የቤኔዲክት 16ኛ የስንብት ዜና | ዓለም | DW | 11.02.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የቤኔዲክት 16ኛ የስንብት ዜና

የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት የቤኔዲክት 16ኛ በእድሜ መግፋት፤ የመንፈስና አካል ጥንካሬ ዉሱንነት ምክንያት መንበር ለመልቀቅ መዘጋጀት ለብዙዎች የተጠበቀ ዜና አልነበረም።

በሰበር ዜና ነቱ ይፋ ሲደረግም ከታዋቂ መገናኛ ብዙሃን ሽፋንነት አልፎ የየሀገራቱ መንግስታትና የሃይማኖት መሪዎች በዉሳኔያቸዉ ከመደነቅ በላይ አክብሮታቸዉን ሲገልፁ ተስተዉሏል።

የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ለሀገራቸዉ ኩራት መሆናቸዉን በማወደስ ዉሳኔያቸዉ የሚከበር መሆኑን ሲገልፁ የፈረንሳዩ አቻቸዉ ፍርናሷ ኦሎንድም እጅግ የሚከበር ዉሳኔ በማለት አድናቆታቸዉን ገልፀዋል። የተለያዩ ሀገራት የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች በበኩላቸዉ ሊቀጳጳሳቱ በማስተዋል ከወዲሁ ያሳለፉት ዉሳኔ ለቤተክርስቲያኑቱ ህልዉና የሚበጅ መሆኑን በመጠቆም አርቆ አሳቢ ሲሉ አወድሰዋቸዋል። 

በጎሮጎሮሳዊዉ 2005ዓ,ም የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት የሆኑት ቤኔዲክት 16ኛ በጎርጎሮሳዊዉ 1927ዓ,ም ሚያዝያ 16ቀን በጀርመን ባርቫሪያ ፌደራል ግዛት ማርትል አም ኢን በምትባል ስፍራ ነዉ የተወለዱት። የያኔዉ ዮሴፍ አልይዝ ራትዚንገር ሶስት ልጆች ለነበሯቸዉ ወላጆቻቸዉ ትንሹ ናቸዉ። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በወጣትነት እድሜያቸዉ ለጥቂት ጊዜያት በጀርመን ናዚ ሠራዊት ዉስጥ ተመልምለዉ ቆይተዋል። እሳቸዉ የዛሬ 20ዓመት ለታይም መጽሔት እንደለጹትም ብዙም በዘርፉ ሳይሰሩ በተባበሩት ኃይላት ተማርከዉ በጦር ምርኮኝነት ለወራት ታስረዋል። ሙኒክ ዩኒቨርሲቲ በስነመለኮት የዶክትሬት ዲግሪያቸዉን በመያዝም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በፕሮፌሰርነት ደረጃ ሲያስተምሩ ቆይተዋል። በሙኒክ እና ፍራይዚግ ሊቀጳጳስነት ያገለገሉት ቤኔዲክት 16ኛ በቀዳሚያቸዉ ሊቀጳጳሳት ዮሃንስ ጳዉሎስ ዳግማዊ የካርዲናልነት ብሎም የእምነቱ ዶግማ ግሩም አስጠባቂ የሚል አክብሮት ሲቸራቸዉ ብዙም አልቆየም።

86ኛ ዓመታቸዉን የፊታችን ሚያዝያ የሚያከብሩት አባ ቤኔዲክት በእድሜ እና ጤና ምክንያት ኃላፊነታቸዉን በአግባቡ መወጣት እንደማይችሉ በማስረዳት መንበራቸዉን ለመልቀቅ መወሰናቸዉን ዛሬ ይፋ ሲያደርጉ የዕምነቱን ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ማስደንገጣቸዉ አልቀረም። በአዲስ አበባ ከተማ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአስተማሪነት፤ በመፈንሳዊ መሪነት፤ እንዲሁም የማኅበር አለቃ በመሆን የሚያገለግሉት አባ ግሩም ተስፋዬ እንደሚሉትም በቤተክርስቲያኒቱ ታሪክ የዛሬ ስድስት መቶ ዓመትም በልዩ ምክንያት በህይወት ሳለ መንበሩን በፈቃዱ የለቀቀ አባት ነበር። የእሳቸዉ በፈቃዳቸዉ መንበራቸዉን ለመልቀቅ መወሰንም ከግል ሃሳባቸዉ ይልቅ የቆሙለትን ተልዕኮ ያስቀደሙ መሆናቸዉን እንደሚያሳይ ነዉ አባ ግሩም የሚናገሩት። የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም የዓለም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አካልነቷ የሌላዉን ስሜት ከመጋራት የዘለለ ነገር እንደማያስከትላባት አመልክተዋል። ቤኔዲክት 16ኛ ይህን ዉሳኔያቸዉ ይፋ ያደረጉት ዛሬ ከቀትር በፊት ካርዲናሎች በተሰበሰቡበት ሲሆን ከቢሊዮን የሚልቁ ተከታይ ምዕመናን ያሏትን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለመምራትና ኃላፊነትን ለመወጣት የመንፈስና የአካል ጥንካሬ እንደሚጠይቅም ግልፅ አድርገዋል። ሊቀጳጳሳቱ ዉሳኔያቸዉን ለቤተክርስቲያኒቱ ህልዉና ወሳኝ ብለዉታል። ቫቲካን አዲስ የሃይማኖት መሪዋን በመጋቢት መገባደጃ እንደምትመርጥ ይጠበቃል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic