የብሌር-ቡሽ ዉይይትና አፍሪቃ | ኤኮኖሚ | DW | 08.06.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የብሌር-ቡሽ ዉይይትና አፍሪቃ

«እንደሚመስለኝ-ያን የተቸገረ ክፍለ-ዓለም ለመርዳት---ብዙ ሚሊዮን ሕዝብን ከሚያሰቃየዉ ድሕነትና እጦት ለማዉጣት የምርና የጋራ ፍላጎቱ አለ።»

ብሌርና ቡሽ

ብሌርና ቡሽ

ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ አፍሪቃ ላይ ያላቸዉን ዕዳ መቶ በመቶ ለመሠረዝ የሁለቱ ሐገሮች መሪዎች ተስማሙ።የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌርና የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ትናንት ዋሽንግተን ዉስጥ ከተወያዩ በሕዋላ እንዳስታወቁት ሌሎች አበዳሪ ሐገራትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ሐሳቡን ለቡድን ስምንት ጉባኤ ያቀርባሉ።አፍሪቃን ከችግር ለማላቀቅ «የአፍሪቃ ማርሻል ዕቅድ» የሚል መርሕ የነደፉት ቶኒ ብሌር ወደ ዋሽንግተን የተጓዙት ፕሬዝዳንት ቡሽ ዕቅዳቸዉን እንዲደግፉ ለማግባባት ነዉ።ቡሽ መንግሥታቸዉ ዕዳ ከመሰረዝ ሌላ ለአፍሪቃ 674 ዶላር አስቸኳይ ሠብአዊ ርዳታ እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋል።

የጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር መንግስት «የአፍሪቃ ማርሻል ዕቅድ» ላለዉ መርሑ ስኬት የበለፀገዉ ዓለም ሃያ-አምስት ቢሊዮን ዶላር እንዲረዳ ይሻል።ብዙዎቹ የብሪታንያ ተሻራኪ ሐብታም-ሐያል ሐገራት በተለይም ዩናይትድ ስቴትስ እከትናንት ድረስ ለብሬርና ለመንግስታቸዉ ዕቅድ የሰጡት ቀዝቃዛ መልስ-ዘመቻዉንም ዕቅዱንም በጅምር ያስቀረዋል የሚል ሥጋት አሳድሮ ነበር።

ብሌር ባለፈዉ ወር ለሰወስተኛ ዘመነ-ሥልጣን ከተመረጡ ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ የቅርብ ወዳጅ ተባባሪያቸዉን ለማነጋገር ወደ ዋሽንግተን የተጓዙትም ትልቁን ሥጋት በትልቅ ወዳጃቸዉ ድጋፍ ለማስወገድ ነዉ።በፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊ ቡሽ።ቡሽ ወዳጃቸዉን አላሳፈሯቸዉም።ብሌር ከዉይይቱ በሕዋላ።

«እንደሚመስለኝ-ያን የተቸገረ ክፍለ-ዓለም ለመርዳት---ብዙ ሚሊዮን ሕዝብን ከሚያሰቃየዉ ድሕነትና እጦት ለማዉጣት የምርና የጋራ ፍላጎቱ አለ።»

ይሁና የጋራ መግባባቱ አፍሪቃን ለመርዳት ብሌር የነደፉትን ሰፊ ዕቅድ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ሙሉ በሙሉ መቀበላቸዉን አያረጋግጥም።ብሌር ከሰፊ ዕቅዳቸዉ መሐል-በያዝነዉ ወር ማብቂያ ስኮትላንድ-የሚያስተናግዷቸዉ የቡድን ሥምንት አባል ሐገራት መሪዎች ስድስት ቢሊዮን ዶሩን እንዲያፀድቁላቸዉ ይፈልጋሉ።ፕሬዝዳንት ቡሽ ሐሳቡን እንዳለ መቀበል-አለመቀበላቸዉን በግልፅ አልተናገሩም።ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪቃ የምትሰተዉን ርዳታ-መጨመሯን በተጨመረዉ ላይ ለመጨመር ማቀዷን ግን ቡሽ አረጋግጠዋል።

«ለአፍሪቃ የምንሰጠዉን ርዳታ በሰወስት እጥፍ ጨምረናል።የአፍሪቃ ጉዳይ የዉጪ መርሔ የሚያተኩርባቸዉ ክፍል ነዉ።ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመዋጋት የቀይስነዉ ጠቃሚ መርሕ ገቢር እየሆነ ነዉ።የእልፈ-አመቱ ፈተና---የምንለዉ።የበለጠም እናደርጋለን።»


በርግጥም ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ሥልጣን ከያዙ ወዲሕ ዩናይትድ ስቴትስ ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመወጋት የምትሰጠዉን ርዳታ በእጅጉ ጨምራለች።ዩናይትድ ስቴትስ ባሁኑ ወቅት የምትሰጠዉ አጠቃላይ አለም አቀፍ የልማት ርዳታ ካጠቃላይ አመታዊ ምርቷ 0.18 ከመቶ ነዉ።ይሕ የርዳታ መጠን ሌሎች የምዕራብ ሐገራት ከሚሰጡት ጋር ሲነፃፀር-ግን ትንሽ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእልፈ-አመቱ ዕቅድ ላለዉ መርሁ ገቢራዊነት የበለፀገዉ አለም ከአጠቃላይ አመታዊ ምርቱ ሰባት ከመቶዉን እንዲለግስ ከጠየቃዉ ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የአሜሪካ ርዳታ ቅምም አትል።

ፕሬዝዳንት ቡሽ የብሪታንያ እንግዳቸዉን ካነጋጋሩ በሕዋላ ሐገሮቻቸዉ መቶ በመቶ ዕዳ እንደሚሰርዙ ማስታወቃቸዉ፣ ሐሳቡን ሌሎቹ የቡድን ስምንት አባል ሐገራት እንዲደግፉት እመጠየቃቸዉ ግን ጥሩ ጅምር-ትልቅ ተስፋ ነዉ።

«በተሐድሶ ለዉጥ ጎዳና የሚጓዙ-ከፍተኛ የዕዳ ጫና ያለባቸዉ አዳጊ ሐገራትን መርዳት አለብን። የዕዳ ክምር ሊጫናቸዉ አይገባም።አበዳሪ ሐገራት መቶ በመቶ እዳ እንዲሰርዙ ሐገሮቻችን ቡድን-ስምንትን ይጠይቃሉ።ይሕ ተጨማሪ ሕብት በመስጠት የአለም ባንክና የአፍሪቃ ልማት ባንክን የገንዘብ አቅምና ትስስርን እናጠናክራለን---።»


በመጪዉ ሳምንት የሚሰበሰቡት የቡድን ሰባት-(ስምተኛዋ ሩሲያ ስትቀነስ) አባል ሐገራት የገንዘብ ሚንስትሮች የእዳ ሥረዛዉን እንዲሰረዝ ቡሽና ብሌር ያቀረቡትን ሐሳብ ይመረምራሉ።ከተስማሙ ዕዳዉ የሚሰረዝላቸዉን-ሐገራት ይመርጣሉ።ፕሬዝዳንት ቡሽ ሐገራቸዉ ከእዳ ስረዛዉ ሌላ ስድስት መቶ ሰባ አራት ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የሰብአዊ እርዳታ ለአፍሪቃ እንደምትሰጥ አስታዉቀዋል።ከተጨማሪዉ እርዳታ አራት መቶ ሚሊዮን ያሕል በረሐብና፣ ጦርነት ለተጎዱት ለምሥራቅ አፍሪቃን ሐገራት የሚሰጥ ነዉ።