋታቸው አንዱ ያሉበት

ቦታ ለብሩንዲ ድንበር በጣም ቅርብ መሆኑ ነው። እኚህ የብሩንዲ ስደተኛከዚህ ሌላ ሌሎችም ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል ።

«የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ለደህንነታችን አስተማማኝ የሆነ ቦታ ሊወስደን ይገባናል ።እዚህ ከባድ ችግር ውስጥ ነው ያለነው ።እንራባለን ።በወር የሚሰጠን 15 ዶላር ነው እንዴት ነው በዚህ መኖር የሚቻለው ።»

በመሠረቱ የUNHCR ተግባር መሆን የነበረበት የሰዎችን ደህንነት ማስጠበቅ ነበር ። የድርጅቱ ባልደረባ ማሃመት ኑር አብደላህ እንዳመኑት በቅርቡ አንድ ስህተት ተሰርቶ ነበር ። ሆኖም ጊዜያዊ መፍትሄ ተገኝቶለታል

« የምግብ ራሽን በወቅቱ ባለመሰጠቱ ጥር 8 ተቃውሞ ነበር ።ከአለም የረሃብ መቋቋሚያ ድርጅት ጋር ጊዜያዊ መፍትሄ ፈልገን ተቃውሞውን አርግበናል ።»

በመጠለያው የተነሳው ተቃውሞ በመላ ሃገሪቱ መወያያ ሆኖ ነበር ። በወቅቱ ከዋና ከተማይቱ ኪንሻሳ ስደተኞቹን ለመጎብኘት አንድ ባለሥልጣን ወደ መጠለያው ሄደው ነበር ። አንዳንድ ስደተኞች ደግሞ በመጠለያው ለገጠማቸው ችግር የራሳቸውን መፍትሄ እየፈለጉ ነው ። ይህን ከሚያደርጉት አንዷ ማኒራኪዛ ቦራ ናት ። ማኒራኪዛ ቦራ ከብሩንዲ የተሰደደችው የመንግሥት ሚሊሽያዎች ባለቤቷን ከገደሉባት በኋላ ነው ። ስለ ወደፊቱ ህይወቷ ፤ ሌሎች እስኪወስኑላት መጠበቅ አልፈለገችም ። በመጠለያው የራስዋን ቡና ቤት ከፍታ ካሳቫና አተር በ500 የኮንጎ ፍራንክ ፣ሩዝ በስጋ በ1 ዩሮ ከሃምሳ ሳንቲም በሚገመት ዋጋ ትሸጣለች ።የስኳር ህመምተኛዋ ማኒራኪዛ ባላት አነስተኛ ገቢ ለጤናዋ አስፈላጊ የሆነውን የተመጣጠነ ምግብ ልታገኝ ችላለች ። ሃገር ሰላም ሲሆን ወደ ብሩንዲ መመለስ ትመኛለች ።አንዳንዴ በመጠለያው የሚፈጠሩት ችግሮች ግን ያሳስቧታል ።

«እዚህ መሆን በመቻሌ እደለኛ ነኝ ።ሆኖም የፀጥታ ኃይሎች ስደተኞች ጋ ሲመጡ ውጥረት ይፈጠራል ። አንዳንዶቻችን ትዕዛዝ የምንቀበል ሰዎች አይደለንም ።እንደኔ ያሉ ስደተኞች በመጠለያዎች ውስጥ የሚሰጣቸውን መመሪያዎችን ማክበር ይገባቸዋል ። ፀጥታ አስከባሪዎችም ስደተኞችን መተንኮሳቸውን ማቆም አለባቸው ። »

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic