የብሔራዊ ቡድኑ ሽንፈት እና የሳዑዲ ተመላሾች ስጋት | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 16.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የብሔራዊ ቡድኑ ሽንፈት እና የሳዑዲ ተመላሾች ስጋት

ሳዑዲ ዓረቢያ በሕገወጥ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በአጠቃላይ ከሀገሪቱ ካለ ብዙ እንግልት እንዲወጡ የሰጠችው ቀነ-ገደብ ሊጠናቀቅ ጥቂት ጊዜያት ብቻ ቀርቶታል። በጋና ብሔራዊ የእግር ኳስ  ቡድን ኃያል ምት የገጠመውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በተመለከተም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የተንሸራሸሩ አስተያየቶችን አካተናል።   

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:47

ሳዑዲ ዓረቢያ፤ ኢትዮጵያ እና ጋና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች

ሳዑዲ ዓረቢያ በሕገወጥ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በአጠቃላይ ከሀገሪቱ ካለ ብዙ እንግልት እንዲወጡ የሰጠችው ቀነ-ገደብ ሊጠናቀቅ ከሁለት ሣምንት በታች ብቻ ቀርቶታል። ቀነ-ገደቡ ላይ ለመድረስ የጊዜው መክነፍ በሳዑዲ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች ዘንድ ውጥረት አንግሷል። በዛሬው መሰናዶዋችን ሰፋ ያለ ቦታ የሰጠነው ርእሰ-ጉዳይ ነው።  ለአፍሪቃ ዋንጫ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ከጋና ጥቋቁር ከዋክብት ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከባድ ሽንፈት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የስላቅ ምንችጭ ኾኗል።  

ሳዑዲ ዓረቢያ ሕገወጥ ናቸው ያለቻቸው የውጭ ሃገራት ነዋሪዎች ከሀገሪቱ እንዲወጡ የሰጠችው የ90 ቀን የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀረቡት በአሁኑ ወቅት ውጥረቱ አይሏል። ፌስቡክ እና ትዊተርን በመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ጎልተው የሚታዩ አስተያየቶች ነዋሪዎች በመውጣት እና እዛው በመቅረት መሀል አጣብቂኝ ውስጥ መውደቃቸውን ያመለክታሉ።

ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ዓረቢያ ያሉበት ኹኔታን በተመለከተ ወኪላችን የላከልን የቪዲዮ ዘገባም ይህንኑ አመላካች ነው። የቪዲዮ ዘገባውን በፌስቡክ ገጻችን ለአተከታዮቻችን አቅርበናል። የቪዲዮ ዘገባውን 24 ሰአታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ  600 ያኽል ሰዎች ተቀባብለውታል። 400 ግድም ወደውታል። ዘገባው ከመቶ ሺህ በላይ ለሚኾኑ ሰዎች ደርሶም አምሳ ሺህ ግድም ሰዎች ተመልክተውታል። ከዘጠና በላይ አስተያየቶች ደርሰውናል።

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው ይኽ ቁጥር የቪዲዮ ዘገባው ፌስቡክ ገጻችን ላይ ከወጣ 24 ሰአት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው። አስተያየቶቹ በአብዛኛው ነዋሪዎች ከምንጊዜውም በበለጠ ስጋት እንዳጠላባቸው ይጠቁማሉ። 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አብዛኞቹ ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ የአውሮፕላን ቲኬት ለማግኘት እና ለመግዛት ፈተና እና መንገላታት እንደገጠማቸው ጠቅሰዋል። እስካሁን ድረስ የት ዘግይታችሁ ነው አሁን ጊዜው ሊያልቅ ሲል መንግሥት ላይ የምታማርሩት የሚሉ አስተያየቶችም ተሰጥተዋል። ወደ ሀገር ቤት ብንገባ የሚገጥመን ሌላ መከራ ነው፤ ስለዚህ እዚሁ ሁሉንም እንደ አመጣጡ እንቀበላለን ያሉም አሉ። 

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ የተለመደ ስለሆነ እንዲሁም ነዋሪዎቹ የእኛን መቆየት ስለሚፈልጉ እንግልት አይደርስብንም የሚሉ የመዘናጋት ሁኔታ የሚታይባቸው አስተያየቶችም ተሰጥተዋል። ሁሉንም ነገር ለፈጣሪ የተዉ፤ የከዚህ ቀደም በደል እና ግፎችን በማስታወስ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ሀገሪቱን የረገሙም አልታጡም።  

«እኔ ሳኡድ ነበርኩ የኖርኩት ቢያንሰ 2 ይሆነኛል ውጡ ሲባል ወጣሁ ብመጣ የሰራሁት ቤት ፈርሶ አገኝሁት» የሚል የዋትስአፕ የጽሑፍ አስተያየት የደረሰን ከኢትዮጵያ ነው። «የኢትዮጽያ መንግስት ለዜጎች እንኳን ወደሀገራቸው ገና ለሚመለሱት ይቅረና በሀገሪቱም ላሉት የስራ እደል አልፈጠረም እንደውም ለዜጎቾ ምንም አይነት አመለካከት የለውም»  ይኽም ከኢትዮጵያ የደረሰን  መልእክት ነው።

«ኢትዮጲያ እኮ እኛን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ነው የሚያዩን። እሺ እንደ ሁለተኛ ዜጋማ ባያየን ሳኡድ ባወጣችው ዐዋጂ ለምን እያፋጠኑ አይሰሩም? በሳኡድ የሚገኙ ኢንባሲ እየሰራን ነው ይላሉ፤ ግን በተላይ ገብተው ሲያዩት ምንም የለም። ከስደት ብሶ ለምን በየሰአቱ ተገኝተው በጥሩ ሁኔታ አያስተናግዱም?» ሲሉ ያጠየቁት አስተያየት ሰጪ      «እዝነት ስለሌላቸው ነው እንጂ አሁን ይህ ቀን አልቆ አንድ ሰው ቢሞት ከኢትዮጲያወያን መካከል ተጠያቂም የኢትዮጲያ መንግስት መሆኑን እንደታውቁት ግን ቢሞቱም ለሱ መቀነሱ ነው ግን ስራውን አንድ አምላክ ብቻ ይይለት እኛስ መቸም አልታደልንም ትምህርትም ተምረን ስንጨርስ የስራ እደል አይፈጥርልን በከብት እርባታ አየተባልን በንብ እርባታ ይለናል ብቻ የተመቸ ነገር አለገኝንም» መልእክቱ የደረሰን ከሳዑዲ ዓረቢያ ነው። 

በአንጻሩ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግ፤ እያደረገም እንደገሚገኝ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ጨምሮ በተለያዩ የመገናኛ ዘርፎ ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር ለመጋጠም ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ጋና አቅንቶ ነበር። በግል ችሎታ እና በቡድን እጅግ ከተደራጀው የጋና ቡድን ጋር ኩማሲ ስታዲየም ውስጥ የገጠመው የኢትዮጵያ ቡድን በተወርዋሪ ኮከቦቹ ኃያል ምት ገጥሞታል። ብሔራዊ ቡድኑ 5 ለ0 የተሸነፈ ሲሆን፤ ስድስት ለዜሮ ከመሆን የተረፈው ለጥቂት ነው። እግር ኳስ በኢትዮጵያ ተገቢው አስተዳደር እንዳላገኘ እና የይድረስ ይድረስ በጥድፊያ ሁሉም ነገር እንደሚከወን አስተያየት የሰጡ በርካቶች ናቸው። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ
 

Audios and videos on the topic